የኮረና ቅስፈትና ተዛማጅ ጉዳዮችን በተመለከተ – ይድረስ ለ ዶር አቢይ (ከአባዊርቱ)

ይድረስ ለአቢቹ ለየት ላልከው መሪ
ወገን ያልተረዳህ ምስራች አብሳሪ
አንዳንድ ያልተረዱህ ይሉሃል መሰሪ።

እስቲ የትዝብቴን በግጥም ልግለጸው
መቼስ የስድ-ስዱን አላውቅም እንደሰው
በጭራሽ ይቅርብኝ ወገን አይጭነቀው።

ሀ ብዬ ስጀምር “አንተን” በማለቴ
አንቱታው ይቆየኝ ልንገርህ ካንጀቴ
ከልብ ይቅር በለኝ አቢቹ በሞቴ
እንዲህ ነው ጉዳዩ የዛሬው አርስቴ።

የኮረናና የአቢይ ጉዳይ!

ኮረና እንደገባች በኢትዮጵያችን ምድር
ገና ከጅምሩ ባታደርግ ምክክር
ካሊባባው ንጉስ ከነ ጃክ-ማ ሰፈር
ደሀው ወገናችን ምን ይሆነው ነበር?
ቀላል አልነበረም የጃክ-ማው ድርሻ
ከጭንብል አንስቶ አየር መተንፈሻ
አየር መንገዳችን ሆኖ ማዳረሻ፣
አፍሪካም ቀምሳለች ከዚሁ ካንተው ጉርሻ!!

ድንቅ ነህ አቢቹ ገራገሩ መሪ
ምስጢሩ እንደገባኝ የያንተው በሓሪ
ምን ታርጋ ቢሰጠን “በጭፍን አፍቃሪ” ።
ድንቄም ጭፍኖች ነን አዙረን የማናይ
ድሮን ካውሮጲላ ፈጽሞ የማንለይ።
ነው እኮ ነገሩ እያሉን ያሉቱ
መሆናችን ቀርቶ እድሜ ጠገብ ጎምቱ።

ኸረ ለመሆኑ ምንድነው የቀረህ?
አርቆ አስተዋይ በእድሜ ያልገፋህ
ኖቤል ተሸላሚ ባለ ራእይ መሪ
ሳቂታ ቦረቦር ሲሻህ አስተማሪ
እኮ በል ንገረኝ ምኑን ነው ያልሆንከው
ድንገት የሚያስወቅስ በግልጽ የማላየው?
ዳግም ልጠይቅህ እንዲህ ባደባባይ
በጣም ያሳሰበኝ አለኝ አንድ ጉዳይ።
ካማራው ወገኖች ደጋግሞ ሚነሳ
በብዙ ሚዲያ ጠልቆ የሚወሳ
መቼስ ባላምነውም አጥልቷል ጠባሳ
እውነት ችግር አለህ ከአማራው ጎሳ?
ውሸት ሲደጋገም እውነት እንዳይመስል
እባክህ ተጋፈጥ ይህን ጉዳይ በውል
ቁርጡን ንገርልኝ እንዳልሆንክ “አማር ጠል” ፣
ሁሉም ወገን ይወቅ ይህን ፍርደገምድል፣
ይለፈፍ በይፋ በአማራው ክልል።

እንግዳ ሆነብኝ ባወጣው ባወርደው
ግማሹን ይቻላል ሊጠላ እራሱን ሰው?
ያውም በሚስት /እናት ፍቅር እርር ድብን ላልከው??
እናትስ አርፈዋል አፈር ይቅለላቸው
አማራ-ጠል ያሉህ አይ ዝናሽ ታያቸው
እንዴት ያዩህ ይሆን ስትመለስ እቤት
ሃሜቱን ሲሰሙ ቀዳማይ እመቤት?
ይልቅ ካማራ ጠል ሴንስ የሚሰጥ ለኔ
ያሳየህው ትእግስት ለገዳይ ወያኔ
ከወገን ባላንጣም ጁዋር ሳይቀር ሸኔ
ጠንከር ብለህ ይሆን በተለየ መንገድ ባማራው ወገኔ??
አንተኑ ልጠይቅ አልወድም ኩነኔ፣
ብዬ ደግሞ እንዳልል ሸኔም ተበራይቷል
የነ ዖነግ ጎማም በእጅጉም ተንፍሷል።
እንጅ እንዴት አርጎ በጅምላ ልትጠላ
ይቻልሀል አንተን አማራን በሞላ?

ይልቅ ቅር ካለኝ ለወለድነው ሁላ
በጣም ልብ ሰባሪ ያጣሁለት መላ
ያልተቋጨው ነገር የኒያ ተማሪዎች
ወላጅ ቁርጡን ይወቅ ለጆሮም ባይመች
ተበልተው እንደሆን በሰው መሳይ ጅቦች።

በመጨረሻም!

ሁለቷን አመታት አለፈሀት በሩጫ
ወራቶች ቀርተውት የታሰበው ምርጫ
ብልጽግናው ደርቶ ሞልቶ ፈሶ ዋንጫ
በኮረና ምክንያት ሁሉ በየቤቱ ቀረ በፍጥጫ።
እናም ዛሬ ሳስብ ስላንተ ውለታ
ድንገት ብርታት ቢሆን እንዲሁም ሰላምታ
በርታልን አቢቹ የወገን መከታ
የሚያስወሩብህን አትስማ ላንዳፍታ።
ኮረናን ሸኝተን ወደመጣችበት
ኢትዮጵያ ታድጋለች በሁላችን ህብረት
ብሩህ ቀን ይመጣል እንጠብቅ በትእግስት
ያባይ ግድብ ያልቃል የኢትዮጵያ አጽመርስት።

ይህ የኔ ደብዳቤ አየር ላይ እያለ
ዲጂታሎች ካዩት መቼስ ሀፍረት የለ
ስድ-ስዱ ላይሆነኝ ከላይ እንዳልኩቱ
ቃልኪዳን አለብኝ ኤታማዦር ዊርቱ።

ለማጠቃለያ በጸሎት ልጨርስ
ኮረናን ካገሬ ፈጣሪ ይደምስስ
አንተንም ክርስቶስ በእጆቹ ያብስ
በቃችሁ ይበለን በጠፋው ሁሉ ነፍስ።

ሚያዝያ 2012, ዘመነ ምህላ

2 COMMENTS

 1. አባዊርቱ የዋርካው የሳይበር ዘመዴ
  እንዴት ነህ ባያሌው ልጠይቅህ ጓዴ
  በዚህ ዘመን ህዝብን መምከር በዘዴ
  እኔም እንዳንተ ከትባለሁኝ አንዳንዴ
  ይህን መድረክ ያዘጋጁ ወገኖቼን አመሰግናለሁ
  ለሃገራችን መልካም ራእይ ያሳየ መሪ አከብራለሁ
  ከነቃፊ ስህተት ፈላጌ እንደልሜዴ እርቃለሁ
  አንተን የመሰሉ ሀገርወዳዶችን ከልቤ አደንቃለሁ
  የጠራህው ጌታ ኢትዮጵያን እንዲባርክ እጸልያለሁ
  ዲጎኔ ሞረቴው

 2. ለአባ የዊርቱ የጫላ ምትክ፣
  አይይይ አባዊርቱ፣ጥፋታችሁ ለካ በደንብ ገብቷችዃል
  በክርስቶስ እጅም መዳሰስ አምሮሃል።
  ክርስቶስም ቢሆን ሁሌም መሐሪ ነው
  ንሥሐና ፀፀት እሱም ሲገባ ነው።
  እናትና ሚስቱ ቢባሉም አማራ
  ከሐዲ መሰሪ ተብሎ አልቆለታል ሐገር አያጋራ።
  ድሮውንም ቢሆን እናቱን የተወ ፣መመለሻ የለው ሀገሪን ለመክዳት
  ይብላኝ ላንተ ደሞ ለምታመልከው ፣ ህዝብ በጊዜው በፍትህ ሲበይንበት።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.