ኮሮናቫይረስ፡ “ቀጣፊ ዋሾ ነሽ፣ አሳፋሪ ሰው ነሽ” ዶናልድ ትራምፕን ያስቆጣችው ጋዜጠኛ

የዶናልድ ትራምፕ ጋዜጣዊ መግለጫ ራሱን የቻለ የኮሜዲ ትዕይንት መልክ የሚይዝበት ጊዜ ብዙ ነው። የትናንት ምሽቱ ከነዚህ የሚመደብ ነው፡፡ በዋሺንግተን ሰኞ ከሰዓት ነው የተደረገው፤ በኛ ሌሊቱን።

በትራምፕ ጋዜጣዊ መግለጫ ታሪክ ዘለግ ያለ ሰዓት ወስዷል የተባለት ይህ ጋዜጣዊ መግለጫ በድራማዎች የተሞላ ነበር። በድምሩ 2 ሰዓት ከ 24 ደቂቃ የወሰደ መሆኑም ልዩ ያደርገዋል።

ወትሮም ትራምፕ ጠላቶቼ ከሚሏቸው ጋዜጠኞች ጋር የሚያደርጉት ቆይታ አንዳች አስቂኝ ክስተት አያጣውም።

ለምሳሌ ባፈለው አርብ በፈረንጆች ስቅለት ዕለት በነበራቸው መግለጫ ጋዜጠኞቹን፣ “እስኪ ዛሬ እንኳ እርስ በርስ እንተሳሰብ፤ ስቅለት ነው፤ እስኪ ዛሬ እንኳ ጨዋ ሁኑ…” ብለው ነበር መድረኩን ለጥያቄ የከፈቱት።

ዶናልድ ትራምፕ “ተራ ጉንፋን ነው፤ በራሱ ጊዜ ብን ብሎ እንደ ተአምር ይጠፋል” ሲሉት የነበረው ቫይረስ 600ሺህ የሚጠጋ ዜጋቸውን አጥቅቷል። ከ20ሺ በላይ አሜሪካዊያንን ገድሏል። አሁንም ቢሆን ግን እርሳቸው ስለ ስኬታቸው እንጂ ሌላ ማውራት አይወዱም።

ከሰሞኑ የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ዶናልድ ትራምፕ ፈጣን እርምጃ እንዲወስዱ በቂ መረጃ ቀርቦላቸው እንደነበር፣ በቂ ምክር ተሰጥቷቸው እርሳቸው በመዘናጋታቸው ነው ይህ ሁሉ ጥፋት የደረሰው የሚል ይዘት ያለው ሰፊ ዘገባ ይዞ መውጣቱ ፕሬዝዳንቱን ክፉኛ ሳይረብሻቸው አልቀረም።

ለዚህም ይመስላል ሰፊ ጊዜ ወስደው በጊዜ ሰንጠረዥ ሳይቀር መቼ ምን እንዳደረጉ እስኪሰለች ድረስ ደጋግመው ሲናገሩ የነበረው።

በትናንቱ የጋዜጣዊ መግለጫ መድረክ ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣን በቻሉት አቅም ሁሉ ወርፈውታል። “ቀጣፊ!” ብለውታል።

• ኮሮናቫይረስ ለምን ከ50 ዓመት በላይ የሆኑ ወንዶችን ያጠቃል?

ወረርሽኙን በመከላከሉ ሂደት ስማቸው ገዝፎ የሚነሳው ዶ/ር ፋውቺን ከሥራ ሊያባሯቸው ይችላሉ የሚለው ዜና ከወጣ በኋላ በተደረገው በዚህ ዘለግ ያለ የጋዜጠኞችና የትራምፕ ጥያቄና መልስ ክፍለ ጊዜ ጎልቶ የወጣው ታዲያ የፓውላ ሬይድና የትራምፕ ፍጥጫ ነው።

ፓውላ ሬይድ የሲቢኤስ ጋዜጠኛ ናት። ትናንት ዶናልድ ትራምፕን በጥያቄ ተናንቃቸው ነበር። እርሷን ለመስደብ ያደረሳቸውም ፈታኝ ጥያቄዎቿን ያለማቋረጥ በመሰንዘሯ ነው።

በቂ ሥራ ከጃንዋሪ ወር ጀምሮ ሠርቻለሁ ልወቀስ አይገባም የሚሉትን ትራምፕን በፌብሪዋሪ ወር ምን ሲሰሩ ነበር? በር ለመዝጋት ለምን ዘገዩ? ስትል ጠይቃቸዋለች።

ትራምፕ ነገሩን ቸል ብለው ስለስኬታቸው ማውራት ሲጀምሩ እያቋረጠች ፋታ ነሳቻቸው። ይህ የሁለቱ ምልልስ የሚሊዮኖችን ቀልብ ስቧል። በግርድፉ ይህን ይመስላል።

ትራምፕ፡- “በጃንዋሪ 11 አንድም ታማሚ በአሜሪካ አልነበረም። ይሄ የናንተ ዋሾ ሚዲያ ዝም ብሎ ይቀባጥራል። ‘ኦ… ፕሬዝዳንቱ ቀደም ብሎ ነገሮችን መቆጣጠር ነበረበት’ ይላል። ልንገራችሁ አይደል? እኔ መጀመርያ ነው እርምጃ የወሰድኩት። እርምጃ ፈጥኜ ስወስድ ደግሞ ይቺ ናንሲ ፒሎሲ የምትባል ሴትዮ እና ይሄ እንቅልፋሙ ጆ ባይደን ደርሰው ይተቹኛል።

“…እንዲያውም በአየር መንገዶች ቁጥጥር እንዲደረግ በማድረጌ መጤ ጠል ሲሉኝ ነበር። በጃንዋሪ 21 ነው የመጀመርያው የቫይረሱ ተጠቂ የተገኘው። አንድ ሰው እንኳ አልሞተም። በዚህ ጊዜ ለምን የዓለሙን ትልቁን ኢኮኖሚ አልዘጋህም ነው የምትሉኝ? ምን ነክቷችኋል እናንተ ሰዎች?

“…የዓለምን ቁጥር አንድ ኢኮኖሚ፣ ቻይናን የሚያስከነዳውን ኢኮኖሚ፣ የታላቋን አሜሪካንን ኢኮኖሚ፣ ታላቁን ቀጣሪ ኢኮኖሚ…በዚያ ወቅት ለምን አልዘጋህም ነው የምትይኝ? ደግሞ ትልቅ ኢኮኖሚ የገነባሁት እኔ ነኝ። በጃንዋሪ 31 በዚች ታላቅ አገር አንድ ሰው ሳይሞት ነው በር የዘጋሁት።

• ቻይና ከኮሮናቫይረስ ጋር ያደረገችውን ፍልሚያ በቅርብ የታዘበው ኢትዮጵያዊ ዶክተር

“…ቶሎ በር ስዘጋ ደግሞ እናንተ ሐሳዊ መረጃ ፈልፋዮች የትችት መዓት ታደርሱብኛላችሁ፤ የሚገርም እኮ ነው፤ ስፈቅድም መከራ፣ ስከለክልም መከራ…

“…እንቅልፋሙ ጆ ባይደን ምን አለኝ መሰለቻሁ!? ዘረኛ አለኝ፣ ከቻይና ሰው እንዳይመጣ ስላልኩ እኮ ነው እንዲህ የሚለኝ። ያቺ ፒሎሲ ደግሞ መጤ ጠል አለችኝ። ከዚያ ትንሽ ቆይቶ ባይደን መግለጫ አወጣ፣ ሰው ነው የጻፈለት ለነገሩ። ትራምፕ በር መዝጋቱ ትክክል ነበር ብሎ ጻፈ። እሱ አልጻፈውም፤ ጓደኞቹ ናቸው በሱ ስም የሚጽፉለት።

“…ይሄ ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ የለየለት ቀጣፊ ነው፤ የታወቀ ዋሾ። ፕሬዝዳንት ትራምፕ እርምጃ ለመውሰድ ዘግይቷል ይለኛል ደግሞ…ቀጣፊ። ለነገሩ ስለኔ ካልጻፈ ይዘጋል። አይሸጥለትማ…ማን ገዝቶ ያነባል እሱን…

አሜሪካ የሚገኝ መመርመሪያImage copyrightGETTY IMAGES

ትራምፕ ከዚህ በኋላ መብራቱ እንዲጠፋ አዘዙ፤ ጋዜጠኞቹን ፊልም እንዲመለከቱ ጋበዙ። የተቀነባበረ የቲቪ ምሥል ነው። በምሥሉ ላይ የተለያዩ ሰዎች በተለይም የተለያዩ የአሜሪካ ግዛት ገዢዎች እርሳቸውን ሲያንቆለጳጵሱ ይታያል።

የሚገርመው ይህ ቪዲዮ ሲተላለፍ ትራምፕ ከፊት ለፊት ቆመው ጋዜጠኞቹ በትኩረት እንዲመለከቱት ያበረታቱ ነበር። አንዳንድ ገዢዎች ስለርሳቸው ታላቅነት ሲናገሩም ወደ ጋዜጠኞች እየዞሩ ይጣቀሱ ነበር፤ ከፈገግታ ጋር።

ይህ አጭር ዘጋቢ ፊልም እንዳለቀ አንድ ጋዜጠኛ እጁን አውጥቶ “ክቡር ፕሬዚዳንት! ይህንን የሙገሳ ቪዲዮ ማን አቀነባበረልዎ፤ የምርጫ ዘመቻ ላይ ያሉ ይመስላሉ? ሲል ጠየቃቸው።

ትራምፕ፡-“እኛው ነን የሠራነው፤ በ2 ደቂቃ ነው ያቀናበርነው። ከፈለክ የዚህ ዓይነት ሺ ላሳይህ እችላለሁ”

ጋዜጠኛ፡-“ለምን ያን ማድረግ አስፈለገዎ”

ትራምፕ፡-“ምክንያቱም ቀጣፊ ሚዲያዎች አስቸገራችሁኝ።”

ጋዜጠኛ፡- “በመንግሥት በጀትና በዋይት ሃውስ ሰራተኞች ነው ይህን ቪዲዮ የሚያሰሩት”

ትራምፕ፡- “የተቀናበረ ቪዲዮ አትበለው፤ የሰዎችን ንግግር ነው ቀጣጥለን ያሳየናችሁ.”

ትራምፕ በድጋሚ ስሜታዊ ሆነው መናገር ጀመሩ

“እኔ የምለው፤ እንዴት ነው ማንም ሰው ሳይሞት ማንም ሰው በቫይረሱ ሳይያዝ በታሪክ በዓለም ትልቁን ኢኮኖሚ ለምን አልዘጋህም እያላችሁ የምትወቅሱኝ?

የሲቢኤስ ጋዜጠኛ እጇን አወጣች፡-

“ክቡር ፕሬዝዳንት፣ እርስዎ እየተተቹ ያሉት እኮ እርምጃ ለመውሰድ ጊዜ ገዝተዋል ተብለው ነው። በዚያ በሚሉት ወቅት አልጋ ለማዘጋጀት፣ ሆስፒታል ለመገንባት፣ የምርመራ መሳሪያዎችን ለማዘጋጀት አልተጠቀሙም ነው የተባሉት። በአሁን ሰዓት 20 ሚሊዮን አሜሪካዊያን ሥራ ፈተዋል…ሺዎች ሞተዋል። እርስዎ ነዎት…

ትራምፕ ተቆጡ፡-

“አንቺ አሳፋሪ ጋዜጠኛ ነሽ። ነገሩን ያስቀመጥሽበት መንገድም አሳፋሪ ነው። እስኪ ዝም በይ አንድ ጊዜ…፤ማንም ያላደረገውን አድርጊያለሁ፤ ስላደረኩት…

ጋዜጠኛዋ አቋረጠቻቸው፤

“በጃንዋሪ ሳይሆን በፌብሪዋሪ ምን ሰሩ ነው የተባሉት፤ ሥራ ቢሰሩማ ኖሮ ያ ሁሉ ሰው ባልሞተ…

“ይቅርታ ይቅርታ፣ ራስሽ ዘግበሽዋል እኮ፣ አንድም ሰው አልሞተም፣ አንድም ሰው አልተያዘም፤ እንዴት አገሩን ልዝጋው በዚህ ወቅት…ንገሪኝ…እንዴት ይህን ታላቅ አገር ልዝጋ

ጋዜጠኛዋ አቋረጠቻቸው በድጋሚ፡-

“አሁንም ያልጠየቅዎትን ነው የሚመልሱት፤ በፌብሪዋሪ ምን አደረጉ ነው እያልኩ ያለሁት…”

ትራምፕ፡- “በጣም ብዙ! በጣም ብዙ ነገር ነው ያደረኩት…ምን የላደረኩት አለና…እንዲያውም ዝርዝሩን በጽሑፍ ልሰጥሽ እችላለሁ…

ጋዜጠኛዋ፡- “እሱን አኮ ነው ይንገሩኝ ያልኮት…

ትራምፕ ተናደዱ፤ አንድ ነገር ልንገርሽ ? ቀጣፊ ነሽ፣ አንቺም ያንቺ ሚዲያም ዋሾዎች ናችሁ። እኔን እንደዚያ ከምትጠይቂ ለምን ጆ ባይደን ይቅርታ ጠየቀኝ። ለምን ዲሞክራቶች አደነቁኝ…ቀድሜ እርምጃ ስለወሰድ አይደለም ጆ ባይደን…

ጋዜጠኛዋ በድጋሚ አቋረጠቻቸው፡-

“ስለ ጆ ባይደን ማንም አልጠይቅዎትም ክቡር ፕሬዝዳንት…

ትራምፕ፡- “ቆይኝ ቆይኝ…እንደ አንዳንድ አገሮች በሩን ከፍቼው ብቆይማ ሚሊዮኖች ይረግፉ ነበር፤ ያን አላደረኩም። ቶሎ ብዬ እርምጃ በመውሰዴ የሚሊዮኖችን ሕይወት ታድጊያለሁ። ችግሩ እናንተ ዋሾ ጋዜጠኞች አትዘግቡም። ዋሾ ነሽ…ቀጣፊዎች ናችሁ…ፌክ ኒውስ…

BBC Amharic

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.