መንግስቱ ጋሼ ከሌሎች ንጹሃን ኢትዮጵያን ጋር ሰማዕት ሆኖ በሊቢያ በረሀ ቀርቷል

345በምስራቅ ወለጋ ዞን ዋዮ ጡቃ ወረዳ ውስጥ የምትገኘው ጋራ ሆዳ ቀበሌ- ከአዲስ አበባ 331 ኪ.ሜ ተጉዘው ነቀምት ለመድረስ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ሲቀር ትገኛለች፡፡ ከእዚህች ቀበሌ ወጣ ብላ በምትገኝ አነስተኛ የገጠር መንደር ውስጥ ነው ሰማዕቱ መንግስቱ ጋሼ የተወለደው፡፡ የ60 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት ወ/ሮ አለሚቱ ከወለዷቸው 12 ልጆች መካከል የቤተሰቡ 6ተኛ ልጅ የነበረው መንግስቱ ጋሼ ከሌሎች ንጹሃን ኢትዮጵያን ጋር ሰማዕት ሆኖ በሊቢያ በረሀ ቀርቷል…

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፤በምስራቅ ወለጋ ዞን ዋዮ ጡቃ ወረዳ ውስጥ የምትገኘው ጋራ ሆዳ ቀበሌ- ከአዲስ አበባ 331 ኪ.ሜ ተጉዘው ነቀምት ለመድረስ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ሲቀር ትገኛለች፡፡ ከእዚህች ቀበሌ ወጣ ብላ በምትገኝ አነስተኛ የገጠር መንደር ውስጥ ነው ሰማዕቱ መንግስቱ ጋሼ የተወለደው ፡፡
የ60 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት ወ/ሮ አለሚቱ ከወለዷቸው 12 ልጆች መካከል የቤተሰቡ 6ተኛ ልጅ የነበረው መንግስቱ ጋሼ ከሌሎች ንጹሃን ኢትዮጵያን ጋር ሰማዕት ሆኖ በሊቢያ በረሀ ቀርቷል ፡፡


መንግስቱ ገና የ3 ዓመት ህጻን እያለ ነበር በ1983 ዓ.ም ወላጅ አባቱ በድንገት ከእዚህ ዓለም በሞት የተለዪት ፡፡… በወቅቱ ቤተሰቡ በአባወራው ሞት ምክንያት ከፍተኛ ችግር ውስጥ በመውደቁ መንግስቱ ጉልበቱ ሳይጠነክር … አቅም ሳያደረጅ ገና የ7 ዓመት ጨቅላ እያለ በዓመት ብር 70 (ሰባ ብር) ብቻ እየተከፈለው በአከባቢው ሻል ያለ ኑሮ ለነበራቸው ገበሬዎች በከብት እረኝነት ተቀጠረ፡፡ ከከብት እረኝነቱ በተጨማሪ በጊዜው አቅሙ የሚችለውን የእርሻ ስራ መስራትም ግዴታው ነበር ፡፡
ለ3 ዓመት ያህል በከብት እረኝነት ከሰራ በኋላ ዕድሜው 10 ዓመት ሲሞላው እራሱን ለመቻል እንዲሁም እናቱን ለመርዳት ሲል ዶሮ ማርባት ጀመረ ፡፡ያረባቸውን ዶሮዎችና እንቁላሎች ከትውልድ መንደሩ አቅራቢያ ካለው አርብ ገበያ እየሸጠ ከወጪ የሚተርፈውን አነስተኛ ገንዘብ እያጠራቀመ በግ…በሬ…ላም ማርባት ስራው ሆነ ፡፡ ዕድሜውም ጨመረ ፡፡ ግን በችግር እየዳከሩ …መከራ እያዩ ያለ አባት የሚያሳድጉት እናቱን ለመርዳትና የተሻለ ነገር ለማግኘት አስቦ ከ3 ዓመት በፊት ወደ ሱዳን አመራ ፡፡ በሱዳን ቆይታውም ግንበኝነት እየሰራ …ከሰል እየሸጠ ካጠራቀመው ገንዘብ ውስጥ ሰባት ሺህ ብር በመላክ ወላጅ እናቱ ወ/ሮ አለሚቱ አነስተኛ የቆርቆሮ ቤት እንዲሰሩ አደረገ ፡፡
ከልጅነቱ ጀምሮ መንግስቱ ድሃ እናቱን ለመርዳት ህልሙ ትልቅ…ተስፋውም ሩቅ ነበር፡፡ ሱዳን በስደት ላይ እያለ ባጠራቀመው ገንዘብ ወደ ሀገሩ ተመልሶ ለእርሻ የሚሆን አነስተኛ መሬት በመግዛት ወላጅ እናቱ አጠገብ ሆኖ ደካማ እናቱን መርዳት ነበር ሃሳቡ ፡፡ ግን በመሃል ላይ ከትውልድ መንደሩ አብሮት የተሰደደውና ቀደም ብሎ ወደ ሊቢያ የተጓዘው ጓደኛው ከሊቢያ ወደ ጀርመን መግባቱን ይነግረዋል ፡፡ ሁሌም የተሻለ ነገር ነው ብሎ ያመነበትን የሚያደርገው መንግስቱ ጓደኛው ጀርመን መግባቱን ሲነግረው እርሱም ወደ ሀገር የመመለስ ሃሳቡን ሰርዞ ጓደኛው በተጓዘበት መንገድ ተጉዞ ጀርመን ለመድረስ ወደ ሊቢያ ያመራል ፡፡ ግን ካሰበው ሳይደርስ አይ.ኤስ በተባለው ፅንፈኛ ቡድን እጅ ወደቀና በሰው ሀገር …በሰው መሬት መስዋዕት ሆነ፡፡
ጆሲ መልቲሚዲያ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፤በምስራቅ ወለጋ ዞን ዋዮ ጡቃ ወረዳ ውስጥ የምትገኘው ጋራ ሆዳ ቀበሌ ወደሚኖሩት መንግስቱ ጋሼ ቤተሰቦች ዘንድ ተጉዞ ሀዘኑን ገልጾና መፅናናትን ተመኝቶ ሲያበቃ ፤በሚኒሶታ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሌሎች የኤጋን ፓስት ኦፊስ ሰራተኞች እና የኤርፖርት ፖስት ሮድ ታክሲ አሽከርካሪዎች በአቶ ዳንኤል አሰፋ በኩል የላኩትን የኢትዮጵያ ብር 40‚000 (አርባ ሺ ብር) ለወጣት መንግስቱ ወላጅ እናት ለወ/ሮ አለሚቱ አስረክቧል ፡፡
በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጥልቅ ሀዘናቸውን ለገለፁ፤ እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን በሞት ላጡ ወገኖቻችን የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉትንና እያደረጉ ያሉትን ሁሉ ጆሲ መልቲሚዲያ በመላው ኢትዮጵያውያን በተለይም በሀዘንተኞቹ ስም ከፍተኛ ምስጋና ያቀርባል ፡፡
ወደ መንግስቱ ጋሼ ቤተሰቦች ዘንድ ስንሄድ ግዜውን መስዋት አድርጎ አብሮን የተጓዘውን በነቀምቱ ጋዜጠኛ ኬኔሳ አመንቴንና እሱን እንድናገኘው የተባበረንን መምሕር ዘመድኩን በቀለንም እናመሰግናለን ፡፡
መንግስቱ ጋሼን በሞት ያጡት ወላጅ እናቱና ቤተሰቦቹ አሁን በከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው ያሉት ፡፡ በአሳዛኝ ድህነት ውስጥ የሚዳክረውን ይህንን ቤተሰብ ለመታደግ የአካባቢው ተወላጆች …በጎ አድራጊ ግለሰቦችና ድርጅቶች የበኩላቸውን ድጋፍ ያደርጉላቸው ዘንድ ጆሲ መልቲሚዲያ መልዕክቱን ያስተላልፋል ፡፡… ሁላችንንም

ፈጣሪ ያፅናናን ፡፡
ጆሲ መልቲ-ሚዲያ

Jossy in z house show

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.