ለቸኮለ! የዛሬ ሰኞ ግንቦት 24/2012 የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1. ባለፉት 24 ሰዓታት ምርመራ 85 ሰዎች ኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው ከጤና ሚንስቴር ፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡ 72ቱ ከአዲስ አበባ፣ 5ቱ ኦሮሚያ፣ 4ቱ ከትግራይ እና 1 ከአማራ ናቸው፡፡ የ1 ሰው ደሞ ሕይወት አልፏል፡፡ በተያያዘ፣ ደቡብ ክልል በአርባ ምንጭ የቫይረስ ምርመራ እንዳስጀመረ ኢትዮ ኤፍኤም ዘግቧል፡፡

2. ፌደሬሽን ምክር ቤት ከሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በቀረበለት የሕገ መንግሥት ትርጓም ላይ ለመወሰን በዚህ ሳምንት እንደሚሰበሰብ ሪፖርተር ዘግቧል፡፡ ከስብሰባው በፊት የምክር ቤቱ አመራሮች ለስብሰባው የውሳኔ ሃሳብ ይቀርጻሉ፡፡

3. የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ የትግራይ ክልላዊ ምርጫን ዘንድሮ እንደሚያካሂድ ትናንት በፌስቡክ ገጹ ባሰራቸው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ማዕከላዊ ኮሚቴው ቀደም ሲል ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ያሳለፈውን ውሳኔ ነው ያጸደቀው፡፡

4. በማጎ ብሄራዊ ፓርክ ሕገ ወጥ አዳኞች 8 ዝሆኖች እንደገደሉ ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል፡፡ ገዳዮቹ የዝሆኖችን ጥርስ ወስደዋል፡፡ የፓርኩ ሃላፊዎች ወንጀሉን ‘ዘር የማጥፋት ጭፍጨፋ’ ብለውታል፡፡ 2ቱ ገዳዮች ዝሆኖቹ ባደረሱባቸው ጉዳት ሕክምና ላይ ይገኛሉ፡፡

5. በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ሆቴሎች ሠራተኛ እንዳይቀነሱ መንግሥት ያወጣውን መመሪያ፣ የኢትዮጵያ ሆቴሎች ማኅበር ባግባቡ ማስፈጸም አልቻልኩም ማለቱን ካፒታል ዘግቧል፡፡ ከመመሪያው ውጭ 14 ሆቴሎች ሠራተኛ ወይም ደመወዝ ቀንሰዋል፡፡ መንግሥትም እስካሁን በቂ ክትትል አላደረገም፡፡

6. ትናንት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የራያ ቆቦ ወረዳ አስተዳዳሪ ሥዩም መስፍን እና የጸጥታ ሃላፊው መንገሻ ሞላ ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደላቸውን የክልሉ ብዙኻን መገናኛ ዘግቧል፡፡ ሃላፊዎቹ የተገደሉት ሮቢት ከተማ አቅራቢያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማስከበር ላይ ሳሉ ነው፡፡

7. የኢትዮጵያ ታጣቂዎች በሱዳን ወታደሮች ላይ የፈጸሙት ጥቃት በጋራ ወታደራዊ ኮሚቴ እንዲጣራ እና ችግሮች በዲፕሎማሲ እንዲፈቱ ኢትዮጵያ መጠየቋን ከውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ፌስቡክ ገጽ አይተናል፡፡ 1 የሱዳን መኮንን እና 7 ወታደሮች ለቆሰሉበት የሐሙስ’ለቱ ጥቃት መንግሥት ሐዘኑን ገልጧል፡፡ ሱዳን በበኩሏ ድንበሩን የጋራ ወታደራዊ ቃኝ ይጠበቅ ብላለች፡፡

8. ኡጋንዳ ከ‘ናሉባሌ’ ሃይል ማመንጫ ግድቧ ወደ ቪክቶሪያ ሐይቅ በምትለቀው ውሃ መጠን ሳቢያ 5 ኬንያዊያን ጠበቆች ክስ እንደመሰረቱባት ዘ ኢስት አፍሪካን ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ ከሐይቁ የሚወጣው ጎርፍ ከ50 ሺህ በላይ ኬንያዊያን አፈናቅሏል፤ እናም ኡጋንዳ የጉዳት ካሳ መክፈል አለባት፡፡ የኡጋንዳ ድርጊት ከግብጽ ጋር ያላትን የውሃ አለቃቅ ስምምነት እና የናይል ተፋሰስ ማዕቀፍን ይጥሳል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.