በ12ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ውድድር ዛሬ ፋሲል ከነማ ከወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ይጫወታሉ፡

ፋሲል ከነማ ከሜዳው ውጭ ሲጫወት ያለውን ታሪክ ለመቀየርና ለመሻሻል ጥረት እንደሚደርግ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ተናግረዋል፡፡ ፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ባደረጋቸው 11 ጨዋታዎች በአምስት አሸንፏል፡፡ በሁለቱ ሲሸነፍ በአራቱ ደግሞ በአቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡ አቻ የወጣባቸው እና የተሸነፈባቸው አብዛኛዎቹ ጨዋታዎች ደግሞ ከሜዳው ውጪ ባደረጋቸው ውድድሮች ነው፡፡

ለምን? አማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት አሰልጣኝ ስዩም ከበደን ጠይቋል፡፡ ‹‹የዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ ሲጀመር ቡድኑ በአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታ ዋንጫ ያነሳው ከሜዳው ውጪ ተጫውቶ ነበር፤ ከድሉ በኋላ ከአዳማ ከተማ ጋር ባደረግነው ጨዋታም በአቻ ውጤት ነበር ያጠናቀቅነው›› ብለዋል አሰልጣኝ ስዩም፡፡ ከሜዳ ውጪ ሲጫወቱ እየታዬ ያለው ሁኔታ ሲደጋገም የሥነ ልቦና ጫና ሊያሳድር እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

በእርግጥ ከሜዳ ውጭ ያለው ውጤት በክለቡ ሥነ ልቦና ዝግጅት የሚወሰን ቢሆንም በርትቶ ከመጫዎት ባለፈ ዕድልም ወሳኝ እንደሆነ አሰልጣኙ ተናገረዋል፡፡ ‹‹ጥር 20/2012 ዓ.ም ከጅማ አባ ጅፋር ጋር በነበረን ጨዋታ የጨዋታ ብልጫ ነበረን›› ብለዋል አሰልጣኝ ስዩም ከበደ፡፡ ፋሲል ከ11 ጊዜ በላይ የግብ ሙከራ ማድረጉን፣ ሦስት ኳሶች የግብ ዘንግ ጋር ተጋጭው ወደ ግብነት ሳይቀየሩ መቅረታቸውንና እድሉን ያለመጠቀም ሁኔታም መስተዋሉንም አስታውሰዋል፡፡

ከሰበታ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታም በተመሳሳይ ፋሲል የጨዋታ ብልጫ እንደነበረው አሰልጣኝ ስዩም አንስተዋል፡፡ ከሜዳ ውጭ ያለውን ታሪክ ለመቀየርና ለመሻሻል ደግሞ ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም በሜዳውና በደጋፊው ፊት እንደሚያደረግው ሁሉ በሰከነ ጨዋታ ለማሸነፍ ጥረት እንደሚደረግ ነው የተናገሩት፡፡ በ11ኛ ሳምንት ከሜዳቸው ውጭ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ከተጫዎቱ በኋላ አጼዎቹ በጅማ አባ ጅፋር ደጋፊዎች አስደናቂ አሸኛኘት እንደተደረገላቸውም አሰልጣኝ ስዩም ተናግረዋል፡፡

ዛሬ የሚደረገውን ጨዋታ በማሸነፍ በዋንጫ ፉክክሩ ለመቀጠል በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውንም አሰልጣኙ ገልጸዋል፡፡ ሁሉም ተጨዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ መገኘታቸውና ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸው ደግሞ ሀሳቡን ለማሳካት መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ የፋሲል ከነማ ተመላላሽ ተከላካይ ተጨዋቹ አምሳሉ ጥላሁን (ሳኛ) ደግሞ ከሜዳ ውጭ በርካታ ተፅዕኖ እንደሚደርስ አስረድቷል፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሀገሪቱ ሠላም ሁኔታ ጋር በተያያዘ እና ዳኞች በፍራቻ ስለሚያጫውቱ ለማሸነፍ ከባድና አስቸጋሪ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

ከሜዳ ውጭ ነጥብ ሊያዝበት የሚችለው የአዲስ አበባ ስታዲዬም እንደሆነና ሌሎች ሜዳዎች ላይ ጫናዎች እንደሚበረክቱ ነው የገለጸው፡፡ ዛሬ ጥር 25/2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ጨዋታ ፋሲል ከነማ በሜዳውና በደጋፊው ፊት ከወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ይጫወታል፡፡ ጨዋታው በፋሲለደስ ስታዲዬም ቀን 9፡00 ይካሄዳል፡፡ ሰበታ ከተማ ደግሞ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ይጫዎታል፡፡

ፎቶ፡- ከፋሲል ከነማ ማኅበራዊ የመረጃ ገጽ

ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.