የከተማ አስተዳደሩ የፀጥታ አመራሮች “ህገ ወጥ ናችሁ፣ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳታደርጉ ካልሆነ እርምጃ እንወስዳለን” በማለት እያስፈራሩን ነው ሲል የአማራ ወጣቶች ማህበር በፍኖተ ሰላም አስታወቀ

አሚማ
ግንቦት 14 ቀን 2012 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ

የአማራ ወጣቶች ማህበር በፍኖተ ሰላም ሰብሳቢ ወጣት ጌራ ወርቁ እና የማህበሩ ም/ሰብሳቢ ወጣት ሳሙኤል አስራት ከአማራ ሚዲያ ማዕከል ጋር ቆይታ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት ማህበሩ ከገዥው ፓርቲ በርካታ እንቅፋቶች እየገጠሙት ነው።

ኮሮና ከመምጣቱ በፊት ህጉ በፈቀደላቸው ዘርፍ ሁሉ ተሰማርተው መቆየታቸውን ያወሳው ወጣት ጌራ ወርቁ የኮሮና መምጣትን ተከትሎ ግን በበጎ ፈቃድ ተግባራት ቢሰማሩም ገዥው ፓርቲ “ማህበሩ ህጋዊ አይደለም በማንኛውም የስራ ዘርፍ መሳተፍ አትችሉም” በሚል እንደከለከላቸው አስታውቋል።

አደረጃጀቱን ሙሉ በሙሉ ማፍረስ አለብን በሚል በብአዴን/አዴፓ አመራሮች ተንኮል እየተሰራብን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ብሏል።

ከቀናት በፊት በፌደራል መንግስት የተሰጠውን ፈቃድ አንቀበልም ያሉ የፀጥታ አካላት የአማራ ወጣቶች ማህበር በዳንግላ ያለውን ቅ/ጽ/ቤቱን እንደዘጉባቸው ተነግሯል።

በተመሳሳይ ትናንት ግንቦት 13 ቀን 2012 ዓ.ም የፍኖተ ሰላም ከተማ የአስተዳደርና ፀጥታ ኃላፊ አቶ መንግስቱና የከተማው የፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ዘለቀ ቢሮአቸው ድረስ በመጥራት “ህጋዊ አይደላችሁም ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ማድረግ አትችሉም፣ ካልሆነ እርምጃ እንወስዳለን” ሲሉ አስፈራርተውናል ብሏል ወጣት ጌራ።

“ፍቃዱን ለማሳየት ቢቻልም የክልል እንጅ የፌደራል አንቀበልም” የሚል ምላሽ እንደሰጧቸውም ተናግሯል።

አመራሮቹ የሚፈልጉት ከአማራ ክልል ወጣቶች ማህበር ጋር ተቀናጅተን እንድንሰራነው ያለው ሰብሳቢው የእኛ ማህበር ከአማራ ክልል ወጣቶች ማህበር ጋር በአላማም ሆነ በፍልስፍና አይገናኝም ብሏል።

ልዩነቱን ሲያብራራም የአማራ ክልል ወጣቶች ማህበር ሊግ ነው፣ ከላይ የሚቆጣጠረው የወጣቶች ፌዴሬሽን ነው፣አላማውም ለፓርቲው ተተኪ አመራር ማፍራት ነው፣ ከፖለቲካ ነፃ አይደለም፣በክልልም የታጠረ ነው ብሏል።

በአንፃሩ “የአማራ ወጣቶች ማህበር አቃፊ ነው፣ ከክልል ውጭ ያሉ ወጣቶችንም ጭምር ይፈልጋል፣ሲቪክ አደረጃጀት ነው፣ የአማራን ህዝብ ለመታደግ የሚሰራ ነው፣ የፖለቲካ ማስፈፀሚያ አይደለም” ሲል ወጣት ጌራ ተናግሯል።

“እንደ አማራ ህዝብ ካሰብን የሚሻለው ተደማምጦ፣ በጠረጴዛ ዙሪያ ተነጋግሮ ውጫዊ ችግሮችን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ውስጣዊ ክፍተቶቻችን መድፈን ነው” ያስፈልጋል ብሎ እንደሚያምን ገልጧል።

በር ዘግተው እየደበደቡበት ያሉበት ሁኔታ ግን ተገቢ አይደለም፣ ቤት ዘግተህ የደበደብከው ውሻ መናከሱ አይቀርምና የአዴፓ አመራሮች እየሄዱበት ያለው መንገድ የማይጣፍጥና ለህዝባችን፣ለክልላችን ብሎም ለሀገራችን የማይጠቅም በመሆኑ በድርጅቱ በኩል የማስተዋል ስራ ከተሰራ ጥሩ ነው ብለን እናስባለን ነው ያለው።

የአማራ ወጣቶች ማህበር በፍኖተ ሰላም ም/ሰብሳቢ የሆነው ወጣት ሳሙኤል አስራት በበኩሉ ማህበሩ የአማራ ህዝብ አንገቱን ቀና አድርጎ እንዲሄድ እየሰራ ቆይቷል፣ብዙ እንከኖችን በመቋቋም እያገለገለ መቆየቱን አውስቷል።

በትናንትናው እለት የፍኖተ ሰላም የፀጥታ አመራሮች ከክልል እንደታዘዙ በመግለፅ ማህበሩን ህገ ወጥ በሚል የፖለቲካ ወገኝተኝነት አሳይተዋል፤ ይህ አካሄድ ደግሞ ለማንም አይጠቅም ብሏል።

የአማራ ወጣቶች ማህበር ሲመሰረት እንደ አማራ ለአማራ ህዝብ ነው የቆምነው፣ የአማራ ህዝብ አንገት ደፍቶ እንዲኖር ስለማንፈልግ ቢሮ በመዝጋት ወይም በማነጋገር የሚቆም ትግል እንደሌለ፣ አደረጃጀታችን ስራውን እንደሚቀጥል ነግረናቸዋል ብሏል።

በመጨረሻም ወጣት ሳሙኤል እርምጃ እንደሚወሰዱብን ነግረውናልና ህዝባችን፣የአማራ ምሁራን፣አንቂዎችና ሌሎችም እንዲያውቁልን ሲል ጥሪ አድርጓል።

የአማራ ሚዲያ ማዕከል በፍኖተ ሰላም ከተማ የአስተዳደርና ፀጥታ ኃላፊን አቶ መንግስቱን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት “ስራ ላይ ነኝ አይመቸኝም” ከማለት ውጭ ሌላ ለመናገር ባለመፍቀዳቸው ሀሳባቸውን ለማካተት አልቻለም።

የፍኖተ ሰላም ከተማ የፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ዘለቀ በበኩላቸው ከእኛ ጋር ሳይሆን ከሚመለከተው ከመንግስት አመራር ወይም ከፖለቲካ አመራሩ ጋር ብትነጋገሩ ይሻላል በማለት ስልካቸውን ዘግተዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.