በሽግግሩ ዙሪያ ላለው ውዝግብ አስታራቂ የመፍትሄ ሐሳብ – ግርማ ካሳ

በፕሮፌሰር በየነ የሚመራው ፣ ኢሶዴፓ፣ ኢዜማ፣ አብን ፣ በአቶ ዳዎድ የሚመራው ኦነግን፣ የኦጋዴን ነጻ አውጭ ግንባርን ፣ የሞጫ ና የአገው ሸንጎን ያቀፈው ትብብር፣ ዶር አብይ አህመድ ምርጫው እስኪደረግ ድረስ ቢቆዩ ችግር እንደሌለባቸው ገለጸዋል፡፡ ሲደመሩ ሰባት ደርጅቶች፡፡ እነዚህ ድርጅቶች የዶር አብይ መስተዳደር እንዲቀጥል ቢጠይቁም አንዳንዶቹ መጭው ምርጫ ሰላማዊ ፍታሃዊን ነጻ እንዲሆኑ የሚረዱ ክሚሽኖች እንዲቋቋሙ፣ ሌሎች ደግሞ ችግሩ ሕግ መንግስቱ ራሱ ስለሆነ ሕግ መንግስቱን የማሻሻል ሂደቶች እንዲጀመሩ ጠይቀዋል።

በአንጻሩ ኢዴፓና ሕብር የሽግግር መንግስት፣ አረና/ኦፌኮ/ሲሃንና መኢአድ የብሄራዊ አንድነት መንግስት፣ ባልደራስ ደግሞ የባለሞያዎች መንግስት ይቋቋም የሚል አቋም ይዘዋል፡፡በአጠቃልይ ስድስት ድርጅቶች፡፡

ኢዴፓዎች ምንም እንኳን የሽግግር መንግስት ይቋቋም የሚል አቋም ቢይዙም፣ በሽግግሩ መንግስት ግን ዶር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆነው እንዲቀጥሉ ነው ፍላጎት ያላቸው፡፡ “እኛ ሀሳባችን ይሄ ነው፤ ያ ማለት ግን የሌሎችን አንቀበልም ማለት አይደለም፣ እንነጋገር” ሲሉ ፣ በገዢው ፓርቲና በተቃዋሚዎች መካከል ንግግር እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከዚህ የምንማረው የኢዴፓም አቋም በተወሰነ መልኩ ከነአብንና ኢዜማ ጋር የሚመሳሰል መሆኑ ነው፡፡

ባልደራስ ያቀረበው ሐሳብ፣ በመርህ ደረጃ የሚስብ ቢመስልም፣ተግባራዊ ሊሆን የመቻሉ ጉዳይ ላይ ግን አጠያያቂ ነው፡፡በርግጥ ኢትዮጵያ፣ ለአገር አይደለም ለአህጉር ብሎም ለአለም የሚበቁ ምህራን ያሏት አገር ናት፡፡ የምሁር ድሃ አይደለችም፡፡ አገር በበማለሞያዎች ብትመራ ደግሞ የበለጠ ታድጋለች፡፡ ሆኖም ግን ይሄን የባለሞያዎች መንግስት በአጭር ጊዜ በማሰባሰቡ አንጻር ያለውን ዉስብስበነት በማየት የባልደራስ ሐሳብ ተግብራዊ የመሆን እድሉ በጣም ትንሽ ነው፡፡በመሆኑም ባልደራስ የአቋም ማሸጋሸግ በማድረግ ከነ ኢዜማና አብን ጋር ቢቀራረብ የተሻለ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ዶር አብይ ጠቅላይ ሚኒስቴር እንዲሆኑ በመደገፍ፣ ካቢኒያቸውን በሚያዋቅሩበት ጊዜ ግን፣ ባለሞያዎች የካቢኔ አባላት እንዲሆኑ ሐሳብ መስጠት ይቻላል፡፡ ሲቪል ኢንጂነሯን ወ/ሮ አይሻን የመከላከያ ሚኒስቴር አድርገው እንደነበረው አይነት መሆን የለበትም፡፡ ወታደርን የትራንስፖርት ሚኒስቴር ማድረግ፣ እንግሊዘኛ ወይም የዉጭ ቋንቋ በደንብ ተናግሮ ማሳመን የማይችልን ሰው የዉጭ ጉዳይ ማድረግ አይነት አሰራሮች መስተካከል አለባቸው፡፡ በካቢኔ የሚመደቡ የብልጽግና ሆነ የሌሎች ድርጅቶች አባላት ሊሆኑ ወይም ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ትግሬ፣ ኦሮሞ ወይም ከዚህ ጎሳ ወይ ከዚያ ጎሳ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ግን ባለሞያዎች መሆን አለባቸው፡፡ የካቢኔ ቦታ ላይ የሚቀመጡ መስፈርቱ የገዢው ፓርቲ አባል መሆናቸው ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ብቃት ነው መታየት ያለበት፡፡

ለዚህ ደግሞ ትልቅ ትምህርት ከአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ መውሰድ ይቻላል፡፡በአማራ ክልል በኢሕአዴግ አሰራር ያልተለመደ ስራ ነው የተሰራው፡፡ በልማትና ጥናት (development studies) ፒኤችዲያቸውን በሄግ ኔዘርላንድ ያገኙትና በአዲስ አበባ ምሁርና ተመራማሪ የነበሩ፣ የብልጽግና ፓርቲ አባል ያልሆኑ ዶር ፈንታ ፣የክልሉ ም/ርእሰ መስተዳደር ሆነው ክልሉን በብቃት እያገለገሉ ነው፡፡

በዚህ ፈታኝ ወቅት ዶር አብይ በአማራ ክልል ብልጽግና ቅርንጫ ያደረገውን ተመክሮ በመውሰድ፣ ካቢኔውን በብቃትና በሞያ ላይ የተመሰረተ የአንድነት ካቤኔ ያደርጉ ዘንድ አበረታታለሁ፡፡ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ፣ ዶር ዳንኤል በቀለን የሰብአዊ ኮሚሽን ኮሚሽነር አድርጎ የሾሙት ዶ/ር አብይ ፣ ምን አልባትም ከኢሕአዴግ ጊዜ ጀመሮ ተከትሎ የመጡ አሁን በአስተሳሰብ ያልተለወጡ የብልጽግና አመራሮች ካላስቸገሯቸው በቀር፣ ካቢኔዉን የባለሞያዎች ስብስብ የማድረግ ችግር ይኖረቸዋል የሚል ሐሳብ የለኝም፡፡

የጎሳ ወይንም፣ የብሄር ብሄረሰብና ሕዝብ የሚሉት ኮታ መኖርም የለበትም፡፡ ዘርን ሃላፊነቶችን ለመያዝ መመዘኛ ማድረግ የኃላ ቀርነት ነው፡፡እርግጥ ነው አሁን ባለው የዘር ፖለቲካ እብደት፣ ብዙ አማራ ካቢኔ ውስጥ ከሌለ፣ ካቢኔው ውስጥ አማራ በመብዛቱ አማራው የሚጠቀም ይመስል፣ የአማራ ብሄረተኞች ሊጮኹ ይችላሉ፡፡ ኦሮሞም ብዙ ከሌለ “ኦሮሞ ተገለለ፣ አብይ የኦሮሞ ጠላት ነው” መባሉ አይቀርም፣ እንደነ ጃዋርና በቀለ ገርባ ባሉት፡፡፡ግን ለኦሮሞ የሚጠቅመው ኦሮሞ ስልጣን መያዙ ሳይሆን ማንም ስልጣን ያዘ ማንም፣ የኦሮሞ መሰረታዊ የሰላም፣ የፍትሕ የልማት ጥያቄዎችን ያሟላል ወይ የሚለው ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.