«መጤ ቄሶችን አባሯቸው» የተባለበት ሰላሌ ወይም የጥንቱ ሰላላ የማን ርስት ነው? – አቻምየለህ ታምሩ

የዶክተር መረራ ጉዲና ድርጅት ኦፌኮ ባለፈው ሳምንት በሰላሌ ያካሄደው ዘመቻ [ቅስቀሳ አላልሁም] «የኦሮምያ ቤተ ክህነት» የሚባለው ቡድን የፖለቲካ ድርጅት እንጂ የሃይማኖት ባለጉዳይ አለመሆኑን በግላጭ አሳውቆናል። በመሆኑም «የኦሮምያ ቤተ ክህነት» የሚባለው የፖለቲካ ቡድን የቄሮው ጠቅላይ ኢታማጆር፣ የ«ኦሮሚያ ክልል» ሱፕሪም መሪ፣ የሕወሓት እጮኛ ፤ የኦሕዴድ ባል፤ የኦነግ የመንፈስ ልጅ፤ የመደመሩን ሕግ ሰርቶ ሥልጣኑ ከሕግ በላይ በመሆኑ የማይጠየቀው፤ ሁሉን ፈቃጅ፣ ሁሉን ከልካይ፤ ሥይጣኑ የማይገሰጽ፤ የነቄስ በላይ የመንፈስ አባት፤ የጠቅላይ ሚኒስቴሩ የበላይ አዛዥና ርኡሰ ርኡሳን አያቶላህ ጃዋር መሐመድ የሃይማኖት ክንፍ መሆኑ በአደባባይ አይተነዋል። ጃዋር መሐመድ ፖለቲካ የጀመረው «Ethiopia out of Oromia» በማለት ነበር። የመንፈስ ልጁ የሆነው «የኦሮምያ ቤተ ክህነት» የሚባለው ቡድን የፖለቲካ ድርጅት አደራጅ ሰውዬም ሰላሌ ላይ ፖለቲካውን የጀመረው ቄሮዎች መጤ ቄሶችን ከሰላሌ እንዲያባርሩና ደብረ ሊባኖስን እንዲወርሱ በመጠየቅ ነበር።

ዶክተር መረራ ጉዲናም ሰላሌ ባደረገው ዲስኩር የምኒልክን ቤተ መንግሥት ተቆጣጥሮ የጄኔራል ታደሰ ብሩን ሐውልት እንደሚያቆምበት ነግሮናል። ይገርማል! እንደኳን የዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ግቢ ኢትዮጵያ የጋራችን ካልሆነች በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ኢንቺ መሬት የሌለው ቢኖር ኦሮሞ ብቻ ነው። ኦሮሞ እንደ ነገር በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለመሬት የሚሆነው ኢትዮጵያ የጋራችን ከሆነች ብቻ ነው። በየርስትህ፣ በያባትህ ግባ ከተባለ ግን ኦሮሞ በዛሬዋ ኢትዮጵያ አንድ ኢንች ርስት የለውም።

በዳንኤል ክብረት የፈጠራ ታሪክ የተመሰረተው «የኦሮምያ ቤተ ክህነት» የሚባለው የፖለቲካ ድርጅት ተወካይ ሰላሌ ሄዶ «መጤ ቄሶችን አባሯቸው» ያለው ካባቶቻቸው ርስት ነው። ሰላሌ ወይም ሰላላ የአማራ ጥንታዊ ርስት ነው። መራራ ጉዲና ስለ ጀኔራል ታደሰ ብሩ ዛሬ ላይ የሚያራምደው አቋም ያስቀኛል። ጀኔራል ታደሰ ብሩ አባታቸው አቶ ብሩ ኬኔ ናቸው። አቶ ብሩ ኬኔ የከረዩ ኦሮሞ ሲሆኑ የትውልድ ሀረጋቸው እንደሚከተለው ነው፤ ብሩ ኬኔ ጅሩ ኡመቶ ጉታ ሞገር ደራ አቦቴ ሲንቼል ሲቡ ኢሌ አባዶ ሊበን ከረዩ ኦቦ። በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አዋሽን ተሻግሮ ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን ወደ ነበሩበት ወደ አማራ ምድር ወደ ግራርያ አውራጃ ሰላላ ወረዳ የመጣው የመጀመሪያው ትውልዳቸው አባዶ ሊበን ነው።

የጄኔራል ታደሰ አባት አቶ ብሩ ኬኔ ጸረ ፋሽስት አርበኛ የነበሩ ሲሆኑ ሕይዎታቸው ያለፈው ከራስ ካሳ ጋር በመዝመት ለአገራቸው ተሰልፈው ሲዋጉ በፋሽስት ጥሊያን የመርዝ ጭስ ነው። አባቱ ሲሞቱ የ13 ዓመት ልጅ የነበረው ታደሰ ብሩ የአባቱን ፈለግ በመከተል ፋሽስት ጥሊያንን ለመፋለም ዱር ቤቴ ባለበት ወቅት በፋሽስት ጥሊያን ተማርኮ ወደ ሞቃድሾ እስር ቤት ውስጥ ተሰቃይቷል።

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት እንደገና ሲቋቋምና ፋሽስት ጥሊያን ያሰራቸው የኢትዮጵያ አርበኞች ከሶማሊያ እስር ቤት ሲለቀቁ ወጣቱ ታደሰ ብሩም የጦር ሠራዊት አባል በመሆን አገሩን ማገልገል ጀምሯል። የኢትዮጵያ ፖሊስ እንደ ተቋም ሲመሰረት ጀኔራል ጽጌ ዲቡ ከሶስተኛው ክፍለ ጦር ወደ አዲስ አበባ ይዘዋቸው ከመጡት ወጣት የሠራዊቱ አባላት መካከል አንዱ ታደሰ ብሩ ነበሩ። በጊዜ ሂደት በሹመት ላይ ሾመት እየደረቡ በማደግ የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ አዛዥ ሆነው በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ተሹመዋል።

ቀደም ብዬ እንዳወሳሁት ጀኔራል ታደሰ ብሩ የተወለዱበት አገር ሰላሌ ኦሮሞ ወደ ቦታው ከመስፋፋቱ በፊት የአማራ አገር ነበር። በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የቱለማ የኦሮሞ ጎሳዎች ከብቶቻቸው እየነዱ ሸዋን ወረው ባለ ርስቱን ገበሮ፣ ጠለታና ገርባ በማድረግ የቦታውን ስያሜ ሰላሌ ብለው corrupt ከማድረጋቸው በፊት የቦታው ትክክለኛ መጠሪያ ሰላላ የሚል የአማርኛ ስም ነበር። ሰላላ አማርኛ ነው። ሰላላ የሚለው የአካባቢ መጠሪያ ኦሮሞ ወደ ቦታው ከመስፋፋቱ በፊት በተጻፈው የዐፄ ሱስንዮስ ዜና መዋዕል ውስጥ ተጠቅሶ ይገኛል። የዐፄ ሱንዮስ ጸሐፌ ትዕዛዝ አዛዥ ተክለ ሥላሴ ዐፄ ሱስንዮስ በአያታቸው ምድር በሸዋ ያሳለፉትን የወጣትነት ዘመን በገለጹበት የዜና መዋዕሉ ክፍል እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፤

“ወበውእቱ ምድረ ረከቦ ዓብይ ምንዳቤ ረኅብ እስከ በልኡ ሠራዊቱ አሣእነ እግሪሆሙ። እስመ ተኃጥ አእክል ለሲሳይ በእንተ ዘኮነት ይእቲ ምድር በድወ ወዓጸ። ወእምዝ ተንሥአ እምይእቲ ምድር ወአመልአ ፍኖቶ መንገለ ግንድ በረት ። ወእምዘ የሐውር በጽሐ ምድረ ሰላላ።” [ ምንጭ፡ Pereira, F. M. E. (1892). Chronica de Susenyos, Rei de Ethiopia: Texto ethiopico: destinado á X sessão do congresso internacional dos Orientalistas. Imprensa nacional; Page 22 ]

ትርጉም፤

ያንጊዜም ሐንገታሞ በሚባል ስፍራ ተቀመጠ። በዚያም ስፍራ ታላቅ የርሐብ ችግር ገጠመው፤ ተከታዮቹ የእግራቸውን ጫማ እስኪበሉ ድረስ። ለምግብ የሚሆን እህል ታጥቷልና፤ቦታዋ ምድረ በዳና ደረቅ ስለሆነች። ከዚህ በኋላ፣ ከዚያች ቦታ ተነስቶ ወደ ግንደ በረት ጉዞ አደረገ። ሲሄድም ሰላላ ደረሰ።

ሐንገታሞ ደብረ ብርሀን አካባቢ የሚገኝ አገር ነው። ግንደ በረትም አሁንም ድረስ ሸዋ ውስጥ የሚገኝ ቦታ ነው። ዜና መዋዕሉ እንደሚነግረን ዐፄ ሱስንዮስ ከደብረ ብርሀን አካባቢ ተነስቶ ወደ ግንደ በረት ለመሄድ ሰላላ አድሯል። ይህ ሁሉ ታሪክ የተፈጸመው ኦሮሞ ወደ ቦታው ከመምጣቱ ከአንድ ክፍለ ዘመን በፊት ነው።

ሰላላ በአማርኛ አነጋገር ውስጥ በብዛት ጥቅም ላይ ይውላል። ጎጃም ስናድግ ልጆች ሳለን የዘመን መለዋጫ በዓልን ሲከበር በወጣቶች በሚዜሙ ጥዑመ ዜማዎች ውስጥ ሰላላ ጥቅም ላይ ይውል ነበር። በበዓሉ እለት ከሚዜሙት ጥዑመ ዜማዎች መካከል ሴት ቆነጃጅት እንዲህ እያሉ ያዜሙ ነበር፤

የቅዱስ ዮሐንስ ያልዘፈነች ቆንጆ፣
ቆማ ትቀራለች እንደ ሰፈር ጎጆ፤
እቴ አደይ አበባ ነሽ፣
ዉብ ነሽ ዉብ ነሽ፤
ልጃገረዶች ይህንን ዜማ እንግጫ እየነቀሉ ሲያሰሙ፤ ጎረምሶች ወንዶች ደግሞ የሚከተለውን እያዜሙ ወደ ልጃገረዶች ይሄዳሉ፤
እንግጫችን ደነፋ፣
ጋሻዉን ደፋ፤
እንግጫዬ ነሽ ወይ፤
ኮረዶች ይህንን ሲሰሙ እንዲህ ብለው ይመልሳሉ፤
እሰይ እሰይ፣
የቅዱስ ዮሐንስ የመስቀል የመስቀል፤
የላክልኝ ድሪ ሰላላ መላላ፣
መልሰህ ዉሰደዉ ጉዳይም አይሞላ፤

በዚህ ጊዜ ጎረምሳው ለወደዳት ልጃገረድ ማተብ ያስርላታል። ጨዋታው እንዲህ እንዲያ እያለ ይደራ ነበር. . .

ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ አዛዥ፣ በ1953 ዓ.ም. እነ ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ላይ የሞከሩትን ስዒረ መንግሥት በቀዳሚነት ያከሸፉትንና ደርግ ከጭሰኞቻቸው ጋር በግፍ ለረሸናቸው ለጄኔራል ታደሰ ብሩ ባለፈው አመት መጋቢት ወር ላይ ሐውልት ያቆመው በዚህ ሰላላ/ሰላሌ ምድር የኦሮሞ የገዢ መደብ አካባቢውን ከመውረሩ በፊት አማራ ይኖርበት በነበረው ርስት ላይ ነው። የአገሩ ስም ራሱ የአማርኛ ስም ያለው የአማራ ምድር ነበር። ሰላሌ ወደሚል የኦሮምኛ ድምጸት ያለው ስያሜ የተለወጠው ከኦሮሞ መስፋፋት በኋላ ነው።

ዐቢይ አሕመድ ሰላሌ ያቆመው የጄኔራል ታደሰ ብሩ ሐውልት የጄኔራሉን የዘመን እውነት የሚያንጸባርቅ አይደለም። ጀኔራል ታደሰ ብሩ በደርግ ሲገደሉ ብቻቸውን አልነበሩም። ጄኔራል ታደሰ ብሩን ደርግ የገደላቸው ከጭሰኞቻቸው ጋር ነበር። ሐውልት ሲቆምላቸው ግን አብረዋቸው የተገደሉት የታደሰ ብሩ ጭሰኞች መታሰቢያ አልቆመላቸው።

ኦነጋውያን ጀግና ለመፍጠር ስለሚፈልጉ የነሱን ትርክት ፈጥረው በጄኔራሉ ታሪክ ዙሪያ የራሳቸው ትርክት ፈጥረው ብዙ ውሸት አምርተዋል። ኦነግ የጀኔራል ታደሰ ብሩን የኢትዮጵያ አርበኛነትና የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የፈጥኖ ደራሽ አዛዥ እንደነበሩ ማውሳት አይፈልጉም። የዶክተር መራራ ጉዲና በነበረው በመኢሶን ቋንቋ ጀኔራል ታደሰ ብሩና ኮለኔል ኃይሉ ረጋሳ ፊውዳሎች ነበሩ። ጀኔራል ታደሰና ኮሎኔል ኃይሉ ጫካም የገቡት ኦነጋውያኑ እነ ባሮ ቱምሳ፣ ዲማ ነገዖና ዘገዬ አስፋው ያረቀቁትን የደርግን «የመሬ ላራሹ» አዋጅ ተቃውመው ነው።

ይህ ደርግና መኢሶን ያቀረቡት ትርክት ብቻ አይደለም። ለእድገት በኅብረት ዘመቻ የመሬት ላራሹን አዋጅ ሊያስፈጽሙ ከዘመቱ ተማሪዎች መካከል ጀኔራል ታደሰ ብሩ በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ መሬት ለጭሰኞች ለማከፋፈል ሲሞክሩ ጀኔራል ታደሰ ተማሪዎችን መሬት ለጭሰኞች ማከፋፈል አትችሉም ብለው ያባረሯቸው ተማሪዎችም አረጋግጠዋል። የዶክተር መራራ ድርጅት መኢሶንም እነ ታደሰ ብሩና መለስ ተክሌ በአንድ ቀን በተረሸኑበት ወቅት በልሳኑ ባወጣው መግለጫ ተራማጆቹ እነ መለስ ተክሌ ከፊውዳሎቹ ከነ ታደሰ ብሩ ጋር መገደል የለባቸውም የሚል መግለጫ አውጥቶ ነበር። በሌላ አነጋገር የዶክተር መራራ ጉዱና ድርጅት ፊውዳል ባሏቸው በጄኔራል ታደሰ ብሩ ላይ ደርግ የወሰደውን አብዮታዊ እርምጃ ደግፏል።

የዶክተር መራራ ተቃርኖ በዚህ አያበቃም። ዶክተር መራራ ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይን በኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲ ለማምጣት የተንቀሳቀሰ ጀግና አድርገው ያሞካሹታል። ይህን የሚሉን መራራ ጉዲና ጀኔራል ታደሰ ብሩ ያከሸፉትን ስዒረ መንግሥት የመሩትን እንቅስቃሴ ነው። ጄኔራል ታደሰ ብሩ ራሳቸው ታኅሣሥ 16 ቀን 1953 ዓ.ም. ለጀኔራል መድዕድ መንገሻ በጻፉት ማስታወሻ ይመሩት የነበረው የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ የገደላቸውንና የማረካቸውን የክቡር ዘበኛ ስዒረ መንግሥት አድራጊዎች ቁጥር በዝርዝር አስረድተዋል። አንድ ሰው ነገር አለሙ ካልተምታታበት በስተቀር ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይን በለውጥ ፈንጣቂነት አወድሶ መንግሥቱ ንዋይ የጀመሩትን የ«ለውጥ እርምጃ» በግንባር ቀደምትነት ያከሸፈውንና መንግሥቱ ንዋይ ያሰማራውን የክቡር ዘበኛ ሠራዊት የደመሰሰውን ጀኔርላ ታደሰ ብሩን ጀግና አድርጎ ሊያወድስ አይችልም። ዶክተር መረራ ግን ይህ አድርገዋል።

ለማንኛውም የጋራችን ምድር የሆነችዋ ኢትዮጵያ በአማራ ጥንተ ርስት ላይ የኦሮሞ ጄነራል ሐውልት ማቆም የሚቻልባት ምድር ናት። ከታች የታተመው ፎቶ መጋቢት 5 ቀን 1967 ዓ.ም. አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጀኔራል ታደሰ ብሩ ከነ ጭስኞቻቸውና ከኮሎኔል ኃይሉ ረጋሳ ጋር በሻለቃ ተስፋዬ ገብረ ኪዳን [ኋላ ጀኔራልና ከመንግሥቱ ኃይለ ማርያም በኋላ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት የበነበረው – የኦሮሞ ነገድ ተወላጅ ] በሚመራው የደርግ አሳሾች በተያዙበት ወቅት የተነሱ ፎቶ ነው። ጀኔራል ታደሰ ብሩ እንደሸፈቱ እጃቸው እንዲያዙ አልያም እምቢ ካሉ እንዲደመሰሱ ትዕዛዝ የሰጡት የደርጉ ደኅንነት ኃላፊ የነበሩት የወለጋው ኦሮሞ ኮሎኔል ተካ ቱሉ ነበሩ። ጀኔራል ታደሰ ተይዘው ልዩ የጦር ፍርድ በቀረቡ ጊዜ የልዩ የጦር ፍድር ቤቱ አቃቢ ሕግ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ የነበሩ ሲሆኑ ዳኛው ደግሞ ኦሮሞው ሻለቃ በቀለ ነዲ(የሜጫና ቱለማው አይደሉም) ነበሩ።

በሌላ አነጋገር ጀኔራል ታደሰ ብሩ የተረሸኑት ከሸፈቱበት ተይዘው እንዲመቱ ወይም እንዲረሸኑ ኦሮሞው ኮሎኔል ተካ ቱሉ በሰጡት ትዕዛዝ መሰረት ኦሮሞው ጀኔራል ተስፋዬ ገብረ ኪዳን ባካሄዱት ኦፕሬሽን ሲሆን፤ ጦር ፍርድ ቤት የቀረቡትና የሞት ቅጣት የተፈረደባቸው ደግሞ ኦሮሞው ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ አቃቢ ሕግ በነበሩበትና ኦሮሞው ሻለቃ በቀለ ዳኛ ሆነው በተሰየሙበት የልዩ ጦር ፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት ነው። ይህን በጀኔራል ታደሰ ብሩ ላይ የተላለፈውን የግፍ ፍርድ የደገፈው ደግሞ የነ ዶክተር መረራ ፓርቲ መኢሶን ነበር። እነ ዶክተር መረራ ጉዲና ግን ጀኔራል ታደሰ ብሩ በኦሮሞ እንደተገደለና የሳቸው ድርጅትም ጀኔራል ታደሰ ብሩ ሲገደል ፊውዳሉ ታደሰ እንደተገደለ መግለጫ አውጥቶ የጀኔራል ታደሰን መገደልረደግፎ እንደነበር ለመንጋቸው አይነግሩትም።

2 COMMENTS

 1. የዋሾ ሞቱ፣ቀልማዳነቱ!!!
  አቻምየለህ ፣ የኦሮሞ ድርጅቶች ና ህወሓት የሚያደርጉትን የታሪክ ዘረፋ አና ውሸት ማስፋፋት፣ ያለመታከት
  እየተከታተለ በሰነድ የተደገፈውን ትክክለኛ ታሪክ በማስቀመጥ የሚያደርገው ያላሰለሰ ትግል እጅግ የሚያስመሰግነው ነው።
  የአንድን አገር ታሪክ አዛብቶ ውሸት መስበክ፣ ሕዝብን በጅምላ በእፅ እንደመመረዝ ነው።እፁ ግማሹን አሳብዶት የማያውቀውን ሰው ለመጨረስ ይሯሯጣል። ሌላው፣ ትርክቱ አደንዝዞት ለጊዜውም ቢሆን ተጎጂ ይሆናል ።
  ይሄ እፅ ከ60ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በኦነግ ና በሕወሓት (ከውጭ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በመሆን) ተቀምሞ ሲሰራጭ፣ ሌሎቹ የኢትዮጵያ ምሁራን ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የአማራ ምሁራን በቸልተኝነት መቀበላቸው ፣ ያ ትውልድ በጊዜው ከሰራቻው ስህተቶች የመጀመሪያው ይመስለኛል ።
  መረራ ጉዲና ቢያንስ ሁለት ጊዜ ሞቷል ። የመጀመሪያው ሞቱ፣ደርግ ጀነራል ታደሰ ብሩን ፊውዳል ብሎ ሲረሽን ፣ በመኢሶን አባልነቱ ሲደግፍ ፣ ሁለተኛ ሞቱ ደግሞ፣በሰላሊ ላይ ባደረገው የቃል ጭፍጨፋ “የአፄ ምኒልክን ቤተመንግሥት ተቆጣጥረን የጀኔራል ታደሰ ብሩን ሐውልት እናቆማለን ” ብሎ መቀላመዱ ብቻ ሳይሆን ለደጋፊዎቹ ፊሽካ ነፍቶ የደብረሊባኖስን ቀሳውስት ና ምእመናን ለማስጨፍጨፍ ሲነሳ ነው።
  መረራ ጉዲና ከማረፉ በፊት ከውጭ ቅጥረኛው ጀዋር ጋር ተዳብሎ ለ3ኛው ሞቱ እየተንደረደረ ነው።

  ዳንኤል ክብረትም ቢሆን ያልተጣራ፣የውሸት ና የፈጠራ ታሪክ በማሰራጨት አውቆም ሆነ ሳያውቅ የኦሮሞ ፋሽስቶች ተባባሪ ሆኗል ። እውቀቱም ከድቁና እንዳላለፈ ታይቷል ። የዳንኤል ክብረት አንድ ትክክለኛ ታሪክ
  ቢኖር ፣ እራሱን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ማለቱ ነው። የድቁናን ትምህርት ለማሳነስ ሳይሆን ፣ዳንኤል ክብረት ለተንጠራራበት ብቁ የታሪክ ምሁርነት እንደሚቀረው ለማሳየት ነው።

 2. አቻምየለህ ታምሩ ብእርህ አይድረቅ
  አንድ ወንድ ይህን ሃሰት የሚል? እርስ በእርሱ አቆላልፎት ቁጭ አለ ::ይህንን ጉድ ይዘዉ እፍረት የላቸዉም ታሪከ ሰሪም መሆን ያምራቸዋል የኛ ነዉ የሚሉትም ነገር አላቸዉ። እስቲ ከዚህ ልብ ይገዙ ይሆናል ብለን እንገምታለን። አሁንም አላርፍም ካሉ ወደ ሗላ ተጉዘን 14ኛዉ ክፍለ ዘመን እንገባለን።፡አክብረዉ ተከብረዉ የሚኖሩ ከሆነ አብሮ ለመኖር ችግር የለብንም ግን አድራጊ ፈጣሪ እኛ ነን ብዙሃን እኛ ነን የሚሉትን የብልጥ ሂሳብ ቢተዉን ይሻላል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.