ጠያቂና ተጠያቂ ያጣው የሕዝብ ልጆች ጉዳይ !!! መንግሥት ተግባሩ ምንድን ነው ? – ከድሉ ዘገዬ

ከዘመናዊ መንግስት ተግባራት ውስጥ ሥርዓትን ማስጠበቅ፣ ፍትህ ማስፈንና የሲቪል መብቶች ጥበቃ ዋናዎቹ ናቸው። ታዲያ ዶክተር አብይ አህመድ የሚመሩት መንግሥት

በሚያስተዳድራት ኢትዮጵያ ውስጥ ለ <<<<<<<ያክል ጊዜ ዱካቸው ሳይገኝና በህይወት መኖር አለ መኖራቸው ሳይታወቅ የቀሩ እህቶቻችንን ጉዳይ ስራዬ ብሎ ያልያዘ ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሌለው መንግሥት ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው ብሎ መናገር በፍጹም አይቻልም ።

እነኚህ ልጆች ለፖለቲካ ፍጆታ ተብሎ በፌድራሉ ወይንም በክልሉ መንግሥት የጦስ ዶሮ ካልሆኑ በቀር እስካሁን ድረስ በሌላ አካል በአገር ውስጥ የተፈጸመ ውብድና መንግሥትን ከሚያክል የሕዝብንና የሀገርን ጸጥታና ድህንንት ለማስጠበቅ አቅም ካለው አካል ቁጥጥር ውጭ ሆኖ ነው ብሎ ማመን አይቻልም ። ትልቁ እንቆቅልሽ ደግሞ የአማራን ሕዝብ እወክለዋለሁ የሚለው በአቶ ደመቀ መኮንን የሚመራው የአማራ ክልላዊ መንግሥት ዘወትር ማንም የሚጋልበው ባለቤት አልባ ፈረስ መሆኑ ነው ። ይባስ ብለው የሕዝቡ ጩሄት ሲበረታ በራሱ በደመቀ የሚመራ አፈላላጊ

ኮሚቴ አቋቋምን ብለው እርሱንም የአማራንም ሕዝብ መቀለጃ ማድረጋቸው ነው ። አቶ ደመቀ መኮንን ደንዳና ጫንቃ ካላቸውና ፍላጎታቸው ከሆነ እንደ በሬ ተጠምደው ሊታረሱ ይችላሉ ነገር ግን በአማራ ሕዝብ ስምና ደም የመቀለድ መብት የላቸውም። አቅም አንሷቸው ከሆነም ስልጣናቸውን መልቀቅ አለባቸው እንጂ እንደ አሻንጉሊት የማንም መጫወቻ መሆን ያለባቸው አይመስለኝም።

ተማሪዎችን ማን አገታቸው ? ለምንስ ዓላማ ?

በተለምዶ እንደምናውቀው እገታ የሚያደርግ ግለሰብ ወይንም ቡድን የፖለቲካ ወይንም የኢኮኖሚ ጥቅሙን አስገድዶ ለማስፈጸም ወይንም እውቅናን ለማግኘት ብሎ ነው ። ተማሪዎቹን ለእነዚህ ጥቅሞች ብሎ አማጺ አግቷቸው ቢሆን ኖሮ ገሎም ከሆነ የገደለበትን በህይወት ካሉም በቁጥጥሩ ስር እንዳሉ ገልጾ የሚፈልገውን ማግኘት ወይንም ለማግኘት እስካሁን የመደራደርያ ጥያቄውን ማቅረብ ነበረበት ። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ በአማጺ ታግተዋል የሚለው ፈጽሞ ውሸት ነው ። አማጺ የሚባለው ሸኔ የሚታገለው ኦሮሚያ የሚትባል አገር ለመመስረት ስልጣንን ከጨበጠው የዶክተር አብይ መግሥት ጋር እንጂ በፖለቲካ ውስጥ ምንም ተሳትፎ ከሌላቸው ተማሪዎች ወይንም ሥልጣን ካልጨበጠው ከተወለዱበት ጎሳ ጋር ሊሆን አይችልም ። ደርጊቱን የፈጸመው ማንም ይሁን ማን ከላይ ለጠቀስኩት ዓላማ ቢሆን ኖሮ መርጦ ሊያግት አይችልም ። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በአማራ ክልል የኦሮሞ ልጅ ተገደለ ብሎ ያዙኝ ሊቀቁኝ ሲል የነበረ በሚያስተዳድረው ክልል የተፈጸመውን እገታ ሙሉ በሙሉ ለማውገዝ ገት ባይኖረው እንኳን ለይምሰል መግለጫ ለማውጣት አለመፈለጉ በራሱ በድርጊቱ እጃቸው እንዳለበት ያሳብቃል ።

የታገቱት ለምን የአንድ ጎሣ አባላት ሆኑ ?

እንደተባለው አጋቹ አካል ለገንዘብ ብሎ ውይንም እውቅናን ለማግኘት ብሎ የፈጸመው ቢሆን ኖሮ የአማራ ተወላጆችን ብቻ መርጦ አያግትም ስለሆነም እገታው የተፈጸመው አማራ ጠል በሆኑ የኦሮሞ ጽንፈኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ፣ በህጋዊና በህገወጥ ተደራጅተው በሚንቀሳቀሱ አካላት የጋራ ቅንብር ነው። ይህ ባይሆን ኖሮ የኦሮሞ ተወላጆችንም ባገቱ ነበር ። ለፖለቲካ ፍጆታ ወይንም ለስልጣንም ከሆነ አማራው አገር እየመራ አይደለም ፣ እየመሩ ያሉት እነርሱ ራሳቸው በመሆኑ መርጠው ወንጀል እንዲፈጽሙ የሚያስገድድ አመክኒዮ አይታየኝም ።

መንግሥትን ፣ እርስ በርሳችሁና ራሳቸሁን በራሳችሁ የሚትቃወሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህ ጉዳይ አይመለከታችሁም ?

እባብ አርጅቶ ቆዳውን ቢገፍ እባብነቱ አይቀርም እህአዴግ ስሙን ቀይሮ ብልጽግና ስላለ ሌላ ሊሆን አይችልም ። ከ97 ምርጫ ማግስት አቶ መለሰ ዜናዊ ራሱንና ድርጅቱን የታደገው የቤት ውስጥ አድማውን ለማስቀረት ከሰማይ በታች ከምድር በላይ የማንወያይበት ጉዳይ የለም ብሎ አሞኝቶ ነው ሁሉንም ለቃቅሞ ከርቼሌ የከተተው ። የመፎካከሪያ ሜዳ በለለበት አገር ተፎካካሪ ፓርቲዎች አልላችሁም ። መንግሥትን ፣ እርስበርሳችሁና ራሳችሁን በራሳችሁ የሚትቃወሙ እንደ እንጉዳይ የፈላችሁ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዋች ሆይ እባካችሁ እንደ ህጻን ልጅ በእባብ ሁለቴ እስከምትነከሱ አትጠብቁ ። ለጽድቅ ብላችሁ የተደራጃችሁ ፓርቲዎችም ካላችሁ (የምንታገለው ለስልጣን አይደለም ለሚሉ ፓርቲዎች)ይህ ቦታው አይደለምና ለሥልጣን ታገሉ አለዚያ አላማችሁን ከግቡ ማድረስ አትችሉም ። ሊወድቅ ያዘመመን ቤት በእጅ ደግፋችሁ ማቆየት አትችሉም እጃቺሁ ሲዝል እላያችሁ ላይ እንዳይወድቅ እሰጋለሁ ። ጨው ለራሱ ሲል ይጣፍት አለዚያ እንደ ድንጋይ ይወረወራል ። ብልጣብልጥነትና የሴራ ፖለቲካ ሩቅ ስለማያስኬድ በመሪህ መመራት ይበጃል ። በተለይ ኢዜማዎች ዎዶገባነት አያዋጣም ፤ ውስጣችሁን መርምሩ ችግር ካለ ራሳችሁን አጽዱ ፤ ፖለቲካና ይሉኝታ አብረው አይሄዱም ። ከገዥው ፓርቲ ጋር ወዳችሁ ከተለጠፋቺሁ በኋላ መነጫነጩ ዋጋ የለውም ሳይረፍድ ንቁ ።

በማጠቃለያዬ በኢትዮጵያዊነቱ ለማይደራደረው ወገኔ ማስተላለፍ የምፈልገው እነዚ ንጹኃን እህቶቻችን በሕይወት ካሉ እስከሚለቀቁ ተገድለውም ከሆነ እውነቱ እስከሚነገርን ድረስ ምንም አይነት ሕዝባዊም ሆነ አገራዊ ችግር ሳያዘናጋን መታገል እንዳለብን ነው ።

ፈጣሪ ሕዝባችንና አግራችንን ይጠብቅልን

ከድሉ ዘገዬ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.