ለቸኮለ! የዛሬ ዐርብ መጋቢት 11/2012 የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1. ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሰዎች ኮሮና ቫይረስን ለመቆጣጠር ሲባል ለ14 ቀናት በልዩ ማቆያ እንዲገቡ መንግሥት እንደወሰነ ኢቢሲ ዘግቧል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ወደ 30 ሀገራት የሚያደርገውን በረራ አቋርጧል፡፡ ዘገባው ሀገሮቹን በስም አልጠቀሰም፡፡

2. በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠረው የፋና ብሮድካስት ጋዜጠኛ ከቫይረሱ ነጻ መሆኑ በምርመራ እንደተረጋገጠ ፋና ዘግቧል፡፡ ጋዜጠኛው ምርመራ የተደረገለት ትናንት ነበር፡፡ ጋዜጠኛው መጀመሪያ በቫይረሱ መያዛቸው ከተነገረላቸው ጃፓናዊ ጋር ከተገናኙ ሰዎች ጋር እንጅ ራሱ ቀጥተኛ ግንኙነት አልነበረውም ተብሏል፡፡

3. በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 9 ደርሷል፡፡ ትናንት ከተገኙት 3 ሰዎች አንዱ መጋት 6 ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የ39 ዐመት አውስትራሊያዊ ሲሆን፣ ሌላኛዋ ቀደም ሲል በቫይረሱ ከተያዙ ግለሰብ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ጃፓናዊት ናቸው፡፡ ሦስተኛው፣ የካቲት 23 ከውጭ ሀገር የገቡ የ85 ዐመት ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡

4. በአፍሪካ በቀጣይ ሳምንታት የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት እንደሚጨምር ዘ ኢስት አፍሪካን ዘግቧል፡፡ የአሕጉሪቷ የበሽታዎች መከላከያ ማዕከል ሃላፊ ዛሬ በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ፣ በርካታ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከክትትል እና ምርመራ ውጭ እንደሆኑ እንገምታለን ብለዋል፡፡ የጉዞ እገዳዎች ሥርጭቱን ቢያዘገዩት እንጅ ማስቆም አይችሉም፡፡ 40 ሀገሮች ራሳቸውን ችለው ምርመራ እያደረጉ ነው፡፡

5. ኬንያ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል መጠጥ ቤቶች እና የምሽት መዝናኛ ቤቶች ከምሽቱ 7፡30 በኋላ እንዲዘጉ እንዳዘዘች የሀገሪቱ ጋዜጦች ዘግበዋል፡፡

6. የግብጹ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሳሚ ሽኩሪ ትናንት በሕዳሴው ግድብ ውዝግብ ላይ የፕሬዝዳንት አልሲሲን መልዕክቶች ለሩዋንዳ፣ ለኮንጎ እና ታንዛኒያ ማድረሳቸውን አህራም ድረገጽ ዘግቧል፡፡ ግብጽ ሁሉንም የናይል ተፋሰስ ሀገሮች በተናጥል ለማግባባት ዘመቻ ላይ ናት፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.