“የራስን ጥሎ የሰው አንጠልጥሎ” ሆነብን እሳ ነገሩ ሁላ – [ ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ ]

አንዳንድ ጊዜ በጣም ግርም ሲለን ጣል የምናደርጋት ምርጥ ሀገርኛ አባባል አለችን፣ እሷም የራስን ጥሎ የሰው አንጠልጥሎ ትሰኛለች፣ ከሳምንታት በፊት በአራት ኪሎ ቤተ መንግስት ፊት ለፊት ወደ መስቀል አደባባይ ሳልፍ ይህችን ፒኮክ የምትባል እንሰሳ ምስል በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ምዕራባዊ መግቢያ ላይ ደስ የሚል ሀውልት ተሰርቶላት የመግቢያው ጌጥ እንደትሆንም ተደርጋ አየኋት፡፡

ይኸ ምን ማለት ነው፣ ይህች እንስሳት በአገራችን ትገኛለች እንዴ፣ የምትገኝ ከሆነስ በየትኛው የሀገራችን አካባቢ በማለት ከአጠገቤ የነበረውን ሰው ብጠይቀውም አይ አይመስለኝም ብሎ ስለመለሰለኝ እርግጠኛ መሆን አልቻልሁም ነበር፡፡ ከዛም ባለፈው ሳምንት ለስራ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ መግባት ነበረብኝና በዚሁ በር እንድገባ ተነግሮኝ ስገባ የፒኮኳ ነገር እኔንም በእጅጉ አስገረመኝ፡፡

ነገር ግን በቦታው ያገኘኋቸው ሰዎች የእኔ ቢጤ የህግና ተያያዥ ሞያ ባለቤቶች እንጂ የእንስሳት ሳይንስ ዕውቀት የዘለቃቸው ስላልነበሩና የዚህ አይነት ነገር አንስተን ለማውራትም ጊዜው ስላልነበረን ጉዳዩን ለማንም ሰው ሳላነሳ ተመለስሁ፡፡ ሰሞኑን ግን በዚሁ የፌስ ቡክ መንደር ላይ ይኸው የፒኮክ ምስለ ሀውልት የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ አገኘሁትና ጽሁፎቹን አለፍ አለፍ ብየ ሳነብ እንዳውም በአገራችን የማትገኝ እንስሳት እንደሆነች መረጃ አገኘሁ፡፡

በዚህም ምነው ግን አሁን በአገራችን ብርቅየ እንስሳት ጠፍቶ ነው እሷ የተመረጠችው? የሚል ጥያቄም እንዳነሳ አደረገን፣ ደግሞ እኮ የተቀመጠችበት ቦታ ከሰሜን አቅጣጫ ከአራት ኪሎ አደባባይና ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወጥትህ ቁልቁል በሚወረድበት ዋና አስፋልት መንገድና ከምዕራብ አቅጣጫ ደግሞ ከፒያሳ ተንደርድረህ ወደ አቧሬ አደባባይ ስትመጣ ፊት ለፊት ላይ በግልጽ የሚታይ መሆኑ ይበልጥ ትኩረትን እንዲስብና መነጋገሪያም እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

ይሁን መቼም በዚህ ወቅት የምኒልክ ድኩላም ሆነ በሀገራችን ብቻ የሚገኘው ጥቁር አንበሳ በአንዳንድ የብሔር ፖለቲካ አራማጆች ዘንድ የአማራ ገዥዎች ምልክት ተደርገው ስለሚታዩ (ድኩላው በምኒልክ ስለተሰየመና አንበሳው ደግሞ በአጼ ኃይለስላሴ የተለየ ክብር ስለተሰጠው፣ በአጠቃላይም የመንግስታቸው ስያሜ ሞዓ አንበሳ ዘ እምነገደ ይሁዳ ይባል ስለነበረ) በዚያ በር ላይ ሀውልት እንዲሰራላቸው መጠበቅ ባይቻልም እነ ቀይይ ቀበሮ፣ ዋሊያ አይቤክስና ጭላዳ ዝንጀሮ በአማራጭነት ቀርበው ለመወዳደር ብቁ አልሆን ብለው ይሆን? ነው ወይስ እነሱም በአማራ ክልል ስለሚገኙ?

የእኛ አገር ፖለቲካ ምን ያህል ግራ የገባውና በእጅጉ የዘቀጠ መሆኑን የምታየው እንዲህ አይነቱን ለራስ ማንነትና ብርቅየ የተፈጥሮ ሀብት ተገቢውን ክብር ከመስጠትና በእንክብካቤ ከመያዝ ይልቅ አንድም የውጭ ነገር አድናቂ በመሆን፣ አሊያም ከሀሜትና ትችት ለማምለጥ ሲባል መሰረታዊ የሆነ ስህተት እንድትሰራ ያደርግሀል፡፡

እውነት ነው የምላችሁ ይህንን ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድም ሆኑ ምክትላቸው አቶ ደመቀ መኮንን ይህንን እውነታ እያወቁ ከሆነ የተሰራው እጅግ አድርጌ አዝንባቸዋለሁ ብቻ ሳይሆን አፍርባቸዋለሁም፡፡ ሆኖም ዶ/ር አብይ ከእንስሳት ሳይንስ ጋር ያላቸውን ቅርበት ባላውቅም አቶ ደመቀ መኮንን ግን የባዮሎጂ መምህር ስለነበሩ የዚህ ነገር ትርጉም ይሰወርባቸዋል ብየ ለማመን ይቸግረኛልና አሁም ከተቻለ ቢስተካከል መልካም ነው እላለሁ፡፡

[ ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ ]

4 COMMENTS

  1. በዉነቱ የተመረጠችው ፒኮክ ያላት ተፈጥሯዊ ባሕሬዋ ከሀገር ዊ አመለካከት ጋር ተያያዥነት ያለው ትርጉም ከመረጧት መሪዎችን መልስ ይሰጠን፡፡

  2. እኔው ደግሞ በርስዎ ነው ያፈርኩት ዶር ሲሳይ። የህግ ሰው መሰሉኝ ከአጻጻፍዎ።ዛሬ እንደገና ቪኦኤ ስሰማ አየር መንገዳችን፣ የአይን ብሌናችን ምን አይነት ችግር ውስጥ እንዳለሁ ተረዳሁ። የአገራችን ምሁራን ምን ይሆን ያገኛችሁ? እስቲ እንዲህ አይነት እንኳንስ የደህዩ አገራትን ቀርቶ ሀያላንን አስቤዛ ቆጠራ እያስገባ ያለው በሽታ ሰውን እያረገፈ፣ ገና ምኑ ቅጡ በአገራችን ላይ የሚጥለው መጥፎ ጥላ ሳይለይ ፣ ስለቤተ መንግስት ድንጋይ ላይ ስለተሳለች ወፍ በምሬት አጀንዳ ይከፍታሉ? ምናለ እንዲህ አይነቱ ጥያቄ ወይም ትችት እስከ ምርጫው እንኳን ቢቆየን? እነ ገዱና አቢይ ህዝባችንን ምን እናበላው ይሆን? ይህ ኮሮና እስከ ክረምት ከዘለቀ ምን ይውጠን ይሆን እያሉ ይበሉ ወይስ ለንዲህ አይነት የቅንጦት ክስ መልስ ይስጡ? እስቲ የአሜሪካው አየር መንገዳችን ተጠሪ በዛሬው ቪኦኤ የሚሉትን ይስሙና ይመኑኝ ሃሳብዎን ይቀይራሉ። ከባድ ፈተና እየመጣ ነው በተለየ ሁኔታ በታዳጊ ሀገራት ላይ።

  3. አይ አባዎርቱ፣ አሳፋሪስ አንተው ነህ። መላው የሸዋ ኦሮሞ ለዚህ መሪ ያለህ አምልኮና ማጎብደድ ተሸማቆብሃል። በሽታውን በጋራ መቋቋም ልክ ነው የሁሉም ግዳጅ ነው።ከህዝቡ በፊት ገዢ ነኝ የሚለው ትልቅ ሃላፊነት ማሳየትና ምሳሌ መሆን ሲገባው ፣ግርግር ከዘራፊዎች ያመቻል እንደሚባለው የአብይ መንግሥት ቅርስ ማጥፋትና ወረራውን በመጣደፍ ይዘውታል።
    ወረርሺኝ ስለገባ ሌላው የቀን ተቀን የህዝብ ኑሮ አይካሄድም ብለህ ካሰብክ የማስተዋል ግድፈት አለብህ።በዚህ ችግር ጊዜ እንደምናዪው የፓለቲካው ሂደት አልቀነሰም በአንፃሩ ግን ኢኮኖሚው አሽቆልቁሏል ።መጀመሪያውኑ አርኪ መሰረት ያልጣለ ስነስርዓት ፣በችግር ጊዜ ውድቀትን ለመሸፈን በሌላ ስኬትም ይዋዥቃል። በሀገራችን አስከፊው ግን ተረኛ ነን የሚሉት የጎሳ ወገኖችህ ጊዜውን እንኳን በማገናዘብ አደብ አልገዙም።ምክንያት እያንጋጉ ጊዜው አሁን አይደለም በማለት ሌላውን አዘናግቶ ውስጥ ውስጡን የራስን ሕልም ለማሳካት መሞከር ተራ አጭበርባሪነት ነው። ቅልም በጊዜዋ አለት ለመፈርከስ ዳዳ ይላታል፣ሐቁ በኋላ ተከስክሳ ራስ ምታቷ ነው።
    በመሪ መመካት ጥሩ ነው ግን ጭፍን አምልኮት የትንሽነት ስብዕና ነው።

  4. አይ ዶክተር ይገርማል ፒኮክ አገራችን ውስጥ የምትገኝ የአእዋፍ ዝርያ ትሁን አትሁን ለማወቅ የስነ ሒይወት ሊቅ መሖን አይጠበቅብህም ድንቄም ዶክተር 😂😂😂😂 አቶእስኪ ከእንደዚሕ አይነት ትርኺ ምርኺ እና እንቶ ፈንቶ ከሆነ ነገር ወጥተን ህዝብ ሊጠቅም የሚችል ነገር ላይ ብናተኩር ለምን እንደሆነ ባይገባኝም የኢትዮጽያ ምሁራን ተብዬዎች ዶክተርና ኢንጂነር ከተባሉ ዘለው የፓለቲካ ቅርቃር መግባት ይወዳሉ ምእራብያውያን አገራት ግን ዶክተርና ኢንጂነር ብዙም ፓለቲካ ውስጥ አይታዪም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.