የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ ከአሜሪካ አቻቸው ማይክ ፖምፒዮ ጋር ተወያዩ

 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ጋር ተወያይተዋል።

ሚኒስትሮቹ ዋሽንግተን በሚገኘው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባካሄዱት ውይይት በሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነትና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

በዚህ ወቅትም አቶ ገዱ ኢትዮጵያ እያከናወነችው ባለው ለውጥ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም መስፈን አሜሪካ እያደረገች ላለው ድጋፍ ኢትዮጵያ ታላቅ ግምት የምትሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢኮኖሚ መስክ ለሚደረገው ሀገር በቀል የምጣኔ ሃብት የለውጥ ጉዞ እና በተቋማት ግንባታ ረገድ አሜሪካ ድጋፏን አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ውይይት በውጤት እንዲቋጭ እና በሶማሊያ ዘላቂ ሰላምን በመገንባት ረገድ ጥረቷን እንደምትገፋበት የገለጹት አቶ ገዱ፥ለዚህ ስኬት የአሜሪካ አጋርነት ወሳኝ እንደሆነም አስረድተዋል።

ህዳሴ ግድቡ ጋር ኢትዮጵያ የማንንም ጥቅም ለመጉዳት ሳይሆን የህዝቦቿን የዘመናት የልማት ጥያቄ ለመመለስ የምትገነባው ሀገራዊ ፕሮጀክት እንደሆነም ገልጸዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ በበኩላቸው፥ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የኖቤል ሽልማታቸውን በመቀበላቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ ይህም ለጀመሩት የለውጥ ጉዞ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርላቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

አሜሪካ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ እንደምትደግፍ እና በተለይም የአሜሪካ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ ሄደው መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ግፊት እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል።

ለዚህም ስኬት የተቋማት የተቀላጠፈ አገልግሎት አሰጣጥና የኢንቨስትመንት ስራ ምቹነት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አስታውቀዋል።

ከቀጣናው ሰላምና መረጋጋት አኳያ በደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ጉዳይ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን መስተጋብር አጠናክራ እንደምትቀጥል መናገራቸውን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ልዩነታቸውን በውይይት ብቻ እንዲፈቱ የሀገራቸው ጽኑ ፍላጎት መሆኑን ገልጸው ለዚህም ድጋፏ ይቀጥላል ብለዋል።

ኤፍ ቢ ሲ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.