ህዝብ በስፋት በሚገኝባቸው ቦታዎች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ሳይጠቀሙና እርቀታቸውን ባልጠባቁ 1305 ሰዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የኮሮና ቫይርስ (ኮቪድ-19) ለመከላከል የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት በማድረግ ባደረገው ቁጥጥር ህዝብ በስፋት በሚገኝባቸው ቦታዎች ላይ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ሳይጠቀሙ በተገኙ እና እርቀታቸውን ባልጠባቁ 1305 ሰዎች ላይ በአዋጁ መሰረት እርምጃ መውሰዱን ገለፀ፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ በብዛት በሚንቀሳቀስባቸው 23 ስፍራዎች ግንቦት 5 ቀን 2012 ዓ/ም ባደረገው ቁጥጥር የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ያልተጠቀሙ እና እርቀታቸውን ያልጠበቁ 990 ወንዶችና 315 ሴቶች በድምሩ 1305 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል፡፡

በቂርቆስ፣በአራዳ፣በጉለሌ፣በአዲስ ከተማ እና በየካ ክፍለ ከተሞች በተመረጡ ስፍራዎች ቁጥጥሩ የተደረገ ሲሆን መሳለሚያ እህል በረንዳ፣አውቶቢስ ተራ፣ሰባተኛ፣ጃንሜዳ አትክልት ተራ፣አዲሱ ገበያ፣ካዛንቺስ፣ሽሮ ሜዳ፣ፒያሳ ጊዮርጊስ አካባቢ ቁጥጥር ከተደረገባቸው ስፍራዎች መካከል ይገኙበታል፡፡

መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት ህብረተሰቡ እራሱንና ቤተሰቡን ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠበቅ የግንዛቤ ማስጨበጫ ልዩ ልዩ ስራዎችን ትኩረት ሰጥተው ቢሰሩም በርካታ ሰዎች ለጉዳዩ ተገቢ ትኩረት ሳይ ሰጡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተደነገገውን ማስክ የመጠቀም እና እርቀትን የመጠበቅ ግዴታዎችን በመተላለፍ ግብይት ሲፈፅሙና ሲንቀሳቀሱ የሚስተዋል በመሆኑ በቫይረሱ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል እንዲረዳና በተለይ ደግሞ ለማህበረሰቡ ጥቅም ሲባል አዋጁን መሰረት በማድረግ ፖሊስ እርምጃ ለመውሰድ መገደዱን የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል መከላከል ኃላፊ ኮማንደር ጉማታው ገዳሙ ገልፀዋል፡፡

በቁጥጥሩ ወቅት ተይዘው ከነበሩ ግለሰቦች መካከል ፖሊስ የኮሮና ቫይርስ ስርጭት ለመከላከልና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣውን የስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስከበር የሚያደርገው ቁጥጥር ተገቢ መሆኑንና ተጠናክሮ መቀጠል እንደለበት አስተያዬታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በአንድ ቦታ ተሰባስበው ሺሻ ሲያስጨሱና ጫት ሲያስቅሙ በነበሩ፣ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ፣ ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ ዘይትና ስኳር በህገ ወጥ መንገድ ባከማቹ እና የንፅህና መጠበቂያዎችን አስመስለው ሲሰሩ በተገኙ ግለሰቦች፤በአዋጁ ከተደነገገው ውጪ ከታሪፍ በላይ ባስከፈሉ፣ትርፍ ሰው ጭነው በተገኙ እና ኮድ ሁለት ሆነው ከተፈቀደላቸው ቀን ውጪ ሲንቀሳቀሱ በተገኙ አሽከርካሪዎች ላይ ህግን መሰረት በማድረግ እርምጃ መወሰዱ ይታወቃል፡፡

በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ በመሆኑ በተለይ ሰው በሚበዛባቸው አካባቢዎች እርቀታቸውን በማይጠብቁ ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ በማይጠቀሙ፣ከታሪፍ በላይ በሚያስከፍሉ እና ትርፍ ሰው በሚጭኑ አሽከርካሪዎች እንዲሁም በልዩ ልዩ ሁኔታ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በሚተላለፉ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ላይ ቁጥጥሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ደመና ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡

የቫይረሱን አስከፊነትና አሳሳቢነት ህብረተሰቡ፣የንግድ ተቋማት ባለቤቶችና ሰራተኞች ተገንዝበው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አሳስቧል፡፡

(ኢፕድ)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.