«የቷ ኢትዮጲያ» ለሚለው ለኡስታዝ አህመዲን ጀበል ጽሁፍ የተሰጠ አጭር ሂስ – ብሩክ አበጋዝ

ስለ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል ሌላ ሀተታ መጻፌ አይቀርም ግና የሚጨቀጭቁኝ የእሱ አድናቂወች ስላሉ ለጊዜው ብዬ ከዚህ ቀደም የጻፍኩትን ለጠፍኩት። “የቷ ኢትዮጲያ” የሚለውን የእሱን ጽሁፍ ቅድሚያ ላነበበ ሰው ጥሩ ሀተታ ነው።
————————-
«የቷ ኢትዮጲያ» ለሚለው ለኡስታዝ አህመዲን ጀበል ጽሁፍ የተሰጠ አጭር ሂስ

የኢትዮጵያን ታሪክ ከእስላማዊ ትግል እና መሰዋዕትነት ዐውድ አንጻር የጻፈው አህመዲን ጀበል <<የአክሱማውያን ሥርወ መንግስት እስካበቃበት ድረስ የትኛውም የአክሱም መሪ ራሱን ኢትዮጵያዊ እንደሆነ እንዲሁም የሚገዛት ሀገር “ኢትዮጵያ” እንደምትባል የገለፀበት ማስረጃ የለም፤ ሀገራችንን “ኢትዮጵያ” በማለት መጥራት የጀመሩት የ13ኛው ክፍለ ዘመን ልሂቃን ነበሩ።>> በማለት ኢንሳይክሎፒዲያ ኢትዮፒካን በመጥቀስ ያትታል። ነገር ግን ሆን ብሎ ላለመጥቀስ ካልፈለገ በቀር ከ13ኛው ክፍለ ዘመን በፊት በ9ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የአክሱም ንጉሥ የነበረው ድል ነዓድ ለኑብያው ንጉሥ ጊዮርጊስ በግዕዝ ቋንቋ ደብዳቤ ሲጽፍ ስሙን ሳይጠቅስ “ንጉሠ ኢትዮጵያ” ማለቱን ሳያውቅ ቀርቶ አይመስለኝም።

አህመዲን ጀበል የዓፄ ካሌብ ጦር ወደ የመን አገር ነጅራን ሲዘምት ቆሞ ያየው እና በ520ዎቹ ገዳማ ወደ አክሱም የመጣው የግብጽ ሲና ቅድስት ካትሪን ገዳም መነኩሴ የነበረው ኮስሞስ አክሱምን “ኢትዮጵያ” ብሎ እንደጠራት ይገልጽ እና መልሶ ደግሞ የዚህ ኮስሞስ የተባለ መነኩሴን ምስክርነት በመቃወም ዓፄ ካሌብን ጨምሮ ከአክሱማውያን መሪዎች ውስጥ የትኛውም ንጉሥ ራሱን “ኢትዮጵያዊ” ሀገሩንም “ኢትዮጵያ” ሲል አልጠራም በማለት የሚጋጭ ማብራሪያ ያስቀምጣል። አስገራሚው ነገር ግን የአክሱማውያን መሪዎች ደግሞ ኢትዮጵያውያን አይደለነም ብለው ለመናገራቸው ማስረጃ አያቀርብም። ነገሥታቱ ኢትዮጵያውያን አይደለንም ብለው እስካላሉ ድረስ በወቅቱ ምስክርነቱን የሰጠውን የኮስሞስን ሀሳብ ውድቅ ለማድረግ አይቻልም።

አህመዲን ጀበል “ኢትዮጵያ” የሚለው ስያሜ የኑብያ ሕዝቦች እና ማዕከሉ ሜሮይ እና ናፕታ ለነበረው የኑብያ መንግስት መጠሪያ ነው ብሎ ቢያምንም፤ የኑብያ ሕዝቦች ወይም መንግስታቸው ራሳቸውን ኢትዮጵያውያን ነን ብለው ለመጥራታቸውም ማስረጃ አያቀርብም። አህመዲን ጀበል መነኩሴው ኮስሞስ አክሱምን “ኢትዮጵያ” ብሎ ቢጠራትም የአክሱም ነገሥታት ራሳቸውን ኢትዮጵያዊ ብለው የገለጹበት ማስረጃ እስከሌለ ድረስ (ማስረጃ ግን አለ) “ኢትዮጵያዊ” መባላቸውን አልቀበልም እስካለ ድረስ፤ በዚሁ መንገድ ኑብያውያን ወይም ኩሻውያን ራሳቸውን “ኢትዮጵያዊ” ብለው ሳይጠሩ እሱ ግን “ኢትዮጵያውያን” የሚባሉት እነሱ ናቸው ብሎ ለማለት እንዴት ይችላል? ነው ወይስ ነገሩን የሚመለከትበት መለኪያ ሁለት ነው? አህመዲን ጀበል አለፍ ብሎ ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ በ4ኛው ክፍለ ዘመን ገዳማ የነበረውን ንጉሥ ኢዛና ወደ ቤጃ ሕዝቦች ያደረገውን ዘመቻውን በግሪክ ቋንቋ ሲያጽፍ ”ኢትዮጵያ“ የሚለውን ቃል እንደተጠቀመ ይጠቅስና ከራሱ መነሻ ሀሳብ ጋር የሚጋጭ ሀተታ አስቀምጧል።

ለማንኛውም ከላይ እንደተገለጸው የአክሱም ሥርዎ መንግስት ነጋሢ የነበረው ድል ነዓድ በ9ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ራሱን “ንጉሠ ኢትዮጵያ” ብሎ በመጥራት ደብዳቤ የጻፈው አህመዲን ጀበል “ኢትዮጵያ” የሚለው ስያሜ የእነሱ ነው ብሎ ለሚከራከርላቸው ለኑብያ መንግስት ነበር። ወደ ሌላ ማስረጃዎች ሳንሄድ አህመዲን ጀበል በራሱ ጽሁፍ ላይ ያስቀመጠው ሀሳብ መልሶ ራሱን የሚቃረነው መሆኑን ለመረዳት ይቻላል።

አህመዲን ጀበል ከጽሁፉ ለመረዳት እንደሚቻለው “ኢትዮጵያ” የሚለውን ስያሜ አሁን ከሚወክለው ሕዝብ እና መንግስት እንዲሁም “ውዷ ሀገራችን” እያለ በተደጋጋሚ ከሚጠቅሳት የአሁኗ ኢትዮጵያ ይልቅ የእኛ ስያሜ ነው ብለው ካልጠየቁት ሱዳናውያን/ኑብያውያን ጋር የሚያይዘው ስያሜው በመጽሀፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ በመጠቀሱ እና ኢትዮጵያውያን የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ሰባኪዎች እና አማኞች እነዚህን በመጽሀፍ ቅዱስ አልፎ አልፎ በየቦታው ያሉ ጥቅሶችን እየጠቀሱ “ኢትዮጵያ የክርስትያን ደሴት ናት” እያሉ በመስበካቸው እና ይኼም ኢትዮጵያ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ የነበረውን የእስልምና ሃይማኖትን እውቅና የነፈገ መስሎ ስለታየው እንደሆነ ከጽሁፉ በቀላሉ መረዳት ይቻላል። ነገር ግን ኢትዮጵያ የክርስትያን ብቻ ሳይሆን የብዙ ዓይነት ሃይማኖቶች አማኞች አገር እንደሆነች ለማስረዳት እና ለማስገንዘብ ዋናውን ታሪክ ወደ ጎን ብሎ የእሱን ፍላጎት ብቻ የሚያሟሉ ማስረጃዎችን መርጦ በመጥቀስ አሳማኝ ያልሆነ ድምዳሜ መድረሱ ትክክል ካለመሆኑም በላይ ለትችትና ለትዝብት የሚዳርገው ሆኗል።

ኢትዮጵያ የሚለውን ስያሜ የመንግስት መጠሪያ ያደረገው ድል ነዓድ ብቻ ሳይሆን ከአክሱም ሥርዎ መንግስት ፍጻሜ በኋላ ያሉት ነገሥታትም ጭምር ናቸው። የላሊበላ፣ የነአኩቶ ለአብ፣ የዓምደ ጽዮን እና የዘርዓ ያዕቆብ ታሪከ ነገሥታቸው እያንዳንዳቸውን “ንጉሠ ኢትዮጵያ” በማለት ያወሳቸዋል፤ ከውጭ አገር ሊቀ ጳጳሳትም የሮማው ጳጳስ ዳግማዊ ጳውሎስ በ1556 ለዓፄ ገላውዲዎስ፤ የስፔኑ ንጉስ ዳግማዊ ፊሊጶስ ደግሞ ለዓፄ ሠርጸ ድንግል በላቲን ቋንቋ ደብዳቤ ሲጽፉ “IMPERATOREM AETHIOPIAE (የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት)” በማለት ነበር። የሆነው ሆኖ ከላይ ሪኩለስም እንዳስቀመጠው በዛሬው ዘመን ኢትዮጵያ የሚለውን ስም የወረሰችው አገር እና ኢትዮጵያውያን ነን ብለው የሚጠሩ ሕዝቦች የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ብቸኛ ወራሾች ናቸው ለማለት ባያስደፍርም ከስያሜው እና ከታሪኩ ጋር ግን ከፍተኛ የሆነ ግንኙነት እንዳላቸው አስረግጦ መናገር ይቻላል።

ኢትዮጵያ የሚለው ስያሜ የእኔ ነው ብሎ የጠየቀ የሌላ አገር መንግስትም ሆነ ሕዝብ እስከሌለ ድረስ ይህ ነገር የሚያከራክር አይሆንም። ደግሞም እስካሁን ካሉት የዓለማችን አገራት ውስጥ “ኢትዮጵያ የእኔ ነች“ በማለት የይገባኛል ጥያቄ አንስቶ የተከራከረ አንድም አገር የለም። አንዳንድ ወገኖቻችን ሊቀበሉት ባይፈልጉም ወይም ደግሞ ሌላ ስም የሚሰጡን ቢሆንም ኢትዮጵያ የሚለው ቃል የእኛው ስምና መለያችን ሆኖ እየኖርን ነው። ቀደምቶቻችን ቃሉን መጠሪያቸው ሲያደርጉትም ያለ ምክንያት እንዳልሆነ ለመገንዘብ የሚያዳግት አይሆንም። ታሪክን አንባቢ የሆኑ ሰዎች ከላይ በእነ ዲድሮስ፣ ሆሜር እና ሄሮደተሰ እጅግ ስልጡን እና ገናና ተደርጋ የተገለጸችውን ኢትዮጵያን ከዛሬዋ ኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት እንዳላት ለመቀበል የሚከብዳቸው፤ የዛሬዋ ኢትዮጵያ በድህነት እና ረሀብ የምትታወቅ፤ በሥልጣኔ ደረጃ የዓለም አገራት ጭራ መሆኗ ነው።

የዚህ የሩቁ ዘመንን ታሪክ እንኳን ትተነው በ16ኛው ክፍለ ዘመን የፖርቱጋል ንጉሥ መልዕክተኞች ሆነው ወደ ዓፄ ልብነ ድንግል ዙፋን ችሎት ከመጡት ልዑካን መካከል አንዱ የሆነው አባ አልቫሬዝ በኢትዮጵያ ውስጥ ከራሳቸው ከአውሮፓውያን ጋር ሊወዳደር የሚችል ሥልጣኔ እንደነበር በማስታወሻው ገልጿል። አልቫሬዝ የኢትዮጵያን ሕንጻዎች እና ሥዕሎች እንዲሁም የኢትዮጵያውያኑን የዳኝነት እና የፍትህ ሥርዐት ተመልክቶ ከማድነቁም በላይ፤ የአውሮፓውያኑን በቤተክርስቲያን ውስጥ ሆነው ምራቃቸውን የመትፋት ልማድ፤ በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንደ አስጠያፊ ነውረኛ ምግባር የሚቆጠር መሆኑን ጽፏል። ታዲያ በዚያ የሥልጣኔ ከፍታ ደረጃ የነበረች አገር አሁን ለምን ኋላ ቀር እና ደሃ ሆነች? የአገራት ሥልጣኔ እድገት ቀድሞ ከነበረው ላይ እየተጨመረ፣ እየተሻሻለ፣ ማስተካከያ እየተደረገ፣ ችግሮች እየተቀረፉ የሚሄድ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን እየሆነ ያለው በተቃራኒው ወደኋላ መሆኑ አስገራሚ ከመሆኑም በላይ ሊጠና እና ሊመረመር የሚገባው ጉዳይ ነው።

ግርሃም ሃንኮክ Lost Civilization በሚለው መጽሀፉ አስደናቂዎቹን ጥንታዊ የግብጽ ፒራሚዶች እና በዓለም ዙሪያ ያሉ የተለያዩ ጥንታዊ ቅሪቶችን ከመረመረ በኋላ፤ እነዚህ አስደናቂ እና ብዙ ሺህ ዓመታትን ተሻግረው ዛሬ ድረስ በዚያ በሩቁ ዘመን ታላቅ ሥልጣኔ እንደነበር የሚመሰከሩት ቅርሶች፤ ከዚህ በፊት ምድር ላይ የነበረ እና በዋልታዎች መዛባት ምክንያት ከጠፋ እና ከወደመ እጅግ አስደናቂ ሥልጣኔ የተረፉ ቅሪቶች ናቸው በማለት ያብራራል። በዚህ በዋልታዎች መዛባት ምክንያት የጠፋውን ሥልጣኔ ፕላቶ የሚባለው ግሪካዊ ፈላስፋን ጨምሮ ሌሎች ብዙ የታሪክ፣ የአርኪዮሎጂ እና ኢጂፕቲዮሎጂስቶች የአትላንቲስ ሥልጣኔ ይሉታል።

ግርሃም ሃንኩክ የዚያ የጠፋው አስደናቂ ሥልጣኔ ቅሪቶች እና የከተማ ፍርስራሾች በሜዲትራኒያን ባህር እና በበረዶ በተሸፈነው የአንታርቲካ አህጉር እንደሚገኙ በማስረዳት፤ ከዚህ ውድመት በኋላ የሰው ልጅ ትውስታውን አጥቶ ሥልጣኔን እንደገና ከዜሮ እንደጀመረና አሁን ካለበት ደረጃ እንደ ደረስ ይገልጣል። ምናልባት እንደ አክሱም ዓይነቶቹ የቀደምት ሥልጣኔ አሻራዎች ግርሃም ሃንኩክ እንደሚለው የዚያ የወደመው አስደናቂ ሥልጣኔ ትውፊቶች ይሆኑን? ወይስ ተመሳሳይ የሆነ ተፈጥሯዊ ወይም ሰው ሠራሽ የሆነ አካባቢያዊ አደጋ ሥልጡኖቹን ኢትዮጵያውያንን አጥፍቶ ይሆን? በእንደዚህ ዓይነት አደጋ ምክንያት አካባቢው ባዶ ስለነበረ ይሆን በተለይ አውሮፓውያን የታሪክ ጸሀፍቶች በጥንት ዘመን ከደቡብ አረቢያ ወደ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሕዝብ ፍልሰት እንደ ነበር በዝርዝር የሚጽፉት?

ከዚህ ጋር በተያያዘ የአገራችን የታሪክ ተመራማሪዎች በልማዳዊዩ መንገድ ከዚህ በፊት የተጻፉ የታሪክ መዛግብትን እየጠቀሱና ታላቅ ሥልጣኔ ነበረን፣ ሄሮዶተስ ይህን አለ፣ ዲድሮስ ያን አለ፣ ጸሀፈ ትዕዛዝ እንዲህ አሉ ከሚለው ሀተታ በመውጣት ሃይማኖታዊም ሆነ ዘውጌያዊ አቋማቸው ሳይገድባቸው እውነት እንደተጻፈው ሥልጣኔ ነበረን? በጥንቱ ጊዜ በሳንቲም ገንዘብ ሲገበያይ የነበረ ስልጡን ሕዝብ በኋለኛው ጊዜ ለምን ወደ አሞሌ እና ዕቃን በዕቃ ልውውጥ የገበያ ሥርዐት ተሸጋገረ? የባህር መጓጓዣዎችን ፈጥሮ ባህር አቋርጦ አረቢያን ያስገበረ ሥልጣኔ እንዴት ወደታች ወርዶ ከእንሰሳት ጋር የተቆራኘ ትራንስፖርት ላይ ተወስኖ ቀረ? በአጠቃላይ ሥልጡን ከነበርን ለምን ወደኋላ ቀረን? ወዘተ ዓይነት ጥያቄዎችን ለመመለስ እና የጥንቱ ሥልጣኔ ባለቤቶችን አሁን ካለው ማህበረሰብ ጋር የሚያገናኝ ሥር ነቀል ምርምሮችን ሊያደርጉ ይገባል።

ኢትዮጵያ የሚለው ስያሜ ቀደምትነት የሚጠቁመን ሌላ ነገር ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግስት ፍጻሜ በኋላ እየገነኑ በመጡ ጎሳ እና ዘውጌ ፖለቲከኞች እንዲሁም ፖለቲካዊ ትርፍን ታሳቢ አድርገው ታሪክን የሚቀሽቡ የታሪክ ጸሀፊዎች እንደሚሉት “ኢትዮጵያ” በውስጧ የሚገኙት ዘውጎች ተሰባስበው በመፈቃቀድ እና በመስማማት የፈጠሯት አዲስ ስያሜ የተሰየመላት አዲስ አገር ሳትሆን፤ በተቃራኒው በረዝሙ የታሪክ ሂደት በውስጧ ያሉ ባለ ብዙ ቋንቋ እና ባህል ዘውጎች እና ነገዶችን ለመፍጠር የበቃች አገር መሆኗን ነው። በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት ዘውጎች ለዘመናት የተካሄደው የህዝቦች መስተጋብርና ውህደት ውጤት መሆናቸውን መዘንጋት እጅግ የተሳሳተ ድምዳሜ ይሆናል። በዚህ በረዝሙ የኢትዮጵያ ታሪክ በተካሄዱ ማህበረሰባዊ መስተጋብሮች የጠፉ ዘውጎች፣ ባህሎች እና ቋንቋዎች እንዳሉ ሁሉ በአዲስ መልክ የወጡትም አያሌ ናቸው።

ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን እንደሚሉት የኢትዮጵያ ሕዝቦች የተለያዩ ባህላት ፈጥረው፣ በልዩ ልዩ ጎሳ ተከፋፍለው፣ ለየብቻቸው ተፈናጥረው፣ ተገንጥለው እና ተሸሽገው አልኖሩም። በትንሹ ባለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት ውስጥ በንግድ፣ በጦርነት፣ በሃይማኖት ጉዳይ በመዘዋወር በጋብቻ እና ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን በመለዋወጥ እርስ በራሳቸው ሲገናኙ ኖረዋል። በዚህም ምክንያት እያንዳንዱ ማህበረሰብ የባህል ገጽታዎችን፣ እሳቤዎችንና ጥበቦችን ከሌሎች የመውሰዱን ያክል፤ የራሱ ብቻ የሆኑና ሌሎች ማህበረሰቦች የሌላቸውን ደግሞ ለሌላው ጎረቤቱ ሰጥቷል። በዚህ የመስጠትና የመቀበል ሂደት ውስጥ በአንጻራዊ ሁኔታ ያደገ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ አቋም ያላቸው ባህሎች ለሌሎች የሚያበረክቱት በርከት ሊል ቢችልም እንኳን እነርሱም ከሌሎች የሚቀበሉት ስለሚኖር ሂደቱ ሁለትዮሽ አቅጣጫ ያለው ስለሆነ ተመጋጋቢ ነው። ዳሩ ግን የሰው ልጆች ታሪክ በመሰረታዊ ተፈጥሮው ተራማጅ በመሆኑ ምክንያት፤ በኢኮኖሚ፣ በባህልና በፖለቲካ ከፍ ካለ ደረጃ የደረሰው ወገን ሌሎችን መጫኑ አይቀሬ ነው።
_________________
Notes
1. አህመዲን ጀበል 3ቱ ዓፄዎች እና ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች፤ ገጽ 192
2. ተክለጻዲቅ መኩሪያ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፡ ኑብያ፣ አክሱም፣ ዛጉዬ ገጽ 18
3. አህመዲን ጀበል 3ቱ ዓፄዎች እና ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች፤ ገጽ 191
4. አህመዲን ጀበል 3ቱ ዓፄዎች እና ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች፤ ገጽ 188
5. ተክለጻዲቅ መኩሪያ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፡ ኑብያ፣ አክሱም፣ ዛጉዬ ገጽ 18
* Lost Civilization: Graham Hankock
* Francisco Álvares: A True Relation of the Lands of Prester John of the Indies
6. ዶናልድ ሌቪን፤ ትልቋ ኢትዮጵያ የብዙ ነገዶች ማህበረሰብ፤ ትርጉም ሚሊዮን ነቅንቅ: ገጽ 39

2 COMMENTS

  1. ብሩክ ወልደ ኢትዮጵያ እናመስገናለን የኢሜል አድራሻህን ብትልክልን መልካም ነበር ነገር አለቀ ሲባል እንደ እናንተ አይነት ለክፉ ቀን የተቀመጠ ሰዉ እግዚሀር ለሀገራችን ይጥልላታል። አህመዲን ጀበል ቀላል ሰዉ አይምሰለህ ቀደም ባለዉ ጊዜ የኢዝላሚስት ፓልቶክ ዉስጥ ሲሰጥ የነበረዉን መመሪያ “The Best Solution” የሚባል ትንታግ ወገን የፓልቶክ ክፍል ከፍቶ የአጸፋ መልስ ሲሰጥልን ነበር።ይህን ልጂ ብታገኘዉ ያለዉ ሪሶርስ ቆዳ ለዉጠዉ ለመጡት ኢዝላሚስት አፍ ማስያዣ ነበር ለፍርድ ቤትም ጥሩ ማስረጃ ነበር።
    ዛሬ ላይ አህመዲን ጀበልና ዶ/ር አብይ የማንነት ኮሚቴ አባል አድርጎ የሾመዉ አቡበከር ጋር በመሆን ለሀገር ቤት ተከታዮቻቸዉ ጀሌዎቻቸዉ ይሰጡት የነበረዉ መመሪያ የሚገርም ነበር። ፍትህና ህግ ቢኖር እነዚህ ሰዎች በንብረት ማዉደም ዜጋን በአሰቃቂ ሁኔታ በማስገደል፤የእምነት ተቋማታን በማቃጠል የሚገባቸዉን ዋጋ ያገኙ ነበር ያ ግን ሊሆን አልቻለም። አህመዲን ጀበል ወደ ቤተ መንግስት ወጣ ገባ ከሚሉ ሰዎች አንዱ ሁኗል። አህመዲን ጀበልና አቡበከር ሳይደብቁ የነገሩን ኢትዮጵያ ኢዝላሚስተ ሰቴት እንድትሆን ስሟ እንዲቀየር ባንድራዋም እንዲቀየር ነበር። ይህንንም ከቅርብ ጓደኛቸዉ ከጁዋር አህመድ ጋር አብረዉ ይሰራሉ። በተረፈ እባክህ ለማስተማሩ ጊዜ ካጠረህ ማርከሻዉን እንዲህ አልፎ አልፎ ላክልን። አቶ ጌታቸዉ ረዳ(ኢትዮ ሰማይ አዘጋጅ)፣ አቻምየለህ ታምሩ በተወሰነ ደረጃ ግርማ ካሳን የመሳሰሉ አርበኞችም ብእራቸዉ አይደርቅም ያግዙሃል ደህና ማርከሻም ናቸዉ አድር ባይም አይደሉም ከአስተሳሰባቸዉ ጀርባም ንግድ የለበትም።

  2. Ahmedin is our hero pls if u want any independent source u can see the teklesadik mekoria of nlbian history even u r deaf

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.