ለቸኮለ! የዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 15/2012 የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1. በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ፣ ከነገ ጀምሮ ሁሉም የፌደራል መንግሥት ሠራተኞች ከቤታቸው እንዲሰሩ የሚንስትሮች ምክር ቤት ዛሬ መወሰኑን ከጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ፌስቡክ ገጽ አይተናል፡፡ ዝርዝሩን ሚንስቴር መስሪያ ቤቶች ይወስናሉ፡፡ ተለዋጭ ውሳኔ እስኪሰጥ ይኼ ውሳኔ ይጸናል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ተመሳሳይ ውሳኔ እንዳሳለፈ የከንቲባው ጽሕፈት ቤት በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡

2. በኢትዮጵያ አንድ ተጨማሪ በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው እንደተገኘ ጤና ሚንስትር ዶ/ር ሊያ ታደሠ በፌስቡክ ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡ በበሽታው የተያዘው ሰው የ34 ዐመት ኢትዮጵያዊ መጋቢት 10 ከዱባይ ወደ ሀገሩ የገባ ነው፡፡ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ብዛት 12 ደርሷል፡፡

3. የኮሮና ቫይረስን አኮኖሚያዊ ጫና ለመቋቋም መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ቡድን እንዳቋቋመ ዋዜማ ተረድታለች፡፡ ባንኮችም የደንበኞችን ብድር መክፈያ ጊዜ እንዲያራዝሙ መንግሥት በማግባባት ላይ ነው፡፡ LINK-https://bit.ly/2Uf80Rd

4. በሞዛምቢክ ድንበር ዕቃ መጫኛ ተሸከርካሪ ውስጥ ታፍነው የሞቱ 64 ሰዎች ኢትዮጵያዊያን ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡ ሟቾቹ በሕገወጥ መንገድ ከማላዊ በሞዛምቢክ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲጓጓዙ የነበሩ ስደተኞች ናቸው፡፡ 14 ብቻ በሕይወት ተገኝተዋል፡፡ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የሟቾቹን ብዛት እያጣራ መሆኑን በፌስቡክ ገጹ ገልጧል፡፡

5. የጎንደር ከተማ አስተዳደር በከተማዋ ፋኖ በሚል ስያሜ የተደራጀው የታጠቀ ቡድን ትጥቁን ፈትቶ ለመንግሥት እጁን እንዲሰጥ እስከ መጋቢት 20 ቀነ ገደብ ማስቀመጡን የአማራ ብዙኻን መገናኛ ዘግቧል፡፡ ሕገ ወጡ ቡድን የሕዝብን ሰላም እና ጸጥታ ሲያደፈርስ ቆይቷል፡፡ በከተማዋ ከእንግዲህ ማንኛውም ቡድን ወይም ግለሰብ መሳሪያ ታጥቆ መንቀሳቀስ አይችልም፡፡

6. የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቻይናው ባለሃብት ጃክ ማ ለአፍሪካ የለገሷቸውን የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶች ለጎረቤት ሀገራት ሲያደርስ ውሏል፡፡ አየር መንገዱ የፊት መሸፈኛ እና ሌሎች የሕክምና ቁሳቁሶችን ለደቡብ ሱዳን እና ኡጋንዳ አድርሷል፡፡

7. በኬንያ ዛሬ 9 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘው መገኘታቸውን ዴይሊ ኔሽን ጤና ሚንስቴርን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ ትናንት 16 የነበረው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ብዛት አሁን ወደ 25 አሻቅቧል፡፡ ከውጭ በሚገቡ እና በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር ግንኙነት ባደረጉ ሰዎች ላይ አስገዳጅ ምርመራ ይደርጋል፡፡

8. በመጭው ሐምሌ በቶኪዮ ጃፓን ሊካሄድ የነበረው የ2020 የዐለም ኦሎምፒክስ በኮሮና ቫይረስ ስጋት ሳቢያ ወደ ቀጣዩ ዐመት መተላለፉን ዛሬ ዐለም ዐቀፍ የዜና አውታሮች ዘግበዋል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.