አዲስ አበባን አዲስ አበባ ካሰኟት ህዝቦች መካከል አንዱ የሆነው ጋሞ አሻራው በጉልህ ደምቆ በሚታይበት ከተማው ዛሬ ነግሶ ውሏል

ለዘመናት የሚያሰባስበው አጥቶ የሚገባውን ክብር ሳያገኝ ለኖረው የቱንጋ ጋሞ ህዝብ የዛሬዋ ቀን ታሪካዊ ናት። ጋሞነት ደብዛው ጥፍቶ ከኖረበት በኩራት ወጥቶ የነገሰበት፤ የጋሞ ሥነልቦና ከፍታውን ዳግም ያሳየበት፤ የጋሞ ኢትዮጵያዊ ባህሉ ከአዳራሹ አልፎ መላ ሸገርን ያዳረሰበት የኩራት ቀን ነው።

ጋሞ የሚባል ህዝብ የለም ብለው በቁም የቃዡትን በቁማቸው የቀበርንበት፤ ጋሞን ሰባበርነው ብለው ያወጁትን ሰብረን የጣልንበት፤ ገድለን አጠፋነው ብሎም አሳደድነው ብለው ያሰቡትን ዓይናቸው እያየ አንገት ያስደፋበት የካቲት 30 ደማቅ ቀናችን ነው!

ጋሞ ለምሣ ያሰቡትን ለቁርስ አውሎ ፍቅር የሚያበላ የፍቅር ህዝብ መሆኑን ያስመሰከረበት ይህ ቀን የትኛውም ፈተና አይሎ ቢመጣበት እንኳን ጋሞ እና የጋሞ ሥነልቦና ከቶ የማይወድቁ ይልቁንም እንደአጥቢያ ኮከብ ሲያበሩ የሚኖሩ መሆናቸው የተረጋገጠበት ዕለት ነው።

በተለይ ለዚህ ወቅት የማዶላ የግብር ልጆች ጋሞን በጎጥ እና ቀበሌ ከፋፍሎ ለማሳነስ ከመሞከር ከሰማይ ላይ ከዋክብትን ማርገፍ እንደሚቀል፤ ጋሞ የሚባል ህዝብ እና ብሄር የለም በሚል እንቶ ፈንቶ ወሬ ከመባከን አዲስ ማንነትን ከውሃና አፈር መስራት እንደሚቀል ያስመሰክርንበት የዛሬዋ ታሪካዊ ቀን በየ5 ዓመቱ ሳይሆን ሁሌም በየዓመቱ ደምቃ ልትደረግ ይገባል።

የሀገሪቱን ቁንጮ ባለሥልጣናት እርጥብ ሣር አሲዞ ያንበረከከው ይህ ድንቅ ባህላችን በቀጣይም በቤታችን ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ያኮረፉ እና የተገፋፉ ወንድማማቾችንም በአንድ የፍቅር ማዕድ ሊያሰባስብ ይገባል።

ጋሞ እስካሁን እያጋጠሙት ከመጣው ፈተና ይልቅ በቀጣይ የሚገጥመው ስለሚጠነክር ማዶ የሚታየንን ዳገት በጋራ ልንወጣው ይገባል። እንኳንስ ተከፋፍሎ አንድ ሆኖ ጋራውን መውጣት የሚከብደ ቢሆንም ከአባቶቻችን በወረስነው የጀግንነት ባህላችን ሁሉንም ድል እናደርጋለን።

እኛ ጋሞዎች ጠፉ ሲሉን የምንበዛ፤ የሉም ሲሉን ልክ እንዳዛሬው በዝተን የምንኖር ኢትዮጵያ ያፈራችን የትልቅ ሀገር ትልቅ ልጆች ነን!

Gamo Media Network

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.