ለባልደራስ፣ለኢዜማ፣ ለኦሮሞ ፓርቲ፣ ወይንስ ለፒፒ(ደኢህዴን)? የጉራጌ ህዝብ በቀጣዩ ምርጫ ድምጹን ለማን ይስጥ?

በ ሸምሱ በረዳ
እንደሚታወቀው ቀጣዩ ሃገር አቀፍ ምርጫ ሊካሄድ እንደሆነ ተወስኗል። ውሳኔውን ተከትሎም የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች የየራሳቸውን የምረጡኝ ዘመቻ እና እንቅስቃሴ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታም በፖለቲካው መድረክ አጀንዳ የሚያስይዙ የሚያስፈጽሙ እና ፖሊሲ የሚቀርጹ የፖለቲካ ሃይሎች እንወክለዋለን ብለው የሚሉትን ህዝብ ጥቅም ለማስከበር እየተንቀሳቀሱ ነው። ይህ በሆነበት ሁኔታ ግን ወትሮውንም በፖለቲካ መድረክ ላይ እዚህ ግባ የሚባል ተሳትፎ የሌለው የጉራጌ ህዝብ ምን አይነት የፖለቲካ አሰላለፍ እንደሚያዋጣው በውል የተገነዘበ አይመስልም። ግራ በመጋባትም እንደወትሮው ሁሉ በገዛ ሃገሩ የበይ ተመልካች ሆኖ ይገኛል። የዚህ ጽሁፍ አላማም በመጀመሪያ ስለጉራጌ ህዝብ አጠር ያለ መግቢያ በማቅረብ በፖለቲካ መድረኩ ያሉትን አማራጮች ከጉራጌ ህዝብ ጥቅም እና ፍላጎት አንጻር በማየት በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ ፓርቲዎችን እና የሚወክሉትን አስተሳሰብ ለምርጫ ማሰቀመጥ ነው።
ስለ ጉራጌ
በደቡብ ኢትዮጵያ ከሚገኙ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መካከል የጉራጌ ህዝብ ታሪክ ባህል ቋንቋ እና አመጣጥ ጉራጌዎችን ጨምሮ አብዛኛውን ምሁራን እና የስነህዝብ ተመራማሪዎች ግራ የሚያጋባ ነው። የጉራጌ ምንጭ ከየት ነው? የሚለውን ጥያቄ እንደዚሁ በቀላሉ መመለስ እንደማይቻል በርካታ በዘርፉ ጥናትና ምርምር ያደረጉ ጠበብት ያስረዳሉ። በዚህም የተነሳ ነው “ጉራጌ ብሄሩ ምንድነው?” ለሚለው ጥያቄ መልሱ በአብዛኛው “ጉራጌ ብሄሩ ኢትዮጵያዊነት ነው” የሚል የሆነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አብዛኛውን የስነህዝብ እና የስነቋንቋ ተመራማሪዎች የሚያስማማ አንድ ነገር ግን አለ። ይህውም ምንድነው ጉራጌ በደቡብ ኢትዮጵያ ከሚገኙ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መካከል የሴማዊ ቋንቋን የሚናገር ህዝብ መሆኑ ነው። በጉራጌ ቋንቋዎች መካከል የተወሰነ ልዩነትና አንድነት ቢኖርም ጉራጌ በኩሽ ቋንቋ ተናጋሪዎች (ሲዳማ እና ኦሮሞ) የተከበበ እንደሆነ በርካታ የስነ ቋንቋ ጠበብት በጥናቶቻቸው ያስረዳሉ።
በዘርፉ በርካታ ምርምርና ጥናት ያደረጉ ምሁራንም ጉራጌ በሰሜን በደቡብ በምእራብ እና በምስራቅ አቅጣጫ በአካባቢያዊ ተፈጥሮዎች (ወንዝ እና ተራራ) ለረጅም ዘመናት ተለያይቶ በመኖሩ ምክኛት አንድ የነበረው የጉራጌ ህዝብ ቋንቋ በሂደት ይዘትና ቅርጹን እየቀየረ መምጣቱን እና በተለይም ደግም ጉራጌን ከበው በሚገኙት የኦሮሞ እና ሲዳማ (ኩሻዊ) ቋንቋዎች ተጸኖ ስር በመደቁ ወደ ተለያየ የቋንቋ መደብ መሸንሸኑን ያስረዳሉ።
እንደታሪክ አዋቂዎች ከሆነ የጉራጌ ታሪካዊ ርስት እና ግዛት በስተሰሜን ቀድሞ የሴማዊ ንጉስ ከነበረው የዳዊት ከተማ ተብላ ከምትጠራው የበረራ ከተማ አንስቶ በዋና ዋና ተራሮች እና ወንዞች የታጠረ ነበር። በስተምእራብ የኦሞ ወንዝ፣ በስተደቡብ የጊቤ ወንዝ፣ በሰሜን ምስራቅ የአዋሽ ወንዝ፣ በሰሜን ምእራብ ደግሞ የዋቤ ወንዝ ያካልሉት ነበር። በጉራጌ መሬትም አነስተኛ ወንዞችና ተራሮችም የጉራጌን አሰፋፈር ይወስናሉ። ለምሳሌ በጉራጌ መሬት የሚገኘው ትልቁ የጉራጌ ተራራ ከፍታው ከባህር ጠለል በላይ ሶስት ሺህ ሰባት መቶ አስራ ዘጠኝ ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን በ 8°17′፣ 38°23′ ላቲቱድ እና ሎንጊቱድ ይገኛል።
አንዳንድ የታሪክ አዋቂዎች እንደሚናገሩት ከሆነ የጉራጌ ምንጩ ከአክሱም ስልጣኔ ቀደም የሚል ሲሆን በወቅቱ ከሰሜን ኢትዮጵያ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ሃገር ለማቅናት በተንቀሳቀሱ ሰባት የጉራጌ ጦር አበጋዞች መሪነት ወደ ደቡብ ሃገር ለማቅናት የተንቀሳቀሰ የጦር ሰራዊት በቀድሞዋ በረራ (በአሁኗ አዲስ አበባ) ዋና መቀመጫውን አድርጎ ወደ ደቡብ እስከ ዋቤ ወንዝ ድረስ ሃገር አቅንቶ ያስተዳድር ነበር ይላሉ።
ሴማዊው ንጉስ ዳዊት ቀደምት ከሚባሉት የጉራጌ ነገስታት መካከል ነበር የሚሉ የታሪክ አዋቂዎችም አሉ። እንደታሪክ አዋቂዎቹ ከሆነ ንጉስ ዳዊት በወቅቱ የራሱ የሆነ የመገበያያ ገንዘብ፣የወርቅ ሳንቲሞች እና የራሱ የሆነ የከተማ መሪ እቅድ (ማስተር ፕላን) ያለው ስልጣኔ መገንባት ችሎ ነበር። በጉራጌ ሃገር ጀፎረ የሚባለው ሰፋፊ የአውራ ጎራና መንገድ የዚህ ጥንታዊ የከተማ ማስተር ፕላን እቅድ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል የሚሉ የታሪክ አዋቂዎችም አሉ። የጥያ ትክል ድንጋዮችም ሌላ የቅድመ አክሱም ታሪክና ስልጣኔ ማሳያ ተደርገው ይወሰዳሉ ይባላል።
በሃይማኖት አንጻር ጉራጌ ከአክሱማዊ ስልጣኔ በፊት የነበረ ህዝብ እንደመሆኑ እስልምናንም ክርስትናንም የተቀበለው ከጊዜ በኋዋላ ነው። ቀደምት የጉራጌ ህዝብ እስልምናንም ክርስትናንም አያውቅም ነበር። እስልምናም ክርስትናም ወደጉራጌ የመጡት በኋላ ላይ ነው። የጉራጌ ቀደምትና ዋናው እምነት ደምዋምዊት እና ቦዠ ይባላሉ። ደምዋምዊት የጉራጌ የሴት አምላክ ነች። ቦዠ ደግሞ የወንድ አምላክ ሲሆን በመብረቅ እና በቁጣ የሚታወቅ የሚፈራ የጉራጌ አምላክ ነው።
በኋላ ላይ የግራኝ መሃመድ ወረራን ተከትሎ እስልምና ወደ ጉራጌ ምድር መጣ። በስተደቡብ ጉራጌ የሚገኙት የስልጤ ቤተጉራጌዎችም የግራኝ መሃመድ ወረራ እና ጥቃት የመጀመሪያዎቹ ሰለባ ሆኑ። በጉራጌ መሬት እስልምናን ለመቀበል የመጀመሪያዎቹ ቤተ ጉራጌዎች ስልጤ ቤተጉራጌዎች ነበሩ። በኋላም የግራኝ መሃመድ ወረራ እየከፋ ሲመጣ ገፈቱ ለሎች ቤተጉራጌዎችም ተረፈና እስልምናን በግድ ተቀበሉ። ግራኝ መሃመድም ወረራውን ቀጥሎ በረራን አወደመና ወደሰሜን ተስፋፋ። በመንገዱ ላይ ያሉትን ሁሉ እያሰለመም ቀጠለ።
አንዳንድ የስልጤ ቤተጉራጌ ፖለቲከኞች “የስልጤ ህዝብ የግራኝ መሃመድ ሰራዊት ቅሪት ነው” የሚሉትም ይሄንን የግራኝ መሃመድ ወረራ ታሪክ ከስር መሰረቱ በደንብ ስለማይረዱት ነው። እስልምና በግራኝ መሃመድ ወረራ ተስፋፍቶ ወደ ጉራጌ ምድር ከመምጣቱ በፊት የስልጤ ቤተጉራጌ ህዝብ ከላይ በተጠቀሰው የጉራጌ መሬት ከሌሎች የጉራጌ ቤተሰቦች ጋር አብሮ ይኖር ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ የግራኝ መሃመድ ወረራን ተከትለው ወደ ጉራጌ ሃገር የመጡት ደግሞ ኦሮሞዎች ናቸው። ኦሮሞዎች ግራኝ መሃመድን ተከትለው የተወሰኑ የጉራጌ ቤተሰቦችን (እንደ ሶዶ ጂዳ ያሉትን) በገዳ ስራት ወደ ኦሮሞነት ቀየሯቸው። የጉራጌ ህዝብ “ሰባት ቤት፤ አምስት ቤት” እየተባለ ከመከፋፈሉ በፊት ደግሞ ከላይ እንደተመለከተው አንድ ራሱን የቻለ ጉራጌ የሚባል ህዝብ ነበር።
የግራኝ መሃመድ ወረራን እና የኦሮሞ መስፋፋትን ተከትሎ የተዳከመው የጉራጌ ሃገር በርስ በርስ ግጭት ጭምር ኢኮኖሚውና ስልጣኔው ተዳክሞ የነበረ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ 1875 ላይ በሸዋው ንጉስ ምንሊክ ሸዋ ግዛት ስር ተካተተ። ከ1875 በኋላ ያለው የጉራጌ ታሪክም አሁን የጉራጌ ህዝብ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ታሪክ ባህል እና ማንነት መሰረት ነው።
የጉራጌ ህዝብ በሸዋ ግዛት ከተካተተ በኋላ ለማእከላዊው የምንሊክ አስተዳደር እንደ ማንኛውም በምንሊክ ግዛት ስር እንደተካተቱ ሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ግብር መክፈል ስለነበረበት፤በዛን ግዜ ደግሞ ጉራጌ የሚያመርተው ቆጮ ብቻ ስለነበር፤ የግድ የሚከፍለው ግብር በገንዘብ ወይንም በጉልበት ስለነበር፤ወደ አዲስ አበባ እና የተለያዩ ከተማ ማእከላት በመሄድ በጉልበት እየሰራ ሊስትሮ እየጠረገ ኩሊ እየተሸከመ ግብር መክፈል ጀመረ። የጉራጌ ህዝብ ለማእከላዊ መንግስት ግብር በመክፈል ኢትዮጵያን እንደሃገር ማቅናት የጀመረው ከዛን ጊዜ ጀምሮ ነበር ብሎ ማለት ይቻላል። በሂደትም አነስተኛ ንግድ መስራት እንደ ስጋ መሸጥ ሆቴል ቤት እና ሱቅ መስራት ጀመረ። እነዚህ የስራ መስኮች በወቅቱ ለዝቅተኛ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚተው የስራ ዘርፎች ነበሩ። ጉራጌ አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ አሁን ባለበት የተለያየ ቦታ ተስራጭቶ የሚኖርበት ምክኛትም ይህ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እና የጉራጌ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ሃገር ለመገንባት በተጫወተው ሚና ልክ በፖለቲካ መድረኩ ውስጥ እዚህ ግባ የሚባል ተሳትፎ የለውም። ጥቂት የሚባሉትም የሚያስፈጽሙት አጀንዳ እና ፖሊሲ የጉራጌ ህዝብን ጥቅም ማእከል አድረጎ የሚንቀሳቀስ አይደለም። ይህ በሆነበት ሁኔታ ነው እግዲህ ቀጣዩ ምርጫ የሚካሄደው።
በቀጣዩ ምርጫ የጉራጌ ህዝብ አማራጮች
1.ፒፒ (ደኢህዴን)
በቀጣዩ ምርጫ ለጉራጌ ህዝብ ከቀረቡ አማራጭ ፓርቲዎች መካክል ቀዳሚው ፒፒ (ደኢህዴን) ነው። የጉራጌ ህዝብ የጠቅላይ ሚንስቴር አብይ አህመድ ፒፒ ፓርቲ ውስጥ የሚኖረው ውክልና ሚወሰነው በደኢህዴን ነው። ደኢህዴን እንደፖለቲካ አስተሳሰብ የሚከተለው መስመር ደግሞ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ቁጥር ሁለት ወይንም “የብሄር ብሄረሰቦች መብት” መከበርን ያማከለ ነው ይበል እንጂ በተጨባጭ የጉራጌ ህዝብን የብሄር ብሄረሰብ መብትና ዘለቄታዊ ጥቅም የሚያስከብር መስመር አይደለም። ለዚህ ቀላሉ ማሳያ ደግሞ ደኢህዴን የወያኔ መንግስት ላለፉት 27 አመታት በጉራጌ ህዝብ ላይ የፈጸመውን ወንጀል ለመቃወምም ሆነ ለማስቆም አለመቻሉ ነው። በርግጥ ካለፉት 27 የጨለማ አመታት አንጻር የጠቅላይ ሚንስቴር አብይ አህመድ ፒፒ ለጉራጌ ህዝብ የተሻለ አመለካከት ያለው ነው ይባላል። ይህንን የሚሉ ወገኖች እንደማሳያ የሚጠቀሙት ደግሞ አንዳንድ ስልጣን የተሰጣቸውን የጉራጌ ተወላጆች እንደማሳያ በመጥቀስ ነው። እንደምሳሌም የደቡብ ክልል ምክትል ርእሰመስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳውን፣የሰላም ሚንስቴር ወይዘሪት ሙፈሪሃት ካሚልን እና አምባሳደር ፍጹም አረጋን ያነሳሉ።
በሌላ ወገን ደግሞ የእነዚህ ግለሰቦች ስልጣን ላይ መሾም ከጉራጌ ህዝብ የብሄር ብሄረሰብ መብት ዘለቄታዊ ጥቅም አንጻር ምንም ፋይዳ የለውም ማለት ይቻላል። እነዚህ ሹመቶች የጉራጌ ህዝብን ለመደለል የተደረጉ እንጂ በርግጥ ግለሰቦቹ ከራሳቸው አልፈው የጉራጌ ህዝብን የብሄር ብሄረሰሰብ ዘለቄታዊ ጥቅም የማስከበር አቅምም ችሎታም የላቸውም። ምናልባትም ፒፒ(ደኢህዴን) እነዚህን ግለሰቦች ወደፊት በማምጣት ስልጣን ላይ ያስቀመጠው የጉራጌ ህዝብን የብሄር ብሄረሰሰብ ዘለቄታዊ ጥቅም ለማስከበር አልሞ ሳይሆን ከጉራጌ ዞን ውጭ የሚኖሩ የጉራጌ ተወላጆችን ለማማለል እና በተለይ በከተሞች አካባቢ የሚኖረውን የጉራጌ ህዝብ ድምጽ ለማግኘት አስቦ ነው። የጉራጌ ህዝብ እነዚህን ከፊት የሚታዩ ጉራጌዎችን ተከትሎ ለደኢህዴን ፒፒ ድምጽ መስጠት የለበትም። ምክኛቱም እነዚህ ግለሰቦች በሁለት መስመር ደብዳቤ እንደተሾሙት ሁሉ በሁለት መስመር ደብዳቤ ሊነሱ ይችላሉ። የጉራጌ ህዝብ የብሄር ብሄረሰሰብ ዘለቄታዊ ጥቅም ደግሞ ከእነዚህም ሆነ ከሌሎች ግለሰቦች በላይ ነው።
ፒፒ (ደኢህዴን)ን በተመለከተ ሌላኛው ማሰተዋል የሚገባው ነገር ደግሞ የጠቅላይ ሚንስቴር አብይ ፒፒ እንደውም አንዳንድ ጸረ ጉራጌ አቋም ያለው የሚመስል መሆኑ ነው። በተለያዩ ወቅቶች ጉራጌን አስመልክቶ የተሰጡ አስተያየቶችን እንደማሳያ ከወሰድን ፒፒ ከጉራጌ ህዝብ የብሄር ብሄረሰሰብ ዘለቄታዊ ጥቅም በተጻራሪው እንደቆመ ማየት ይቻላል። ለምሳሌ ጠቅላይ ሚንስቴር አብይ በቅርቡ ከሰይፉ ፋንታሁን ኢቤስ ጣቢያ ላይ ቀርበው “ጉራጌ፣ ስልጤ፣ወለኔ” በሚል ያደረጉትን የጉራጌ ህዝብን የሚከፋፍል አደገኛ ንግግር ማንሳት ይቻላል።
በሌላ በኩልም ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የሚኖረው ግማሽ የሚሆነው የጉራጌ ህዝብን የብሄር ብሄረሰሰብ ጥቅም የማያስከብር የፌደራሊዝም ስርዐት ላይ አልደራረድርም ብሎ ፌደራሊዝሙ አሁን ባለበት ቅርጽ እና ይዘት ለማስቀጠል ቁርጥ ያለ አቋም የያዘው ፒፒ (ደኢህዴን) በምን አይነት ሁኔታ አሁን እየተተገበረ ያለው ፌደራሊዝም ለጉራጌ እንደሚጠቅም ማስረዳት አይችልም። የጉራጌ ህዝብ “መጤ፣ ሰፋሪ፣ ግልገል ነፍጠኛ፣ ወራሪ” እየተባለ ጥሮ ግሮ ያፈራው ሁሉ በእሳት ሲጋይ፣በአደባባይ ሲዘረፍ፣ ሲፈናቀል እና “ዘላለማዊ እርምጃ እንወስድባችኋለን” የሚል ይፋዊ የዘር ማጥፋት ጭፍጭፋ አዋጅ ታውጆበት በአደባባይ ራቁቱን ተዘቅዝቆ ሲሰቀል በዚሁ በፌደራሊዝም ምክኛት ሆኖ ሳለ፣ፒፒ ደኢህዴን ይህንኑ ፌደራሊዝም አልደራደርበትም ብሎ አሁን ባለበት ይዘትና ቅርጽ እቀጥልበታለሁ የሚል አቋም መያዙ ከጉራጌ የብሄር ብሄረሰሰብ ጥቅም በተቃራኒው እንደቆመ ማሳያ ነው።
አሁን እየተተገበረ ያለው ፌደራሊዝም የሚጠቅመውም እንደ ኦሮሞ እና ትግሬ ያሉ “እንገነጠላለን” እያሉ ጥቅማቸውን ለማስከበር የሚደራደሩ ብሄሮችን እንጂ አንገነጠልም ኢትዮጵያ ትሻለናለች የሚሉ እንደጉራጌ ያሉ አነስተኛ ብሄር ብሄረሰቦችን አይደለም። በመሆኑም ፒፒ ደኢህዴን አሁን ያለውን ፌደራሊዝም ባለበት በማስቀጠል፣ ለጉራጌም ሆነ በደቡብ ኢትዮጵያ ለሚኖሩ ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ምንም አይነት የመደራደሪያ አቅም የማይሰጥ እና የጉራጌንም ሆነ የሌሎች በደቡብ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦችን ጥቅም ለተረኛ ገዢ (የኦሮሞ) ቡድን አሳልፎ የሚሰጥ ነው።
ፒፒ (ደኢህዴን) አሁን ባለው የፌደራሊዝም ስራት አወቃቀር ውስጥም ሆኖ ቢሆን ከዞኑ ውጭ ቀርቶ በዞኑ ውስጥ የሚኖሩ ጉራጌዎችን የብሄር ብሄረሰሰብ ዘለቄታዊ ጥቅም ለማስከበር እንደማይችል ለማየት ደግሞ በቅርቡ “በጉራጌ ለ158 አመት ተቋርጦ የነበረው የኦሮሞ ገዳ ስርዐት በድጋሚ ተመሰረተ” ሲባልና ግልጽ የሆነ የባህል እና የማንነት ወረራ ሲፈጸም ፒፒ(ደኢህዴን) ትንፍሽ እንኳን ማለት አለመቻሉ ለአቅመቢስነቱና አሁን ባለው የፌደራሊዝም ስርአት ውስጥም ሆኖ ቢሆን የጉራጌን የብሄር ብሄረሰሰብ ጥቅም ሊያስከብር አለመቻሉን ያሳያል።
የሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄን (አዋሳን ማእከል ያደረገ የኦሮሞ የብሄር ብሄረሰሰብ ጥቅምን ለማስከበር በማለም) በኦሮሞ ፖለቲከኞች ትእዛዝ እና ውሳኔ ያስፈጸመው ፒፒ (ደኢህዴን) የጉራጌ ክልልነት ጥያቄ ላይ ሲሆን ወገቤን ያዙኝ ማለቱም ደኢህዴን ለጉራጌ ህዝብ የብሄር ብሄረሰሰብ ጥቅም መከበር ሙት ፓርቲ መሆኑን ያሳያል። ወልቂጤ ላይ “ጉራጌ ወደ አገርህ ግባ” እየተባለ ሲፎከርበትም የፒፒ ደኢህዴን ምላሽ እንደወትሮው ሁሉ ዝምታ ነበር። ይህ በሆነበት ሁኔታ የጉራጌ ህዝብ ለፒፒ (ደኢህዴን) ድምጹን የሚሰጥበት አሳማኝ ምክኛት የለም።
ፒፒ ደኢህዴን የጉራጌ ህዝብን የብሄር ብሄረሰሰብ ዘለቄታዊ ጥቅም አስከብራለሁ ካለ እና የጉራጌ ህዝብ ድምጽን ማግኘት ከፈለገ አሁን ያለውን የፌደራል ስርዐት መቀየር እና ህገመንግስታዊ ማሻሻያዎች ማቅረብ መቻል አለበት። ከነዚህም ማሻሻያዎች ውስጥ ዋነኛ ሊሆን የሚገባው ደግሞ ህገመንግስቱ ለኦሮሞ እና ለትግሬ የሰጠውን የብሄር ብሄረሰቦችን ጥቅም ማስከበሪያ መሳሪያ (እስከመገንጠል የሚለውን አንቀጽ 39) ያህል ተመጣጣኝ የሆነ እንደጉራጌ ላሉ አናሳ ብሄር ብሄረሰቦች ጥቅም ማስከበሪያ የሚሆን መሳሪያ እንዲሰጥ መጠየቅ አለበት።
ኦሮሞ እና ትግሬ “እንገነጠላለን” እያሉ ኢትዮጵያን እንደ ማስያዣ ተጠቅመው መብታቸውን እና ጥቅማቸውን ያስከብራሉ። እንደጉራጌ ያሉ አናሳ ብሄር ብሄረሰቦች ግን ዘላቂ መብትና ጥቅማችን የሚከበረው በኢትዮጵያ አንድነት ስር ስለሆነ ያንን የሚያረጋግጥልን መደራደሪያ (ልክ ኦሮሞ እና ትግሬ መብታቸውን ለማስከበር አንቀጽ 39 እንዳላቸው) ያስፈልገናል የሚሉበት ምንም የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦችን መብት ማስከበሪያ አማራጭ የላቸውም። ፒፒ ደኢህዴን የጉራጌ ህዝብ ድምጽን ከፈለገ ይሄንን እንደ አጀንዳ ይዞ ህገመንግስታዊ እና የፌደራል ስርዐቱ የሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦች መብት በእኩልነት በሚያስከብር መልኩ ማሻሻል አለበት። ያንን ማድረግ ካልቻለ የጉራጌ ህዝብ ፒፒ ደኢህዴንን ለምን ብሎ ይመርጠዋል? በሁለት መስመር ደብዳቤ የተሾሙት እነ አቶ እርስቱ ሙፋሪሃት ካሚል እና አምባሳደር ፍጹም በሁለት መስመር ደብዳቤ ሊነሱ ይችላሉ። የጉራጌ ህዝብ ዘለቄታዊ ጥቅም ከግለሰቦች በላይ ነው የሚባለው ለዚህ ነው።
2. የኦሮሞ ፓርቲዎች
ሌላው ለጉራጌ ህዝብ የሚቀርቡት አማራጮች የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው። በኦሮሞ ክልል የሚኖረው የጉራጌ ህዝብ ቁጥር ቀላል የማይባል ከመሆኑ አንጻር የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎችን እንደአማራጭ ማየት ይቻል ይሆናል። የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ በዋናነት ማእከል አድርገው የሚንቀሳቀሱት የኦሮሞ ህዝብን የብሄር ብሄረሰሰብ ዘለቄታዊ ጥቅም ከመሆኑ አንጻር ለጉራጌ ህዝብ ጥቅም ፋይዳቸው ምን ሊሆን እንደሚችል በውል አይታወቅም። የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ለጉራጌ ህዝብ ያላቸው አመለካከትም በጣም የተለያየ ነው። የኦሮሞ ፓርቲዎች በጉራጌ ህዝብ ላይ ያላቸው አቋም “ጉራጌ ግልገል ነፍጠኛ ስለሆነ በሜንጫ አንገቱን እየቆረጣችሁ ወደመጣበት መልሱት” ከሚሉት አንስቶ “አይ ጉራጌ ምንም እንኳን ግልገል ነፍጠኛ ቢሆንም መጤነቱን እና ሰፋሪነቱን አምኖ ተቀብሎ አንገቱን ደፍቶ እና ኦሮምኛ እየተናገረ ስራውን ከሰራ በሰላም ይኑር” እስከሚሉት ይደርሳል።
በኦሮሞ ክልል የሚኖሩት ጉራጌዎች በአብዛኛው በከተሞች አካባቢ የሚኖሩ ከመሆኑ አንጻር ለዘመናት “የኦሮሞ ህዝብ ፊንፊኔን ጨምሮ ከከተማ ህይወት እና ጥቅም ተገለሃል። ለዚህም ተጠያቂዎቹ አማራ እና ጉራጌ ናቸው።” እያሉ ደጋፊዎቻችውን ሲያሰባብሱ የነበሩ የኦሮሞ ፖለቲካ ሃይሎች ልክ እንደወያኔው ዘመን ሁሉ ጉራጌ ቀጥተኛ የጥቃት ኢላማቸው ነው። ለዚህም እንደማሳያ ደግሞ በጉራጌ ህዝብ ላይ “ዘላለማዊ እርምጃ ውሰዱ” የሚል የዘር ማጥፋት አዋጅ በግልጽ ያወጁ መኖራቸው እና በተለያዩ ከተሞች (ናዝሬት፣ ደብረዘይት፣አለማያ፣ሃረር፣ድሬዳዋ፣ ጅማ፤ሻሸመኔ እና ወሊሶ ጨምሮ የተለያዩ ቦታዎች) በተደጋጋሚ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን፣ የንብረት ቃጠሎ እና መፈናቀሎችን ማየት ይቻላል።
ይህ በሆነበት ሁኔታ ከጉራጌ ዞን ውጭ (በተለይ በኦሮሞ ክልል) የሚኖረው የጉራጌ ህዝብ ለኦሮሞ ፓርቲዎች ድምጹን የሚሰጥበት ምን ምክኛት ይኖረዋል? የኦሮሞ ፓርቲዎችስ “ዘላለማዊ እርምጃ እንወስድባችኋለን” ከሚል ይፋዊ የዘር ማጥፋት እወጃ እና “ሰጥ ለጥ ብላችሁ ተገዙ እና ኑሩ” ከሚል የአምባገነንነት ፖሊሲ ውጭ ለጉራጌ ህዝብ ምን አይነት አማራጭ መስመር ይዘው ቀርበዋል? የጉራጌ ህዝብስ በምን ሂሳብ ድምጹን ሊሰጣቸው ይችላል? በኦሮሞ ክልል ያሉ ጉራጌዎች በአካባቢያቸው እንደሁለተኛ ዜጎች ተቆጥረው ምንም የፖለቲካ ተሳትፎ የላቸውም። ተሳትፎ አላቸው ከተባለም የኦሮሞ ፖለቲከኞችን በመምረጥ እንጂ በመመረጥ አይደለም። ይህ በሆነበት ሁኔታ የጉራጌ ህዝብ ድምጹን ለኦሮሞ ፓርቲዎች የሚሰጥበት ምክኛት ምንድነው?
የኦሮሞ ፓርቲዎች የጉራጌ ህዝብን ድምጽ ከፈለጉ አሁን ያለው የፌደራል ስርዐት በምን አይነት መልኩ እስከታች የቀበሌ እና ወረዳ እርከኖች ድረስ እንዲተገበር ይሰራሉ? ፌደረሊዝም ማለት ራስን በራስ ማስተዳደር ማለት ከሆነ ጅማ አጋሮ የሚኖሩ ጉራጌዎች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች የፈቅዳሉ ወይ? በፌደራል ስራቱ ራስን በራስ የማስተዳደር ያልተማከለ ስራት መሰረት ናዝሬት ወይንም ደብረዘይት የሚኖር ጉራጌ በምርጫ መወዳደር ይችላል ወይ? ሃረር ጅማ እና ድሬዳዋ የሚኖሩ ጉራጌዎች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ እና በህገመንግስቱ የተደነገገውን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እንዲጠቀሙበት ይፈቅዳሉ ወይ? ወይንስ እስካሁን እየተባለ እንዳለው “መሬቱ የኦሮሞ ስለሆነ ከኦሮሞ ውጭ ማንም አይመለከተውም።” የሚል ፖሊሲ ነው የሚከተሉት? ይህ በሆነበት ሁኔታ በኦሮሞ ክልል የሚኖር የጉራጌ ህዝብ በምን መስፈርት ለኦሮሞ ፓርቲዎች ድምጹን ይሰጣል?
3. ኢዜማ
ሌላው ለጉራጌ ህዝብ የሚቀርበው አማራጭ ፓርቲ ኢዜማ ነው። አብዛኛው ሰው የጉራጌ ህዝብና ኢዜማን በተመለከተ ያለው ግንዛቤ በመሰረታዊነት የተሳሳተ ነው። “ኢዜማ የጉራጌ ፓርቲ ነው” ከሚሉት አንስቶ “የፓርቲው መሪ ብርሃኑ ነጋ ጉራጌ ስለሆነ ኢዜማ የጉራጌ ህዝብን የብሄር ብሄረሰሰብ ዘለቄታዊ ጥቅም የሚያስከብር ምትክ የሌለው ፓርቲ ነው።” እስከሚሉት ይደርሳል። እንዲህ ያለው የአመለካከት ስህተት የሚመነጨው የጉራጌ ህዝብ ዘላቂ የብሄር ብሄረሰብ ጥቅም እና የኢዜማ ፓርቲ ፕሮግራም ምን እንደሆነ በውል ካለመረዳት ነው። በመጀመሪያ የጉራጌ ህዝብ ዘላቂ የብሄር ብሄረሰብ ጥቅም ከግለሰብም ሆነ ከፓርቲ በላይ ነው። “የኢዜማ መሪ ብርሃኑ ነጋ በመሆኑ ኢዜማ የጉራጌ ህዝብን የብሄር ብሄረሰሰብ ዘለቄታዊ ጥቅም ያስከብራል” የሚል ሰው “አቶ ርስቱ የደቡብ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ስለሆኑ ፒፒ (ደኢህዴን) የጉራጌ ህዝብን የብሄር ብሄረሰሰብ ዘለቄታዊ ጥቅም ያስከብራል” ከሚል በምንም አይለይም። የኢዜማን መስመር በውል ካለመረዳት የሚመጣ ስህተት ስለሆነም አብዛኛው ጉራጌ የኢዜማን መስመር ሳያውቅ ድምጹን ለኢዜማ በስህተት እንዲሰጥ እያደረገው ነው።
የኢዜማ መስመር ምንድነው ካልን ኢዜማ ይፋ ባደረገው ዶክመንቱ ላይ ሰፍሮ ይገኛል። እንደ ኢዜማ መስመር “ኢዜማ በዜግነት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካዊ ማንነትን የተቀበሉ አባላትን ያቀፈ የፖለቲካ ሰብስብ ይሆናል” ይላል። ይህ ማለት ኢዜማ አንድን ጉራጌ እንደ “ዜጋ” እንጂ እንደ ጉራጌ አያውቀውም ማለት ነው። እንዲህ ያለው መስመር “አማላይ” ቢሆንም በመሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ግን አይደለም። እርግጥ ነው አንድ ሰው መጀመሪያ ከምንም በላይ ሰው ነው። ያ ማለት ግን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሃገሮች ውስጥ ይሄ መስመር ይሰራል ማለት አይደለም። እንኳን በኢትዮጵያ ቀርቶ በበለጸጉት ሃገራትም “ዜጋ ማነው?” የሚለ ጥያቄ እስካሁን ድረስ በውል አልተመለሰም። ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ደግሞ ባለፉት 27 አመታት ሲተገበር የነበረው የመንግስት ፖሊሲ እና አሰራር መሬት ላይ ከፈጠረው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚላተም እና “የዜግነት ፖለቲካ” ሚባል ነገር ተግባራዊ ሊሆን የማይችል ነው።
ኢዜማ እከተለዋለሁ የሚለው “የዜግነት ፖለቲካ” መስመር ለጉራጌ ህዝብ ቅንጦት ነው። በጉራጌነቱ እየተለየ ሱቁ ለሚቃጠልበት፤”መጤ ሰፋሪ” እየተባለ ለሚጨፈጨፈው፤ እየተዘረፈ ለሚፈናቀለው ድሃ ጉራጌ “ዜግነት” ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግራ የሚያጋባ ነው። እንደሰው መቆጠር ያልቻለ ጉራጌ “ዜጋ ነህ” ሲባል ለድለላ እና ሽንገላ እንደሆነ ይገባዋል። ከዚህ በተጨማሪም የኢዜማ “ፖለቲካዊ ስትራቴጂ” መሰረት ያደረገው የ97ቱን ምርጫ ውጤት እና በጊዜው የነበረውን ነባራዊ ሁኔታ እንደ ምነሻ (ቤዝ ሪፈረንስ) በመውሰድ ነው። የኢዜማ ፖለቲካል ስትራቴጂስቶች ዋነኛ ስህተትም ሁል ጊዜ መነሻ የሚያደርጉት የ97ቱን ምርጫ መሆኑ ነው።
ከ97 ምርጫ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ለውጦች እና መሬት ላይ የሚታወቁ ነባራዊ ሁኔታዎች አሉ። ከ97 በኋላ ቢያንስ ቢያንስ 15 አመት አልፏል። ወያኔ ከ97 በኋላ የተከተላቸው ስትራቴጂዎችም በዚሁ 97 ምርጫ ውጤት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። በከተሞች ላይ የተፈጸመው የዲሞግራፊ ለውጥ፣ እና በኮንዶሚኒያም ግንባታ ስም ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በአዲስ አበባ እና በሌሎችም ከተሞች ዙሪያ ተወስደው የተጣሉ እነማን ናቸው ካልን በብዛት ጉራጌዎች እና ስልቴዎች ናቸው። ለዚህ ቀላል ማሳያ ደግሞ በቡራዩው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ እና በለገጣፎው የቤት ማፍረስ ፕሮጀክት የተጨፈጨፉት እና ቤታቸው የፈረሰባቸው በብዛት ጋሞዎች፣ጉራጌ እና ስልጤዎች ናቸው። አማራዎችም በብዛት አሉበት። ይህ የሆነበት ምክኛት ደግሞ ግልጽ ነው።
ከምርጫ 97 በሁዋላ ወያኔ የተከተለው ስትራቴጂ ጉራጌ የቅንጅት ደግፊ ነው በሚል ከመርካቶ፣ልደታ፣ኮልፌ እና የተለያዩ የአዲስ አበባ መሃል አካባቢዎች አፈናቅሎ ወደ አዲስ አበባ ጠረፍ እንዳሰፈራቸው እና በዚህም ምክንያት ከኦሮሞ አርሶ አደሮች ጋር ግጭት ውስጥ እንዲገቡ ስላደረገ ነው። ከዚህም ሌላ ባለፉት 15 አመታት የአዲስ አበባ እና የሌሎችም ከተሞች ዴሞግራፊ እና አሰፋፈር በስፋት ተቀይሯል። አሁን ባለው ሁኔታ ከተሞች ራሳቸው በብሄር አሰፋፈር የተዋቀሩ ሆነው በተቀረው ኢትዮጵያ የሚታየው ነባራዊ ሁኔታ ነጸብራቅ እንዲሆኑ ሆነዋል። ይህ በሆነበት ሁኔታ ኢዜማ ይዞ የመጣው “የዜግነት ፖለቲካ” መስመር በከተማ ለሚኖረው የጉራጌ ህዝብ የብሄር ብሄረሰሰብ ዘለቄታዊ ጥቅም መከበር የሚፈይደው ብዙም ነገር የለም።
ኢዜማ በጉራጌ ዞንም ሆነ ከጉራጌ ዞን ውጭ ለሚኖሩ ጉራጌዎች የብሄር ብሄረሰሰብ ዘለቄታዊ ጥቅምን እንዴት ያስከብራል የሚለው ጥያቄ መልስም በውል አይታወቅም። ለምሳሌ ኢዜማ በኦሮሞ ክልል ከተሞች የሚኖሩ ጉራጌዎችን የብሄር ብሄረሰሰብ ዘለቄታዊ ጥቅም እንዴት ማስከበር ይችላል? ኢዜማ እንኳን በኦሮሞ ክልል የሚኖሩ ጉራጌዎችን ጥቅም ማስከበር ቀርቶ ለራሱ እኳን ኦሮሚያ ውስጥ መቀሳቀስ ተከልክሎ አዲስ አበባ ላይ ተወስኖ ስብሠባ ሲያደርግ ነው የሚውለው። አማራ ክልል በጠመንጃ ተባሯል። ኦሮሞ ክልል ድርሽ እንዳይል ተብሏል። ኢዜማ አንድ ጊዜ ናዝሬት ሄዶ ነበር። ከዛ ውጭ ጅማ ሃረር ድሬዳዋ ሻሸመኔ እና ሌሎችም ቦታዎች ሲንቀሳቀስ አይታይም። ከምርጫ 97 በኋላ የተፈጠረው ሌላው መሬት ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ይሄ ነው።
ከዚህ ውጭ ኢዜማ የጉራጌ ህዝብም ሆነ ሌሎች አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ብሄር ብሄረሰቦች በፌዴራል ስራቱ ውስጥ የሚኖራቸውን ውክልና በምን መልኩ ለማረጋግጥ ይችላል? የሚለው ጥያቄን እንዴት እንደሚመልስ አይታወቅም። እንደ ኢዜማ ዶክመት ከሆነ በኢዜማ ፌዴራላዊ ስራት “ሕግ አውጪው አካል ሁለት ክፍሎች (የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት) የሚኖሩት ሲሆን ሁለቱም ሕግ የማውጣት ስልጣን ያላቸው እና በሕዝብ የተመረጡ ይሆናሉ፡፡ የፌዴራሽን ምክር ቤቱ በአስዳደር አካባቢዎች በእኩል የሚወከሉበት እና የአስተዳደር አካባቢዎች በሚኖራቸው ብሔረሰቦች ብዛት አነስተኛ ቁጥር ላላቸው ብሔረሰቦች ተጨማሪ ውክልና የሚሰጥ ሆኖ አስፈላጊው ድጋፍ እንዲያገኙ ህጎችን የማመንጨት፤ ሕጎችን የመገምገም፤ አፈፃፀማቸውን የመከታተል ሃላፊነት ይኖርበታል” ይላል። ይሄ ማለት ግን ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ህግ የማውጣት ስልጣን በሚኖረው የፌዴሬሽን ምክር ቤት እኩል ውክልና ይኖራቸዋል ማለት አይደለም። ፍትሃዊ ስራት እንዲኖር ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች እኩል የፌዴረሽን ምክርቤት ውክልና ነው የሚያስፈልጋቸው።
ለምሳሌ ኦሮሞ ብዙ ቁጥር ስላለው የተለየ ወይንም የተሻለ ብሄር ብሄርሰብ አይደለም። አማራም። ትግሬም እንደዛው። ሁላችንም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ጉራጌንም ሆነ ሌሎች አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ብሄር ቤረሰቦችን ጨምሮ በህገመንግስቱ እንደተደነገገው እኩል ነን። ኦሮሞ ቁጥሩ ብዙ ስለሆነ የበላይ ይሁን የሚል አካሄድ የጭቆና አካሄድ ስለሆነ ተቀባይነት የለውም። በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ውስጥ ኦሮሞ በቁጥሩ ልክ መቀመጫ ቢኖረው ተገቢ ነው። በፌዴረሽን ምክር ቤት ውስጥ ግን በምን ሂሳብ ኦሮሞ የበለጠ ድምጽ ይኖረዋል? ሁላችንም ብሄር ብሄረሰቦች እኩልነታችን የሚረጋገጠው በፌዴሬሽን ምክር ቤት መሆን አለበት። ሁላችንም ብሄር ብሄረሰቦች እኩል ቁጥር ያለው መቀመጫ እና ድምጽ በፌዴረሽን ምክርቤት ኖሮን የብሄር ብሄረሰሰብ ዘላቂ ጥቅማችንን ልናስክብር እና የተወካዮች ምክር ቤት የብሄር ብሄረሰሰብ መብታችንን የሚጋፋ ህግ ሲያወጣ ልንከላከል ይገባል።
ለምሳሌ ጉራጌ እንደ አንድ አናሳ ብሄር ብሄረሰብ ከኢትዮጵያ መገንጠል አያዋጣውም። ኦሮሞ መገንጠል ያዋጣኛል ሊል ይችላል።መብቱ ነው። ይህ ጥያቄ መፈታት ያለበት ግን በአንድ ብሄረሰሰብ አንድ ድምጽ ነው መሆን ያለበት። ኢዜማ እንዲህ ያለውን አማራጭ ለጉራጌ ህዝብ ይዞ ይቀርባል ወይ? አሁን ባለው ሁኔታ አይቀርብም። ኢዜማ “አነስተኛ ቁጥር ላላቸው ብሔረሰቦች በፌዴሬሽን ምክርቤት ተጨማሪ ውክልና የሚሰጥ ሆኖ አስፈላጊው ድጋፍ እንዲያገኙ ይደረጋል” ይላል እንጂ ሁሉም ብሄር ብሄርሰቦች በፊዴሬሽን ምክርቤት እኩል ድምጽ ይኖራቸዋል አይልም። ስለዚህ ኦሮሞ ብዙ ስለሆነ በፊደሬሽን ምክርቤት ብዙ ድምጽ ይኖረውና መገንጠል ከፈለገም የጉራጌን መብት ጥሶ እና ደፍጥጦ ይገነጠላል ማለት ነው። ይሄ ደግሞ በህገመንግስቱ የተደነገገዉን የጉራጌ ህዝብን ዘለቄታዊ የብሄር ብሄረሰብ ጠቅምም ሆነ እኩልነት አያረጋግጥም።
ኢኮኖሚን በተመለከተ “ኢዜማ ከዚህም በተጨማሪ ማህበራዊ ፍትህ በሀገሩ እንዲሰፍን፤ በራሳቸው ስንፍና ሳይሆን በገበያ ኢኮኖሚው ተገፍተው ለድህነት የተዳረጉ ዜጎችን ለመታደግ ከሀገሪቱ አቅም ጋር የተናበቡ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እርምጃዎችን ይወስዳል” ይላል። በመሰረቱ ኢዜማ በዋናነት ለከበርቴዎች የቆመ ፓርቲ ስለሆነ “ማህበራዊ ፍትህ” ብሎ ያስገባት ቅጥያ ለጉራጌ ህዝብ እንደ መደለያ ተደርጋ ልትወሰድ ትችላለች። በአነስተኛ ንግድ እና የቀን ስራ ለሚለፋው ድሃው የጉራጌ ህዝብ ኢዜማ የሚያቀርበው “የማህበራዊ ፍትህ” ፖሊሲ በርግጥ ለጉራጌ የሚፈይደው ብዙም ነገር የለም። “ከማህበራዊ ፍትህ” ይልቅ ለዝቅተኛ እና መካከለኛ ግብር ከፋዮች ምን ምን አይነት የግብር ቅነሳ ፖሊሲዎች አሉት የሚለው ነው ዋናው ጥያቄ። የኢዜማ ፖሊሲ ከበርቴ ተኮር በመሆኑ የግብርም ሆነ የኢኮኖሚክ ፖሊሲዎቹ ዋና ማጠንጠኛዎች፤ የገንዘብ ምንጮቹም ሆነ አባል ደጋፊዎቹ ከበርቴዎች ናቸው። ኢዜማ ለድሃው እና በአነስተኛና መካከለኛ ንግድ ስራ ለተሰማራው አብዛኛው የጉራጌ ህዝብ የሚያቀርበው አማራጭ የለም።
4. ባልደራስ
አዲስ የተቋቋመው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የሚከተላችውን መስመሮች እና ፖሊሲዎች ገና በዝርዝር ይፋ ስላልሆኑ ወደፊት የሚታይ ይሆናል። ነገር ግን አሁን ካሉት ፓርቲዎች በተለየ አዲስ አበባንም ሆነ የኢትዮጵያ አንድነትን በተመለከተ ቁርጥ ያለ አቋም ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ ያለ ፓርቲ ባልደራስ ነው። ባልደራስ አዲስ አበባን በተመለከተ የያዘው “አዲስ አበባ የሁላችንም ከተማ ነች። ማንም ‘ልዩ ጥቅም’ የለውም” የሚለው አቋሙ የጉራጌ ህዝብ ሙሉ በሙሉ የሚደግፈው አቋም ነው። “አዲስ አበባን ማዳን ኢትዮጵያን ማዳን ነው” የሚለው የባልደራስ መርህም የጉራጌ ህዝብን የሚያስማማ መርህ ነው። ባልደራስ እንደ አዲስ ፓርቲነቱ ይዞ የቀረባቸውን ሌሎች አማራጭ ሃሳቦች ለጉራጌ ህዝብ ቢያሳውቅ በአዲስ አበባ የጉራጌ ህዝብን ድምጽ ያገኛል። እስካሁን ባለው አካሄድ ግን ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች (ፒፒ ኢዜማ የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ወዘተ) በባልደራስ ላይ የሚያድርሱትን የተቀናጀ ጥቃት ላስተዋለ ምናልባትም ባልደራስ እየተከተለ ያለው መስመር ትክክለኛ መስመር ሳይሆን አይቀርም ብሎ ለመገመት ይችላል።

1 thought on “ለባልደራስ፣ለኢዜማ፣ ለኦሮሞ ፓርቲ፣ ወይንስ ለፒፒ(ደኢህዴን)? የጉራጌ ህዝብ በቀጣዩ ምርጫ ድምጹን ለማን ይስጥ?

 1. ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ! በምርጫ አስፈፃሚነት በንቃት በመሳተፍ የህጋዊ የስልጣን ባለቤትነትህን አረጋግጥ!

  JANUARY 24, 2020
  .

  ለመላው የአዲስ አበባ ነዋሪ፣\

  በምርጫ አስፈፃሚነት በንቃት በመሳተፍ የህጋዊ የስልጣን ባለቤትነትህን አረጋግጥ!

  የኢትዬጲያ ምርጫ ቦርድ በቀጣዩ ነሐሴ 10 ቀን 2012 ዓ•ም• አገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫ እንደሚካሄድ በማሳወቅ ዝርዝር መርሃ ግብሩን ይፋ ማድረጉ የሚታወቅ ነው። በዝርዝር ፕሮግራሙ ለመረዳት እንደሚቻለው የፊታችን ጥር 16 ቀን 2012ዓ•ም• በሁሉም ምርጫ ክልሎች የምርጫ አስፈፃሚ ምርጫ እንደሚካሄድ ለመረዳት ተችሏል።

  ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በምርጫ ሂደት ውስጥ የምርጫ አስፈፃሚ አስፈላጊነት የሚመነጨው በምርጫው ህግ መሰረት ያለ አድልኦ መከናወኑን ወይም አለመከናወኑን ለማረጋገጥ የሕዝብ ዓይንን ጆሮ ለመሆን በገለልተኛ አካላት እንዲመራ ማድረግ ለእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አንዱ ምሰሶ እንደሆነ ይገነዘባል። ከዚህ አንፃር ፓርቲያችን የምርጫ አስፈፃሚን የምንመለከተው አንድን እግር ኳስ እንደሚመሩ ዳኞች አካል አድርገን ነው። የእግር ኳስ ዳኞች ገለልተኛ መሆን እንደሚጠቅባቸው ሁሉ የምርጫ አስፈፃሚዎችም ከዳኞቹ በላቀ ሁኔታ ገለልተኛ መሆን ይጠበቅባቸዋል።በመሆኑም የምርጫ አስፈፃሚ የዲሞክራሲያዊ ውድድሩ ሂደት በተገቢው መንገድ መከናወኑና ውጤቱም የእውነተኛ የሕዝብ ፍላጐት የተገለፀበት መሆኑን የሚያረጋግጥና የሚቆጣጠር አካል መኖር የግድ መሆኑን ፓርቲያችን ይገነዘባል።

  Ethiopia Plants Four BILLION Trees!
  x
  ሆኖም ግን ኢህአዴግ ባደረጋቸው ያለፋት አምስት የውሸትና የማስመሰል የምርጫ ዘመናት ለማጭበርበር ከፍተኛ ድርሻውን ከሚወስዱት አካላት አንዱ የምርጫ አስፈፃሚዎች ነበሩ። የምርጫ አስፈፃሚዎች ለኢህአዴግ ወገንተኛ የሆኑ የገዥው ፓርቲ አባላት፣ የፓርቲው ወጣትና ሴት ሊጐች እንዲሁም የፎረም አባላት የተካተቱበት በመሆኑ በሕዝቡ አመኔታና ተቀባይነት ያጡ ነበር። በዚህም ምክንያት ያለፉት ዘመናት ምርጫዎች ኢህአዴግን በይስሙላ ምርጫ ለማንገስ ባደረጉት ርብርብ ህዝቡ በነፃነት እና ዲሞክራሲያዊ መንገድ የሚመርጠው ተወካይ እንዳይኖር አድርገዋል። በተለይም በምርጫው ቀን የምርጫ አስፈፃሚዎች በየጣቢያዎቹ ሕዝቡ ተገቢዎቹን የድምፅ አሰጣጥ ሂደቶች ፍፁም አድሎአዊ በሆነ መንገድ በመፈፀም ኢህአዴግን እስከ መቶ ፐርሰንት የማንገስ ስራ በመስራት በታሪካቸው ጥቁር አሻራ አሳርፈዋል።

  ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ እንዲህ አይነት ሕገ ወጥና ፀረ-ዲሞክራሲያዊ ተግባራት መድገም እንደሌለባቸው በጽናት ያምናል። ይህም ያለ አዲስ አበባ ህዝብ የነቃ ተሳትፎ ሊሳካ እንደማይችል ይገነዘባል። በአዲስ አበባ ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ለእውነት እና ለእውነት ብቻ የሚቆሙ እንዲሁም የምርጫን ፋይዳ በቅጡ የተረዱ የምርጫ አስፈፃሚዎች መሳተፍ የግድ ይላል። በቀጣይ የሚካሄደው ምርጫ በአዲስ አበባ ብሎም በአገራችንና በሕዝባችን ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ያለውን ፋይዳ የሚገነዘቡ አስፈፃሚዎች መሳተፍ ይኖርባቸዋል።

  .
  ስለሆነም የፊታችን ጥር 16/05/2012 ዓም በምርጫ ቦርድ መሪነት በሁሉም የምርጫ ክልሎች የሚደረግ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ የአዲስ አበባ ነዋሪ በነቂስ ውጥቶ እንዲሳተፍ ፓርቲያችን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ጥሪውን ያቀርባል።

  ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ!

  አዲስ አበባ

  ድል ለእውነተኛ ዲሞክራሲ!

  ይህን መረጃ በማሰራጨት አጋርነትዎን ያረጋግጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.