ለቸኮለ! የዛሬ ዐርብ መጋቢት 18/2012 የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1. መንግሥት ትምህርት ቤቶች ለተጨማሪ 2 ሳምንት እንዲዘጉ መወሰኑን ከጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ፌስቡክ ገጽ አይተናል፡፡ ጡረተኛና ትምህርት ላይ ያሉ የጤና ባለሙያዎች ለብሄራዊ ግዳጅ እንዲዘጋጁ ተጠይቀዋል፡፡ ለቫይረሱ መከላከያ ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶች ላይ ቀረጥ ተነስቷል፡፡ ንግድ ባንኮች ኑሯቸው ለሚናጋባቸው ወገኖች እንዲያበድሩ፣ ብሄራዊ ባንክ 15 ቢሊዮን ብር ያከፋፍላል፡፡ ከውጭ የሚገቡ ሰዎች ሆቴል ለመቆየት አቅም ከሌላቸው፣ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርስቲ ይገባሉ፡፡

2. በኮሮና ቫይረስ የተያዙ 4 ተጨማሪ ሰዎች እንደተገኙ ጤና ሚንስቴር በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡ አንደኛው ከኮንጎ የተመለሱ ሞሪሺየሳዊ፣ ሌሎቹ ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዳማ የተገኙት እና አንድ ሌላ ኢትዮጵያዊ የውጭ ጉዞ አድርገው አያውቁም፡፡

3. የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ በኮሮና ቫይረስ ጥርጣሬ ራሳቸውን እንዳገለሉ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡ ሙሳ ከ2 ሳምንት በፊት ከኮንጎ የተመለሱ ሞሪታኒያዊ የቢሮ ተባባሪያቸው በቫይረሱ መያዛቸው እንደታወቀ ኤኤፍፒ ቀድሞ ዘግቦ ነበር፡፡ ሞሪታኒያዊው ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ይሁን አይሁን አልተገለጸም፡፡

4. በማኅበራዊ ሜዲያ ስለ ኮሮና ቫይረስ ሐሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ ጦማሪያን ላይ ርምጃ እየወሰደ መሆኑን ፌደራል ፖሊስ እንዳስታወቀ ፋና ብሮድካስት ዘግቧል፡፡ ቫይረሱን ለመቆጣጠር የወጡ መመሪያዎችን የሚጥሱ አካላት ላይም ርምጃ ይወሰዳል፡፡

5. የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ በረራ ያቋረጠባቸው ሀገራት 72 እንደደረሱ ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ ተናግረዋል- ሲል ሸገር ዘግቧል፡፡ ወደፊትም ሌሎች በረራዎች ሊቋረጡ ይችላሉ፡፡

6. በኤርትራ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች 6 እንደደረሱ ከሻባይት ድረገጽ ተመልክተናል፡፡ ሀገሪቱ ከዛሬ ጀምሮ ትምህርት ቤቶችን ዘግታለች፤ የሕዝብ መጓጓዣዎችንም በሙሉ አግዳለች፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.