ለቸኮለ! የዛሬ ዐርብ ግንቦት 14/2012 የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1. በ24 ሰዓት ምርመራ 30 ሰዎች ኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው ጤና ሚንስቴር በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡ 18ቱ ከአዲስ አበባ፣ 3ቱ ከአፋር፣ 4ቱ ከኦሮሚያ፣ 3ቱ ከትግራይ እና 2ቱ ድንበር አቋራጭ ሹፌሮች ናቸው፡፡

2. የሱማሌ ክልል ምክር ቤት ቀደም ሲል የሥራ መልቀቂያቸው ሳይጸድቅላቸው በተሰናበቱት አፈ ጉባዔ ምትክ ሌላ አፈ ጉባዔ ሳይመረጥ ዛሬ ጉባዔውን እንዳጠናቀቀ ኢትዮጵያን ኢንሳይደር ዘግቧል፡፡ ምክር ቤቱ ትናንት የ12 አባላቱን ያለመከሰስ መብት አንስቷል፡፡ የተወሰኑ አባላት በም/ፕሬዝዳንት ሙስጠፋ ላይ የመተማመኛ ድምጽ ለመስጠት አጀንዳ ይያዝልን በማለታቸው ትናንት ውዝግብ ተፈጥሮ ነበር፡፡

3. በአማራ ክልል በ25 ወረዳዎች የወባ ወረርሽኝ እንደተከሰተ የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ተቋምን ጠቅሶ DW ዘግቧል፡፡ በሽታው ወደ ወረርሽኝ ለመቀየሩ ምክንያቶቹ፣ ኅብረተሰቡ በሽታውን ለመከላከል ያለው አቅም ዝቀተኛነት፣ የኮሮና ወረርሽኝ መከሰት፣ የኬሚካል ዕጥረት እና የጤና ባለሙያዎች ቸልተኝነት ናቸው፡፡

4. ሚንስትሮች ምክር ቤት ጤና ሚንስቴር ለጤና ባለሙያዎች ማበረታቻ ያቀረበውን የአበል ክፍያ ረቂቅ መመሪያ እንዳጸደቀ ከጠ/ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ፌስቡክ ገጽ ተመልክተናል፡፡ የአበል ማበረታቻው ያስፈለገው፣ ጤና ባለሙያዎች ኮሮና ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ግንባር ቀደም አስተዋጽዖ እያደገሩ ስለሆነ ነው፡፡

5. የሚንስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ለ2012 ዓ.ም በጀት ዐመት የተዘጋጀ የተጨማሪ በጀት ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤ እንደመራ ከጠ/ሚንስትር ፌስቡክ ገጽ ተመልክተናል፡፡ ለሕዝብ ጥቅም ከመሬታቸው ለሚነሱ ዜጎች ለሚከፈለው ካሳ እና ተነሽዎቹ መልሰው ለሚቋቋሙበት ሥርዓት የተዘጋጀውን ረቂቅ ደንብም አጽድቋል፡፡

6. ግብጽ በሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ላይ ወደ ድርድር እንደምትመለስ ማስታወቋን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ ግብጽ አቋሟን ያሳወቀችው፣ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚንስትር ሐምዶክ እና ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ትናንት የሦስትዮሽ ድርድሩን እንደገና ለመቀጠል መስማማታቸውን ካስታወቁ በኋላ ነው።

7. በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከሥራ ውጭ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን የቤት ሠራተኞችን ከሊባኖስ ወደ ሀገራቸው ለማጓጓዝ የታሰበው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቻርተርድ በረራ እንደተሰረዘ አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል፡፡ 530 ኢትዮጵያዊያን ትናንት እና ዛሬ ለመጓጓዝ እየተጠባበቁ ነበር፡፡ አየር መንገዱ በረራው ለምን እንደተሰረዘ የሚያውቀው በቤሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ ነው ብሏል፡፡

8. በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና አማራ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ቅዳሜ እና ዕሁድ በተቀሰቀሰ ግጭት 11 ሰዎች እንደተገደሉ DW ዘግቧል፡፡ ግጭቱ ከከብት ዝርፊያ ጋር በተያያዘ የተፈጠረው በአዊ ዞን ዝገም እና ጓንጓ ወረዳዎች ነው፡፡ ከ400 በላይ ነዋሪዎች ደሞ ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለዋል፡፡

9. በኬንያው ደዳብ ስደተኞች መጠለያ ለመጀመሪያ ጊዜ 2 ስደተኞች በኮሮና ቫይረስ እንደተያዙ የተመድ ስደተኞች ድርጅት ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል፡፡ በመጠለያው ከ217 ሺህ በላይ ስደተኞች አሉ፡፡ ቫይረሱ በመጠለያው እና በዙሪያው ወለው ማኅበረሰብ በስፋት እንዳይሰራጭ ተሰግቷል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.