“ለግንቦት 20 የተከፈለው መስዋትነት በአንድ ቡድን የሥልጣን ስስት መክኗል” ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና

አዲስ አበባ:- በአንድ ቡድን የሥልጣን ስስት / ስግብግብነት/ በአገሪቱ ባለፉት 27 ዓመታት በዕኩልነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ባለመቻሉ ለግንቦት 20 ድል የተከፈለው መስዋትነትመባከኑ ተገለፀ።

የፖለቲካ ሳይንስ ምህሩ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ወጣቶች ጫካ ገብተው መራራ ትግል በማድረግ የ17 ዓመቱን የጭቆና አገዛዝ ገርስሰው ቢጥሉም፤ በአንድ ቡድን የሥልጣን ስስት በአገሪቱ ባለፉት 27 ዓመታት በዕኩልነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለመገንባቱ ለግንቦት 20 ድል የተከፈለው መስዋትነት ሊመክን ችሏል።

ከዘውዳዊው አገዛዝ ማብቂያ ማግስት ጀምሮ ባለፉት 50 ዓመታት የመጡ አገራዊ ለውጦች በዋናነት የከሸፉት በዕኩልነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለመገንባቱና የአንድ ቡድን የበላይነት በአገሪቱ በመንገሡ ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ በንጉሡ ዘመነ መንግሥት በዋናነት የወጣቱ ጥያቄ የዕኩልነትና መሬት ላራሹ የሚል የነበረ፤ የዚያ ዘመን ወጣቶችም ዋጋ ከፍለው የንጉሣዊ ሥርዎ መንግሥትን ከጫንቃቸው አሽቀንጥረው ቢጥሉም የመጣውን ለውጥ ደርግ ነጥቆ የራሱን አብዮት ለ17 ዓመት አካሂዷበታል ብለዋል።

ደርግም ወደ ሥልጣን ሲመጣ መሬት ላራሹ የሚለውን ጥያቄ በገደምዳሜው ቢመልስም፤ በ17 ዓመቱ አብዮት በዕኩልነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለመገንባቱና የአንድ ቡድንን የበላይነት በሰፊው ህዝብ ጫንቃ ላይ ለመጣል ሲደረግ በነበረው ግብ ግብ የአገሪቱ ብርቅየ ልጆች ተሰውተዋል፤ ብሔር ብሔረሰቦች ተጨፍልቀዋል፤ የዕምነትና የፖለቲካ ነፃነት ተገፏል።

ወጣቶች ጫካ ገብተው መራራ ትግል በማድረግ የደርግን የጭቆና አገዛዝ ገርስሰው ወደ ሥልጣን ሲመጡ ደመላሽ ወንድም መጣልን በሚል ሰፊው ህዝብ አጨብጭቦ ቢቀበላቸውም፤ ተጨቁነናል ብለው ጫካ ገብተው የታገሉ ሰዎች ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከትናንት ታሪክ ሳይማሩ የጠባብ ቡድንን ስሜትና ፍላጎት በሰፊው ህዝብ ላይ ለመጫን ባደረጉት ጥረት ወደ ጨቋኝነት መሸጋገራቸውን አመልክተዋል።

ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ በዕኩልነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመፍጠርና በቀን ሦስት ጊዜ ሊያበላ የሚችል የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ለኢትዮጵያ ህዝብ ቃል መግባቱን ጠቁመው፤ አንድ ቡድን ባለው የሥልጣን ስስት ባለፉት 27 ዓመታት የራሱን የበላይነት ለማስፈን ዜጎችን ሲገል፣ ሲያስርና ሲያሰቃይ መቆየቱን ጠቁመወዋል።

በዚህም ወጣቶች ዋጋ የከፈሉለት የዴሞክራሲ፣ የዕኩልነትና የልማት ጥያቄዎች ባለፉት 27 ዓመታት አለመመለሱን ፕሮፌሰሩ ገልፀው፤ በነበረው የአንድ ቡድን ስሜትና ፍላጎት ሁሉንም ያካተተና ያሳተፈ አገራዊ ግንባታ ውስጥ ባለመገባቱ ለግንቦት 20 ድል የተከፈለው መስዋትነት ሊመክን እንደቻለ ገልፀዋል።

ከንጉሡ አገዛዝ መጨረሻ ጀምሮ አገሪቱ ከአንዱ ቀውስ ወደ ሌለው ቀውስ እየተሸጋገረች ያለችው በዋናነት የፖለቲካ ጥያቄው ባለመፈታቱ ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ታሪክ እንደሚያስረዳው በአገሪቱ የአንድ ቡድንን የበላይነት ለማስፈን የሚደረገው ጥረት አገርን ያፈርስ እንደሆን እንጂ ማነንም አትራፊ ስለማያደርግ፤ ከትናንት በመማር አሁን ላይም በወጣቶች መስዋትነት በአገሪቱ የመጣው ለውጥ በዕኩልነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሊሳለጥበት ይገባል ብለዋል።

ከሀገሪቱ የቀደመ ታሪክ እንደምንረዳው በታሪክ አጋጣሚ ወደ ሥልጣን የመጣ ቡድን ሥልጣኑን ለማስቀጠል አገርና ህዝብን ብዙ ዋጋ ሲያስከፍል መቆየቱን አመልክተው፣ አገር በአንድ ቡድን ፈቃድ ብቻ አገር አትሆንም፣ አገር እንድትሆን ሁሉም የሚሳተፉበት እና አስተዋጽኦ የሚያደርጉትም ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል፤ ለዚህ ደግሞ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

አዲስ ዘመን ግንቦት 20/2012

ሶሎሞን በየነ

2 COMMENTS

 1. የጋራ መግባባት የሚገባኝ በነበረን የጋራ እሴት ላይ ተጨማሪ መግንባት እንጂ ያለውን እያፈረሱ ኣይደለም።
  እንደ ሀገር የሚያግባቡንን ታሪካችንን እያፋለሳችሁ ፣ ለዘመናት ያስተሳሰሩንን እምነቶች እያዋረዳችሁ፣ ያስተሳሰረችንን ባንዲራችንን ቢሮኣችሁ ለመስቀል የተጠየፋችሁ ደናቁርት፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን፣ ኣቶ ሙስጠፌን፣ ኦባንግ ሜቶን፣ዶ/ር መራራን፣ዶ/ር ደብረጺዮንን፣ ሽፈራው ሽጉጤን………….ወዘተርፈ ከኣራቱ መኣዘን ያሉ ዜጎችን በኣንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ማግባባት የቻለች፣ በዘመናት በማይገነባ የጋራ መግባቢያ ፣ በሁልም ዜጋ የዳበረች ውን፣ ከጥቁር ኣፍሪቃ ፊደል ያላትን ኣማሪኛን ስታራክሱ እና ለኣንድ ብሄር ሀብት ኣርጋችሁ ስት ሰጡ ባንጽሩ እንግሊዞች ሳት ሆኑ ፣ ወይም ቅኝ ተገዢዎች ሳትሆኑ የትኛው ነፍጠኛ ጭኖባች ሁ እንደሆነ የማይታወቅ፣ እንግሊዘኛን የምታጠኑ ማስተዋል የጎደላችሁ ፣ የምታሳዝኑ ናችሁ።
  መጀመሪያ ያለህን ኣጠናክር ፣ የተቅመትክበት እየናድክ የጋራ መግባባት፣ስትል ከስላቅ ያለፈ ቁም ነገር የለውም !!
  You may have accumulated knowledge ,you and your likes, but knowledge only is not enough , transform it into wisdom. One thing you miss, you ethno politicians , is wisdom . YOU ARE DEVOID OF WISDOM. Cultivate it , you are way behind to assume leadership position at your infantile stage now. Why Abiy is so embraced by most people irrespective of its ethnic origin ? because he exhibited wisdom . Period . Got it ?

 2. ባለፈዉ ጄነራል ታደሰን አስመልክቶ ዶክተር መራራ ነገር ለሳቱበት ጄነራል ታደሰ ብሩ ላይ አዝማቹም ሆነ ዘማቹ የሳቸዉ ድርጅት ያሰማራዉ መሆኑን አቻምየለህ ቢነግራቸዉም አላየሁም በሚል መልኩ አሁንም አስተያየት ሰጠሁ ብለዉ ነገር ያበላሻሉ። እሳቸዉ ታሪክ ከግምቦት 20 ጀምሮ ይነገር የሚሉን እወክለዋለሁ የሚሉትን ድርጅትነሰ ነገድ አከርካሪዉን የሰበሩት የግምቦት 20 ተዋናያን መሆናቸዉን እያወቁ እንዲህ ነገር ሲያበላሹ ማየት ያሳዝናል።

  እኝህ ሰዉ እንደ ጁዋር የፖለቲካ ተመራማሪ ነኝ ሲሉ ይደመጣሉ ሀገር ቤትም ከሀገር ዉጭም ጋብዘን አምጥተናቸዋል ነገር ግን ምንም ጠብ የሚል ነገር አላገኘንባቸዉም። አንድ የዩኒቨርስቲ መምህር የሆነ አመለካከቱ ዩኒቨርሳል መሆን በተገባዉ ነበር እሳቸዉ ግን ወርደዉ ወርደዉ ተፈልገዉ ወደማይገኙበት እየወረዱ ነዉ።

  አሁን ግምቦት 20 ፊደል ለቆጠር ሰዉ በኦዎንታዊ ጎኑ ይጠቅሳል? ኢሬቻ በአል ላይ/ በቅንጂት ዘመን ለወደቁ ዜጎች/ለባድሜ ጦስ የግምቦት 20 ቀጥታ ዉጤት መሆኑነ ቢያዉቁትም ከጅምሩ ጀምሮ በፓርላማ አባልነታቸዉ የሚያገኙትን ጥቅም እንጂ የሚወክሉትን ህብረተሰብ ከጉዳይ ባለመቁጠራቸዉ ጥቅማቸዉን እያጠነጠኑ ያልተገባ አስተያየት መስጠት ባልተገባቸዉ ነበር።
  ይልቁንስ የፖለቲካና የአለም አቀፍ ግንኙነት መምህር በመሆናቸዉ ስለ አባይ እንደ ምሁራን የሚቻላቸዉ ከሆነ አንድ ሊነበብ የሚችል ሰነድ ቢያስነብቡን የተገባ ይሆናል። ድፍረቱና ችሎታዉ ካላቸዉ በእንግሊዝኛ ጽፈዉት ለአለም አቀፍ ሚዲያ ተቋማት ልከዉ እንመልከተዉ ያ ካልሆነ ዘወትር የመንደር ፖለቲካ በሳቸዉ ስም የተጻፈ ካየሁ ሳላነብ እንደማልፈዉ ሊገነዘቡልኝ ይገባል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.