ቦርኮሃራም በኢትዮጵያ  (አሁንገና ዓለማየሁ)

አባቷን አግዛ እናቷንም ረድታ
እንስራዋን አዝላ ከወንዝ ውሃ ቀድታ
ቁርስም አቀራርባ ደብተሯን አንስታ

አድምጣለችና ጥበብ ስትጣራ
ወንዝና ዐቀበት በሩጫ ተሻግራ

በቅርከሃ አዳራሽ አፈር ላይ ቁጭ ብላ
የሰጧትን ትምህርት ስትቀበል ውላ

የገጠሯ ወጣት ቤቷም ተመልሳ
የቀራትን ሥራ እንዳቅሟ ጨራርሳ
ትምህርቷን አጥንታ በጭስ ተጨናብሳ
በብርቱ ጥረቷ አልፋ ኮሌጅ ደርሳ

መንግስት ቢመድባት እንደ እህቶቿ
መሳፈሪያ ወስዳ ከቤተሰቦቿ

ድረሺ እንዳሏት ተቻኩላ በቶሎ
ሀገሬ ነው ብላ ሄደች ደምቢ ዶሎ።

ዘንድሮ ቀውጢ ነው ተረብሿል አገር
ይቅርብሽ ይሆን ወይ እንዴት ነው ይህ ነገር?
ያሏት መካሪዎች ባይጠፉም ከሰፈር
ድካሜን በሙሉ እንዴት ይብላው አፈር?

ትምህርቴንስ ትቼ አልሆንም ቦዘኔ
እድሉ ቢያመልጠኝ
እድሜ ልክ መጸጸት አይቀርም ማዘኔ
አለችና ጀግኒት በኮስታራ ወኔ

ከጓደኞቿ ጋር አውቶቢስ ተሳፍራ
ወለጋ ዘለቀች ዓባይን ተሻግራ።

ደምቢዶሎ ኮሌጅ ሲገቡ በሩጫ
በጠመኔው ቦታ መምህር ይዟል ሜንጫ

ደንግጠው ሲወጡ ያንን ግቢ ለቀው
በቦርኮ ሃራሞች ተወሰዱ ታንቀው።
እናት እዬዬ አለች አባትም ጨነቀው

ኢቲቪና ፋና እንትናና ዋልታ
ሴት ልጆች ታግተው መረጡ ዝምታ።
ሰው የሚያፋጀውም ወሬ እያጋነነ

እየቀባጠረ ያልሆነ ያልሆነ
የውጪውም ሚዲያ ዝም እንደታፈነ።

እናቶች በልጅ ጭንቅ ዳግም እያማጡ
ይታያሉ ዐቢይ ዛፍ ውሃ ሲያጠጡ።

“ለቅሶም እንደሆነ አለቀስኩ አምርሬ
የሆነውን ነገር ቁርጡን ተነግሬ
ሞታም እንደሆነ ልረፈው ቀብሬ
አገርም ሞታለች እንኳን አንዷ ፍሬ”

እያለ ነው አባት!

“ዘጠኝ ወር አርግዤ አምጬ ወልጄ
ትማርልኝ ብዬ ወለጋ ሰድጄ

መንግስት እያለ’ማ
ታፍና፣ ተደፍራ፣ ተዋርዳና ታርዳ አትሞትም ልጄ”

እያለች ነው እናት!

ኧረ አንድ በሏቸው! ይህ ከፋት አይሠራም
ውድቀት ያስከትላል። ሃራም! ቦርኮ ሃራም!

ይህ ግጥም መታሰቢያነቱ ሀገሬ ናት ብላችሁ በዚህ ቀውጢ ዘመን በታላቅ ጀግንነት ወደ ተመደባችሁበት የተለያየ ዩኒቨርሲቲ ሄዳችሁ ትምህርታችሁን በመከታተል ላይ ላላችሁ የኢትዮጵያ ወጣቶች ይሁን።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.