የዶክተር ካሳ ከበደ ነገር (በአቻምየለህ ታምሩ)

ዶክተር ካሳ ከበደ ግንቦት ፳ን አስታክከው በኢሳት ቴሌቭዥን ቀርበው ባካሄዱት ቃለ ምልልስ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት መጨረሻ ላይ ተፈጥሮ የነበረውን የሥልጣን ክፍተት ለመሙላት በእሳቸው አገላለጽ «የተዘረገፈውን ነገር መልሶ ጆንያ ውስጥ ከትቶ ሰብስቦ ለማሰር መልስ ሆኖ የተገኘው ወታደሩ ነው» ሲሉ ደርጎችን አወድሰዋል። ይህ የዶክተር ካሳ አገላለጽ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም እ.ኤ.አ. በ1999 ዓ.ም. በሮይተርስ ቴሌቭዥን ቀርቦ «the only viable institution or social group to rescue the country was the army» ሲል ከተናገረው ጋር አንድ አይነት ነው። ዶክተር ካሳ ንግግራቸውን ይቀጥሉና «በወታደሩ ላይ [ደርጎችን ማለታቸው ነው] የሚሰነዘረው አመለካከት ሚዛናዊ ቢሆን እመኛለሁ» ሲሉ አስተያየታቸውን ያጠቃልላሉ።

ዶክተር ካሳ ከበደ
ዶክተር ካሳ ከበደ

በእውነቱ ይህ የዶክተር ካሳ አስተያየት እጅግ የሚያሳዝን ከመሆኑ ባሻገር ደርግን ለማግዘፍ የተሰጠ በጣም የሚያስተዛዝብ አስተያየት ጭምር ነው። የዝነኞቹ የሳንድረስትና የሳንሲየር ምሩቃን በነበሩባታ አገር ደመወዝ ለማስጨመር ከየ ክፍለ ጦሩ ተጠራርተው አዲስ አበባ የተሰባሰቡ አስር አለቆችንና የበታች መኮንኖችን «የተዘረገፈውን ነገር መልሶ ጆንያ ውስጥ ከትቶ ሰብስቦ ለማሰር መልስ ሆኖ የተገኘው ወታደሩ ነው» ማለታቸው ታሪካችንን ለሚያውቅ ሰው በእጅጉ የሚያም ነው።

ምናልባት ይህ ዶክተር ካሳ ከበደ «የተዘረገፈውን ነገር መልሶ ጆንያ ውስጥ ከትቶ ሰብስቦ ለማሰር መልስ ሆኖ የተገኘው ወታደሩ ነው» ሲሉ የሰጡት አስተያየት እነ ጀኔራል ኃይሌ ባይከዳኝን፣ እነ ጀኔራል ዐቢይ አበበን፣ እነ ጀኔራል ከበደ ገብሬን፣ እነ ጀኔራል ይልማ ሽበሺን፣ እነ ጀኔራል አሰፋ አየነን፣ እነ ጀኔራል ደበበ ኃይለ ማርያምን፣ እነ ጀኔራል እያሱ መንገሻን፣ እነ ጀኔራል ስዩም ገድለ ጊዮርጊስን፣ እነ ጀኔራል ነጋ ተገኝን፣ እነ ጀኔራል ጃገማ ኬሎን፣ ወዘተን የሚመለከት ቢሆን ኖሮ አስተያየታቸው ውኃ ሊቋጥር በቻለ ነበር። ዋናውን ስራቸውን [የአገር ዳር ድንበር መጠበቅን] ትተው ደመወዝ ለማስጨመር አዲስ አበባ የከተቱ ደም የተጠሙ ነፍሰ ገዳዮችን የተዘረገፈውን ነገር መልሶ ጆንያ ውስጥ ከትቶ ሰብስቦ ለማሰር መልስ ሆኖ የተገኘው ወታደሩ ነው» ብሎ ማቅረብ is beyond me to comprehend! ደመወዝ ለማስጨመር ከያሉበት የተሰባሰቡት የበታች መኮንኖች [ደርጎች] ምን አውቀው ነው የተዘረገፈውን ነገር መልሰው ሊያስሩ የሚችሉት? ኢትዮጵያ የተማረና አዋቂ ሰው አልኖራት ብሎ ነው መደዴዎቹ እነ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ክፍተቷን የሚሞሉላት? እንዴውም አብዛኛዎቹ እንደ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አይነት ሌጣዎች በቅጡ እንኳ ትምህርታቸውን ያልጨረሱና የተማሩትን እንደ ኮሎኔል ስምረት መድኃኔና ሜጀር ጥበበ መንክር አይነት ልሒቃንን አጥብቀው የሚጠሉ ዋልጌዎች ነበሩ።

ሌላው ዶክተር ካሳ ከበደ ያነሱት ጉዳይ «የተዘረገፈውን ነገር» ሲሉ የገለጹትና በሳቸው አቀራረብ «ደርጎች የሞሉት የስልጣን ክፍተት» ተፈጥሮ እንደነበር አድርገው ለማሳየር የሞከሩትም በእጅጉ ከእውነት የራቀና የሚያስተዛዝብ አስተያየት ነው። ጤና ይስጥልኝ ዶክተር ካሳ ከበደ?! የትና መቼ ነው የስልጣን ክፍተት የተፈጠረው? የአገር አስተዳደር ልምድና እውቀት የነበራቸው ኢትዮጵያውያን [Ethiopian Statesmen] የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ፓርላማው በሰጣቸው ኃላፊነት መሰረት አዕምሯቸውን ጨምቀው የወደፊቱን የኢትዮጵያ ሁኔታ የሚበይን ሕገ መንግሥት አሰናድተውና ኢትዮጵያ ወደሚቀጥለው የለውጥና የዲሞክራሲ ጎዳና የምትጓዝበትን የለውጥ ፍኖት አዘጋጅተው ጨርሰው ወደሚቀጥለው እድገት እየተሸጋገረች በነበረችበት ደረጃ ላይ አይደለም እንዴ እርስዎ «የሚሰነዘርባቸው አስተያየት ሚዛናዊ ሊሆን ይገባል» ያሏቸው ደመወዝ ለማስጨመር የተሰባሰቡት ደርጎች ከአንዳንድ የውስጥ አዋቂዎች ጋር ተመሳጥረው መፈንቅለ መንግሥት [creeping coup] ያካሄዱት?

ሌላው ቢቀር ደርግ ራሱ መስከረም ሁለት 1967 ዓ.ም. ባስነገረው አዋጅ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አስተዳደር በልጅ እንዳልካቸው መንግሥት የተቋቋመው ኮምቴ ባዘጋጀው ሕገ መንግሥት መሰረት ባስቸኳይ ምርጫ እንደሚካሄድ፣ አልጋ ወራሹ ንጉሠ ነገሥቱን ተክተው እንደሚነግሱና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ እንዲመረጥ የሚደነግገው ረቂቅ ሕገ መንግሥት ስራ ላይ እንደሚውልኮ አውጇል። ይህ የደርግ አዋጅ የተዘረገፈ ነገር እንዳለና መልሶ ወደ ጆንያ ውስጥ በደርጎች እንደሚከተተ አያሳይም። እርስዎም እንደሚያውቁት በአባትዎ በደጃዝማች ከበደ ተሰማ አማካኝነት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፊት ቀርቦ የንጉሠ ነገሥቱን እጅ ነስቶ የተቀበለው 40 ሺህ ብርኮ የስልጣን ክፍተት ለመሙላት አዲስ አባባ መጥቶ የተሰጠው ሳይሆን የተረቀቀው ሕገ መንግሥት ሥራ ላይ እንዲውል ለማገዝ መጣን ባለው መሰረት እሱና ባለንጀሮቹ የሆኑት የበታች መኮንኖች ከተማ ውስጥ ሁከት የሚያስነሱ ተማሪዎች ጥፋት እንዳያስከትሉ የሚያደርጉትን የሰላም ማስፈን ስራ ባግባቡ ለማስኬድ እንዲችሉ የየእለት ወጪያቸውን ለመሸፈን ነበርኮ።

ባጭሩ ደርግ የፈጠረው የአገርና የትውልድ ክፍተት እንጂ የሞላ አንዳች የሥልጣን ክፍተት አልነበረም። አንድ ነገር ሊታወቅ ይገባል። ደርግ ሥልጣን የወሰደውም ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እጅ ሳይሆን እሳቸውን ከተኳቸው ሰዎችና ኢትዮጵያ በሕዝብ የተመረጠ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲኖራት የሚደነግገውን ረቂቅ ሕገ መንግሥት መስከረም ሁለት ባወጣው አዋጅ በማገድ ነው። እንዴውም እንነጋገር ከተባለ ከወያኔ በፊት ኢትዮጵያን አደጋ ላይ የጣለው ደርግ ነው። ኢትዮጵያ ያስተማረቻቸውን ጀኔራሎችን ገድሎ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ያስደፈረው ደርግ ነው። ኢትዮጵያኮ ከሶማሊያ ጋር ጦርነት ስታደርግ ጦሩን የሚመራ አንድም ጀኔራል አልነበራትም። ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ባደረገችው ጦርነት ጦሩን የሚመራ ጀኔራል ያልነበራት ጀኔራሎችን ስላላፈራች ሳይሆን ያፈራቻቸውን ጀኔራሎች ደርግ ፈጅቷቸውና የቀረሩትንም አስሯቸው ነው። ከዚህ በላይ የአገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ መጣልና ክፍተው መፍጠር ምን ሊኖር ይችላል? ግና የወያኔና የደርግ ጠላት ኢትዮጵያ ስለነበረች ደርግ ወድቆ ወያኔ ሲተካ ደርግ በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመው ግፍ እስከዛሬ ድረስ ሳይነገር ተሽፍኖር እንዲሁ ይኖራል! ሌላው ቢቀር ወያኔ በሀብት ባሕር የዋኘው ደርግ ከኢትዮጵያውያን ወርሶ ትቶላቸው በሄደው የኢትዮጵያውያን አንጡራ ሀብት መሆኑን እንኳ ልትነግሩን አትፈልጉም።

ስለእውነት ስለእውነት. . . ኢትዮጵያን አደጋ ላይ የጣሉና የደም ባሕር ያደረጓትን ደርጎችን፤ እነ ክዋሜ ኑክሩማህ «Ethiopia, a land of the wise; the bold cradle of Africa’s ancient rule and fertile school; the beacon of freedom for the black peoples in the world and the repository of Africa’s culture» ያሉላትን ጥንታዊቷን ኢትዮጵያ ታሪክ አልባ አድርገው ታሪኳንና ብሔራዊ ትርክቶቿን [national narratives] ወደ ተጨቋኝና ጨቋኝ ግንኙነት ያወረዱ ነውረኞችን፤ ኢትዮጵያ ወደፊት እንዲረከቧት ያስተማረቻቸውንና እጅጉን የበቁ ልጆቿን በዱልዱም አርደው የበሉ አውሬዎችን፤ ኢትዮጵያ እያደረገችው የነበረውን ተፈጥሯዊ ግስጋሴ ገትተው ከነበረችበት የጥቁር ሕዝቦች የለውጥ ኃዋርያነትና የተስፋ ጮራነት አዋርደውና በስተመጨረሻም ኢትዮጵያውያን በላባቸው ያፈሩትን ሀብት ሁሉ ወርሰው ለወያኔዎች አስከርበው አገር አልባ ያደረጉንን ደርጎችን አገር እንዳረጋጉና የሥልጣን ክፈተት እንደሞሉ አድርጎ ማቅረብ በእጅጉ ያማል!

3 COMMENTS

 1. ዶክተር ካሳ ከበደ በህልም ዓለም የሚኖር ሰው ነው። በአንድ ወቅት ስለ ኤርትራው መሪ ሲናገር ወገቤን ይዥ ስለ አቶ ኢሳያስ እከራከራለሁ ብሎን ነበር። እብደት ከልጅነት እስከ እርጅና። የተዘረገፈውን ለመሰብሰብ ወይስ ለሃገር በጣሊያን ወረራ ጊዜ ፍዳ የከፈሉትን በአንድ ጀምበር ለመደምሰስ? ደርግ የሃገሪቱ ታሪክ ያጨቀየ፤ የኢትዮጵያን የቁርጥ ቀን ልጆች በየምክንያቱ ጉድጓድ የከተተ፤ ለወያኔና ለሻቢያ ሰርጎ ገቦች የውስጥ ሥራቸውን እንዲሰሩ መንገድ የከፈተ ባፉ ብቻ “ኢትዮጵያዊነትን” የዘከረ የደንቆሮዎች ስብስብ ነበር። ዛሬ ሃገሪቱ ላለችበት አጣቢቅኝ ዋናው ምክንያት ደርግ ነው። “አንድ ሰውና አንድ ጥይት እስኪቀር” እንፋለማለን ያለን ያጉረኛና ደም አፍሳሽ የወታደር መንጋ የንጉሱን መንግሥት አሽቀንጥሮ ሲጥል የሃገሪቱን ሥረ መሰረት አናግቶ ነው። ደርግ አውሬ ነው። እነሱን የተካቸው ወያኔ ደግሞ የአውሬዎች ሁሉ አውሬ ነው። ስለዚህ ጊዜ ያለፈበት ንስሃ እየገቡ ከመዘላበድ ይልቅ አርፎ መቀመጡ ይበጃል። በሰው ደም የደነዘዘ ሰው ቢቆነጠጥም ሆነ እሳት ቢበላው አይሰማም። ዓለሙ ሁሉ ድንዝዟና! በደርግ ጊዜ መልካም ነገር ነበር ንጉሱ ጭራሽ ሳጥናኤል ነበሩ የሚሉን ሁሉ የሻቢያና የወያኔ ተላላኪዎች ናቸው። እንደ እውነቱ ከሆነ የሰው ልጆች መብትና ነጻነት አለቅጥ የተናደው ንጉሱ ከሥልጣን ከተገፈተሩ ወዲህ ነው። በአጼ ሃይለሥላሴ ዘመን አስተዳደራቸው ያማረና የሰው ልጆች ሰብአዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ የተከበሩበት ነበር እያልኩ ግን አይደለም። ችግር ነበር። ባላባታዊው አገዛዝ የራሱ የሆነ ትብታብ ነበረው። ግን ከደርግም፤ ከወያኔንም ከሻቢያም አሁን ካለው መንግሥት በእጅጉ ይሻል ነበር። እንደ ዶክተር ካሳ ከበደ ያሉት የፓለቲካ ወስላቶች ዛሬም ሃገራችን ያተራምሳሉ። የሚገርመው በእርጅና እንኳን ሰከን አለማለታቸው ነው። ደርግ ሃገሪቱን ያመከነ፤ ለገንጣይ ሃይሎች አመቻችቶ ያለፈ እቡይ የወታደር መንጋ ነበር። የሚያሳዝነው ይሻላል የተባለው ወያኔ ከግራዚያኒ መክፋቱ ነው። እስቲ እንሰንብት አሁን ሃገሪቱ ባለችበት የፓለቲካ ቸንፈር ሌላም እንሰማለን። ያኔ ዶክተር ካሳ ከበደ ምን ይል ይሆን? አበቃሁ።

 2. አረ በቃችሁ ይበለን ነገር እየባሰ በመሄዱ መንግስቱ ሐይለ ሰይጣን ክፋቱ ተረስቶ ባሉታዊ ጎኑ መነሳቱ ያሳዝናል። ዶ/ር ካሳም ቢሆኑ በእድሜዎ ደርሰዉ እነ ክቡር አክሊሉ ሐ/ወልድንና ሌሎች የጠገቡ ምሁራንን በነበሮት የሶሻል ስታተስ ሳያስተዉሉ አይቀሩም። እንደዉ ደርግ ዉስጥ ሰዉ ሲፈለግ ቢዉል የሐይለ ስላሴን ጁኒየር ሚኒስተሮች ያህል የሚመዝን ይኖራል?።#

  እንደተባለዉ በመጨረሻዉ ዘመን ጥበብን ካዋቂዎች ነጥቆ ለልጆች ይሰጣል የተባለዉ እዉነት መሆኑን እያየን ነዉ። ዶ/ር ካሳም እንግዲህ ከዘመን ርቀት ነገሩ ደብዝዞቦት ከሆነ አቻምየለህ ታሪክና ሰነድ አጣቅሶ እዉነትን በማያሻማ መልኩ አቅርቦሎታል ወይ ተማሩበት ወይ ተጸጸቱበት ሌላ ምን ይባላል።

 3. ዶ/ር ካሳ ያለፈዉን ትተን አሁን ኢትዮጵያን ቀስፎ የያዛት የአባይ ጉዳይ ነዉ ስለ አባይ ለእርሶ መንገር ትንሺ ፈገግ ያሰኛል እንደሰሙት የግብጽ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስተር ከእስራኤል የስለላ ድርጅት ሰራተኞች ጋር ከርሞ እንደመጣ እንኳን እርሶ እኛም ሰምተነዋል። ሙሳ ሺኩሪ የኛ ሊሆኑ የሚችሉትን እስራኤላዊያን ጓዳ ገብቶ አሉን ከምንላቸዉ ጋር መክሮ ሲወጣ እርሶ ለዚህ ታላቅ ተልእኮ አንሰዉ ነዉ ወይ ሳይሰሙ ቀርተዉ ነዉ?
  ይልቁንስ ባለፈዉ ክፉ የሰሩት ስራ ካለ በዚህ እንዲካካስ ስምዎም ከመቃብር በላይ እንዲዉል የሙሲ ሺኩሪን ተንኮል አክሺፈዉ በዛ በኩል ታላቅ ስራ ይሰሩልናል ብለን እንገምታለን። እርሶ ኢትዮጵያዊ እንጂ ምንም ሊሆኑ ስለማይችሉ በዚህ ችግራችን ላይ የሚታይ ስራ ይሰራሉ ብለን እንገምታለን። በዚህ ችግር ጊዜ አብረዉን ላልቆሙት ካሁን በሗላ ክብር መስጠት ይቸግረናል።
  አመሰግናለሁ
  ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.