በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ተፈናቅለው የነበሩ ከ30 ሺህ በላይ ዜጎች ወደቀያቸው እየተመለሱ ነው

ባሕርዳር፡ ግንቦት 17/2012 ዓ.ም (አብመድ) ወደ ቀያቸው በመመለስ ላይ የሚገኙ ተፈናቃዮች መንግሥት የጸጥታ ዋስትና እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ2011 እና 2012 ዓ.ም ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከ49 ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታትም የሁለቱ ክልል መንግሥታት በጋራ ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ በመከላከያ ሠራዊት የሚመራ ኮማንድ ፖስትም ተቋቁሞ እየሠራ ይገኛል፡፡ የአካባቢው የጸጥታ ሁኔታ መሻሻሉን ተከትሎም ከመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ተፈናቅለው የነበሩ ከ30 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ወደ ነበሩበት ቀዬ በመመለስ ላይ ናቸው፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትናና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እታገኘሁ አደመ ከመተከል ዞን የተፈናቀሉት ዜጎች በክልሉ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ በምዕራብ ጎጃም፣ በምስራቅ ጎጃም እና በደቡብ ጎንደር ዞኖች ተጠልለው መቆዬታቸውን ገልጸዋል፡፡ ተፈናቃዮች መደበኛ ሥራቸውን እስከ ሚጀምሩ የ2 ወራት ጊዜያዊ ቀለብ መቅረቡን የተናገሩት ምክትል ኮሚሽነሯ ቤታቸው ለተቃጠለባቸው ዜጎችም ጊዜያዊ መጠለያ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡

አብመድ ያጋገራቸው ተመላሾችም በወቅቱ በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ምክንያት ለዓመታት ያፈሩትን ሀብትና ንብረት ተዘርፈው፣ ለችግር ተጋልጠው መኖራቸውን አስታውሰዋል፡፡ ወደቀያቸው መመለሳቸው ቢያስደስታቸውም በቀጣይም ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር መንግሥት ዋስትና እንዲሆናቸው አሳስበዋል፡፡ በግጭቱ ምክንያት የተዘረፈ ንብረታቸው እንዲመለስላቸውም ጠይቀዋል፡፡

የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግርማ ታደሰ በዞኑ ተከስቶ የነበረውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት ከአማራ ክልልና ከፌዴራል የጸጥታ አካላት ጋር ሲሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ በግጭቱ ወቅት የተዘረፈባቸው ንብረት፣ የቀንድና የጋማ ከብቶች እየተመለሱ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡ ችግሩን እንደፈጠሩ የተጠረጠሩ ግለሰቦችም በሕግ ቁጥጥር ሥር እየዋሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር የነበሩ ችግሮች እየተለዩ፣ ኅብረተሰቡም ድርጊቱን እያወገዘ መሆኑን አስተዳዳሪው አስታውቀዋል፡፡ በቀጣይ የዜጎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡

በሁለቱ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረውን የጸጥታ ችግር በመገምገም ወደ ቀድሞ ሰላሙ ለመመለስ፣ የተፈናቀሉ ወገኖችንና የተዘረፉ ንብረቶችን ለማስመለስ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ባለፈው ሳምንት የአንድ ወር አፈጻጸሙን መገምገሙ ይታወሳል፡፡ በወቅቱም ከ9 ሺህ በላይ ሰዎች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን፣ 581 የቁም እንስሳት ከዘራፊዎች መመለሳቸውን ገልጾ ነበር፡፡ ኮማንድ ፖስቱ 9 ሺህ 681 ቀስቶችና 34 ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም ገልጾ ነበር፡፡

የጸጥታ ችግር ተከስቶባቸው በነበሩ አካባቢዎች በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 97 ግለሰቦች ተለይተው ማስረጃ ከተገኘባቸው 71 ሰዎች ውስጥ 41 የሚሆኑት በህግ ጥላ ስር መዋላቸውን ኮማንድ ፖስቱ መግለጹን መዘገባችንም ይታወሳል፡፡

ዘጋቢ፡- ዘላለም አስፋው

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.