የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እና የስራ እድል ፈጠራ መስክ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ለሶስት ወራት ቢቀጥል 1.4 ሚልዮን ስራዎች ስጋት ውስጥ ሊወድቁ እንደሚችሉ የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ገለፀ

ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ቫይረሱ በስራ መስክ ላይ የጋረጠው ችግር ለስድስት ወራት ቢቀጥል ደግሞ 2.1 ሚልዮን ስራዎች ስጋት ውስጥ ይገባሉ።

“ከዚህ በተጨማሪ በውሎ ገብ ስራ የሚተዳደሩ 1.9 ሚልዮን ሰዎች በሶስት ወራት ውስጥ 8 ቢልዮን ብር ገደማ ገቢ ያጣሉ ስለዚህ የሴፍቲ ኔት ድጋፍ ይሻሉ” ብሏል ኮሚሽኑ።

መግለጫው ጉዳዩን ሲያብራራ “ወረርሽኙ በጤና ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እንደፈጠረው ሁሉ ይህ ጫና መልኩን ወደ ስራ እና ማህበራዊ ቀውስነት ሲለውጥ በቀላሉ ሊጎዱ የሚችሉ ቢዝነሶችና ቀጥተኛ ጉዳት የሚያጋጥማቸው ቤተሰቦችን ገቢ በመቀነስ ከፍተኛ የኢኮኖሚ መናጋትን ሊያስከትል ይችላል” ይላል።

ይህ ትንተና አካላዊ ርቀት በማህበረሰቡ በመካከለኛ ደረጃ ቢጠበቅ የሚለውን ከግምት ውስጥ በማስገባት COVID-19 በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተጽዕኖ የሚያሳይ ነው የተባለ ሲሆን በስራ ዕድሎች ላይ ያንዣበበው ስጋት ሊያስከትል በሚችለው የገቢ መቃወስ ላይ ብቻ የሚያተኩር ነው።

በዚህ ሪፖርት ውስጥ የቀረቡ የፖሊሲ አማራጭ ሃሳቦች ያሉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በመንግስት አካላት ውይይት እየተደረገባቸው ያሉና ውሳኔ የሚሰጥባቸው ናቸውም ብሏል ኮሚሽኑ።

(ጋዜጠኛ ኤልያስ መሰረት)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.