የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እየሰራች ነው

የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመቆጣጠር የቻይና መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ገለጸ። የቻይና ከተሞች የተቀሰቀሰውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የትራፊክ እንቅስቃሴ እገዳና ፌስቲቫሎችን እየሰረዙ ነው።

የቻይና መንግስት ቫይረሱ በአገሪቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ የተጠናቀረ የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባር እያከናወነ ነው። በአንድ የቻይና ግዛት ተከስቶ ወደ 31 ግዛቶች በተስፋፋው በዚህ ቫይረስ የሚያዙ ሰዎችን የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ የሚሰጡ ተቋማት አግልግሎት ላይ ናቸው።

ሆኖም ቫይረሱ ካለው ፈጣን ስርጭት አንጻር በርካታ የቻይና ከተሞች በትራንስፖርትና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ እገዳ እየጣሉ ነው።

የትራፊክ እንቅስቃሴ እገዳ፣ ህዝብ የሚሰበሰብባቸው ፌስቲቫሎችን መሰረዝ፣ በጊዜአዊነት የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን መዝጋት እየተወሰዱ ካሉ እርምጃዎች መካከል ይገኙበታል።

የቻይና መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያን መዳረሻቸው የሚያደርጉ የቻይና ዜጎችም ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት የሚደረጉ አስፈላጊ ምርመራዎችን አልፈው መሆን እንዳለበት ኤምባሲው አቋሙን ገልጿል።

የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ቫይረሱ እየተስፋፋበት ካለው ፍጥነት አንጻር የአለም የጤና ስጋት በመሆኑ አለም ትኩረት እንዲሰጠው ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ቻይና በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አቅም እንዳላት ያስቀመጠው የኤምባሲው፤ ለዚህም የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንዳላት ገልጿል።

ቻይና በሽታውን በተመለከተ በግልጽነትና በሃላፊነት በተሞላው ወቅታዊ መረጃዎችን ለአለም ይፋ ታደርጋለች።

ከአንድ ወር በፊት በቻይና የውሃን ከተማ የተከሰተው ኮሮና ቫይረስ እስካሁን ከ300 በላይ ሰዎችን የገደለ ሲሆን ከ14 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ደግሞ በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጧል።

ቫይረሱ ከቻይና ውጪ ወደ ሌሎች የአለም አገሮች እየተስፋፋ ሲሆን ጃፓን፣ አውስትራሊያ፣ ፈረንሳይ፣ አሜሪካና ሌሎች አገሮች በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸው ተረጋግጧል።

በሽታው ሲጀምር የትኩሳት ምልክት ሲያሳይ ደረቅ ሳል አስከትሎ የትንፋሽ ማጠርን ያስከትላል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.