እንዲህ ፀረ አማራ መንገድ አላየሁም – ጌታቸው ሽፈራው

በትግሉ ውስጥ ብዙ ስህተቶች ይኖራሉ። ስሜቶች ይኖራሉ። እንደዚህኛው ግን የድንቁርና መንገድ አላየሁም። እንዲህ ፀረ አማራ መንገድ አላየሁም። በረራ ጋዜጣ ከመጀመርያዋ ቀን ጀምራ የአዲስ አበባን ጉዳይ ፍንትው ቁልጭ አድርጋ አቅርባለች። እነ ታከለ ኡማ መታወቂያ በብሔር እንደሚሰጡ ለመጀመርያ ጊዜ ይፋ ያደረገች ጋዜጣ ነች፣ እስከነሙሉ ዝርዝሩ። ጉዳዩ አጀንዳ የሆነው በረራ ካተመችው በኋላ ነው። ኢንተርኔት ላይ ያለው የአብዛኛዎቹ የመታወቂታ ታዳይ ስም ዝርዝር ላይ የበረራ መሆኑን ከስር ተፅፎ ታገኙታላችሁ። የተፈናቃዮችን፣ የገቢዎችና ጉምሩክን በአጠቃላይ በአዲሶቹ ገዥዎች የተያዙትን ተቋማት፣ በርካታ የአዲስ አበባ ጉዳይ ይፋ አድርጋ ሞግታለች። ግን ኦነግ አላቃጠላትም! ሰው ዘቅዝቆ የሚሰቅለው ፅንፈኛ ኃይል ዘቅዝቆ አላቃጠላትም!

በረራ ጋዜጣ ለመጀመርያ ጊዜ ፊት ገፁዋን በሙሉ የአማራ ጉዳይ አድርጋ ሚዲያዎች የሚገፉት የአማራ ጉዳይ አደባባይ ላይ እንዲታይ ያደረገች ጋዜጣ ነች። እንዲያውም ከአዲስ አበባ ባሻገር የአንድ ሕዝብ ጉዳይ ብቻ አትዘግቡበት የሚሉ አስተያየቶች ነበሩ። ለአማራ ቆሜያለሁ የሚል ሰው በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ይህን ጋዜጣ ሊያቃጥል አይቻለውም።

ከሞጣው ቃጠሎ በኋላ አማራውን በእምነት ካባ ሊመቱ የሞከሩ ሰዎችን ፊት ለፊት የሞገተችው በረራ ጋዜጣ ነች። በዛ ሰሞን ያለ ስሟ ስም የሰጧት የእነ አህመዲን ጀበልና የእነ ጃዋር መንጋዎች ነበሩ። ግን አላቃጠሏትም! አማራውን ያረዱ ኃይሎች ስትሞግታቸው፣ ስታጋልጣቸው “የማሕበረ ቅዱሳን ነች፣ የአብን ነች” ከሚል የበሬ ወለደ ወሬ ውጭ አላቃጠሏትም።

በተመሳሳይ ፍትሕ መፅሔት አገዛዙ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚያደርሰውን በደል በተደጋጋሚ ይፋ አድርጋለች። ትህነግ ይቆጣጠረው የነበረው ሰራዊት ወደ ኦዴፓ መዞሩን፣ የአማራው ውክልና አናሳ መሆኑን በዝርዝር ሞግታለች። በዚህም ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን የመከላከያ ኃላፊ በቲቪ ቀርቦ እርምጃ እንዲወሰድበት ጥሪ አስተላልፏል። ይህን ያህል አስጨንቋቸው ግን መፅሔቷን አላቃጠሏትም።

ፍትሕ ተቃጠለች ተብሎ የሚታሰበው በትህነግ/ኢህአዴግ ዘመን ነው። የአቶ መለስ ዜናዊ ሞትን ይፋ ያደረገችው ፍትሕ 30 ሺህ እትም ከማተሚያ ቤት እንዳይወጣ ይደረጋል። ይህ ጋዜጣ ለተመስገን አልተሰጠውም። ምን አልባትም በመለስ አፍቃሪ ካድሬዎች ተቃጥሎ ይሆናል። እርግጠኛ አይደለሁም። ከተቃጠለ የዛሬዎቹ ጋዜጣ አቃጣዮች ከትህነግ የወሰዱት መሆን አለበት! ሌላው ቀርቶ ፍትሕ በፊት ገፅ ይዛው የወጣችውን የትህነግ ጉዳይ ያበሳጫው የትህነግ ካድሬ እንኳ አላቃጠለትም። ይህን ለትህነግ የሚያበግን የፊት ገፅ ይዞ የወጣ ፅሁፍ ያቃጠለለት ለአማራ እቆማለሁ የሚል ነው።

እጅግ የሚያሳዝነው እየተለመደ ያለው ድንቁርና ነው። ጋዜጣና መፅሔት ማቃጠል። ይህን አድርጉ ከሚሉት መካከል አንዳንዶቹ የአማራ ርስት ይመለስ ሲባል “ቁራጭ መሬት” የሚሉ ናቸው። ትግራይ ውስጥ ያለው እንቅስቃሴ ላይ አጀንዳ አታድርጉ የሚሉ ናቸው። በሱዳን በኩል ገበሬው ሲወረር አያገባንም የሚሉ ናቸው። በእርግጥ በውሏቸው በረራ ይዛው ከምትወጣው ይልቅ ለትህነግ ይቀርባሉ። ያም ሆኖ የአማራን ጉዳይ ፊት ገፅ አድርጎ የሚወጣውን፣ አማራው በተቋም ደረጃ ውክልና እንደሌለው በጥናት የሚያቀርቡትን ሕትመቶች የሚያቃጥሉ ናቸው። በአጀንዳም በአንድ ወቅት ትህነግ አደረገው እንደተባለው ጋዜጣ በማቃጠልም ቅርበታቸው ከአማራ ሕዝብ ሳይሆን ለትህነግ ይመስላል።

ይህ የድንቁርና መንገድ ለጠላቶቻችን፣ የአማራ ጉዳይ የሚነሳባቸውን ሚዲያዎች ማጥፋት ለሚፈልጉ የአማራ ርስት የቀሙና ሚዲያም እንዳይኖር ለሚፈልጉት ካልሆነ ለማንም አይጠቅምም።

በረራ ጋዜጣ በአዲስ አበባ ታሪካዊ ስም የተመሰረተች ጋዜጣ ነች። ይህ እንኳን ብዙዎችን አይናቸውን አቅልቷል። ፍትሕ ስታሜዋ ግልፅ ነው። በረራ የሚል ስያሜ የማይፈልግም፣ ፍትሕን አልሻም የሚልም አላቃጠላቸውም። ለመጀመርያ ጊዜ ፅንፈኛ ሕትመቶች ተብለው ለየኤምባሲዎች በመንግስት ዝርዝራቸው ከተላኩት መካከል በረራና ፍትሕ ይገኙበታል። በተደጋጋሚ መንግስት ጫና አድርሶባቸዋል። ሆኖም የመንግስት ካድሬና ሕትመት ተከታተሉ የሚባሉት ደሕንነት እንኳ አላቃጠላቸውም። ይቃጠሉ ያለው ለአማራ ሕዝብ እቆማለሁ እያለ ሕዝብን ጎጃምና ጎንደር እያለ ሲከፋፍል የሚውል ወፈፌ ነው። እንዲቃጠሉ ያደረገው “ህወሓት ጀግና ነው፣ ሕወሓትን ለምን ጠየቃችሁ” የሚል አላማው ምን እንደሆነ የማይታወቅ ነው። እንዲቃጠሉ የሚቀሰቅሰው አማራ አደባባይ ላይ እየተገደለ፣ በይፋ እየተፈናቀለ፣ በግልፅ እየተበደለ ፌስቡክ ጫካ ውስጥ ተደብቆ የሚፅፈው ነው። ትህነግ በአማራ ስም ይከፋፍላል፣ ኦዴፓ በአማራ ስም አጀንዳ ሲሰጥ ይውላል። በዚህ ብዙዎች ራሳቸውን ገልጠው በሚፅፉበትና አማራ በአደባባይ በሚበደልበት ወቅት ተደብቆ ሆነ በይፋ እየፃፈ የአማራ ጠላቶች በይፋ ያላደረጉት እያደረገ ያለ የሌሎቹ አስፈፃሚ ካልሆነ ለአማራ ሊጠቅም አይችልም። ምን አልባት፣ ምን አልባት በስሜት፣ በኩታራና እንጭጭነት ከሆነ ይህ የድንቁርና መንገድ እንደማያዋጣ መነገር አለበት።

ሕትመቶቹ ችግር አይኖባቸውም አይባልም። የሚያስቀይሙ ፅሁፎች ሊወጡባቸው ይችላሉ። ሊያስቀይሙም ይችላሉ። የድንቁርናው መንገድ ግን ከዘመናዊ ሚዲያ አንፃርና አሰራር ብቻ ሳይሆን ከአማራ ባሕል አንፃር የሚያስኬድ አይደለም። አማራ በድሮ ዘመን የፈጣሪው ጉዳይ፣ እምነት ጉዳይ ጭቅጭቅ ሲያስነሳ እንኳ ስርዓት ጠብቆ፣ ቁጭ ብሎ ተከራክሮ “ተሸንፈሃል፣ አሸንፈሃል” የተባለ አርዓያ ሕዝብ ነው። አማራ ስሜ ጠፋ ብሎ እንኳ “በላ ልበልሃ” ብሎ በይፋ፣ በአደባባይ የክርክር መድረክ የነበረው ሕዝብ ነው። ያልሆነ ስም ሲሰጠው “በህግ አምላክ ከዚህ ሰው ጋር አከራክሩኝ፣ ሕዝብ ይፍረደኝ” ብሎ ደረቱን ነፍቶ በስልጡንነት ሲከራከር የኖረ ሕዝብ ነው።

አማራ ከድሮም ጀምሮ ሲሰንድ፣ ሲፅፍ የኖረ እንጅ ሲያቃጥል የምናውቀው ሕዝብ አይደለም። እንዲያውም አማራ የፃፈውን፣ አማራ የሰነደውን ያቃጠለው ጠላት ነው። የአማራን ሰነድ፣ አማራ የፃፈውን ያቃጠለች አውዳሚዋ ዮዲት ጉዱት ነች። አማራ የሰነደውን ያቃጠለው ግራኝ አህመድ ነው። ያ ትልቅ ሕዝብ አሁን አመድ የወለደ ይመስል እንደ ዮዲትና ግራኝ አህመድ የተፃፈ የሚያቃጥሉ ጉግ ማግጉጎች ተፈጥረዋል። ይህ የድንቁርና መንገድ ጠላቶቻችን ሲያደርጉት ሀገርን ወደኋላ እንደጎተተው፣ እየገሰገሰ የነበረን ሀገር ወደኋላ እንዳስቀረው በታላቁ አማራ ሕዝብ ስም ተደብቀውም ሆነ በግልፅ የሚፅፉት ሲያደርጉት ወደፊት ሊያራምድ አይችልም። ድንቁርና የጨለማ መንገድ ነው። እጅግ አደገኛ፣ ለታናናሾች ምሳሌ የማይሆን፣ አሳፋሪና የጥፋት መንገድ ነው። ይህ የእነ ዮዲት ጉዲት መንገድ በፖለቲካ ባሕልም በጥቅምም ፀረ አማራ ነው!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.