የታገቱ ተማሪዎች ስለመኖራቸው ጥርጥር የሌለው ሃቅ መሆኑን የሚጠራጠር ካለ ዋና ማረጋገጫው የተማሪዎቹ ወላጆች እንባ ነው – መስከረም አበራ

እነዚህ ምስኪን ሰዎች “እነሱን አያድርገኝ” በሚያሰኝ መከራ ውስጥ እንዳሉ የወለደ ሁሉ ያውቀዋል። ስለዚህ ተማሪዎች እንዳልታገቱ ለማስመሰሉ የማያዋጣ፣ ብዙ መዘዝም ያለው ነገር ነው።

የታጋች ተማሪዎች ቁጥር ሌላው መወዛገቢያ ነጥብ ነው። የታገቱ ተማሪዎችን መንግስት እያሳነሰ በማቅረቡ ቢቀጥልም በኩሌ እንደ VOA ያሉ ታማኝ የዜና አውታሮች የዘገቡትን ማመኑን እመርጣለሁ። ዋናው ጉዳይ ቁጥር አለመሆኑን ለማዎቅ ግን የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ከስልጣን እና ፕሮፖጋንዳ የበለጠና ክቡር ነገር እንደሆነ ማዎቅን ይጠይቃል።

የማይገቡኝ ነገሮች

መንግስት የአስራ ሰባት ሰብዓዊ ፍጡራንን ህይወት ጉዳይ መጀመሪያ ለማድበስበስ፣ማድበስበሱ አልሆን ሲል ደሞ ለማረሳሳት የመሞከር አይነት የማይሆን አካሄድ ውስጥ ከመግባት ይልቅ እንደሰማ፣ሳይውል ሳያድር ለህዝብ አሳውቆ የጋራ ጉዳይ ቢያደርገው ኖሮ ይሄኔ መፍትሄውንም ይገኝ ነበር። የማይደበቅን ነገር ለመደበቅ የተጀመረው ድብብቆሽ /ብሎም ውሸት ለምን እንዳስፈለገ አልገባኝም! የማይደበቀውን መደበቁ የተከሰተውን ነገር ውጤት ለማይቀይረው ወይም መንግስት እንደፈለገው ነገሩ ተረሳስቶ ላይቀርለት አጉል ራሱን መንግስትን ለትዝብት ይዳርገዋል ፣ለወደፊቱም ተአማኒነቱን አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ነው።

መፍትሄ የሚመስለኝ

መንግስት እስከዛሬ ነገሩን ለማለባበስ ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካ ተረድቶ ነገሩን ለህዝብ ግልፅ ማድረግ አለበት።ምናልባት ነገሩን ግልፅ ማድረግ የልጆቹን ህይወት አደጋ ላይ ይጥላል ከተባለም ቢያንስ የልጆቹን በህይወት መኖር አስረግጦ መናገር አለበት። መቼም “ለልጆቹ ህይወት ስል ሙሉ መረጃ ለመሰጠት እቸገራለሁ” የሚባለው ልጆቹ በህይወት አሉ ለማለት ነው።

ልጆቹ ላይ ከዚህ የከፋ ነገር ደርሶም ከሆነ በግልፅ ተናግሮ ምስኪን ወላጆችም ሆነ ህዝቡ ቁርጡን አውቆ እንዲቀመጥ ማድረግ ነው። ይህን እያወቁ ዝም ማለቱ ፣በተለይ ይሄን ያህል ተቆይቶ ልጆቹን በህይወት ለወላጆቻቸው ማስረከብ ካልተቻለ በጣም መጥፎ ችግር የሚያመጣ ነገር ነው።ከመጀመሪያው መንግስት ነገሩን ለመደበቅ ባይሞክር ኖሮ ህዝቡ ከመንግስት ጎን ሆኖ የሚያወግዘው አጋቾችን ነበር። አሁን ግን ከአጋቾቹ በላይ እየተወገዘ ያለውም ግዴለሽነቱ የበዛው መንግስት ነው።

አሁንም ነገሩን ችላ ማለት እንደ ሰነፍ ዕረኛ ከሩቅ የመመለስ ውስብስቦሽ ውስጥ መግባት ነው። ድብብቆሹን ያመጣው ነገሩን ከሰብአዊነት ይልቅ በፖለቲካ መነፅር ማየቱን ነው። በተቀረ እንኳን እንደኛ አንድ የሚረባ ተቋም በሌለው ሃገር ቀርቶ FBIን የመሰለ ተቋም ባላት አሜሪካም ሰዎች ት/ቤት ገብተው ህፃናት ላይ የጥይት እሩምታ ያወርዳሉ። ስለዚህ ከእውነት መታረቅን የመሰለ መፍትሄ የለም! ከሁሉም በላይ ለታጋች ለቤተሰቦች ሰዋዊ ሃዘኔታን ማሳየት ያስፈልጋል።ነገ ዛሬ ሳይባል ቁርጣቸውን ማሳወቅ ያስፈልጋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.