ብአዴን/አዴፓ በሕዝብ ላይ ትልቅ ክህደት ፈጽሟል – ግርማ ካሳ

የጣን ጉዳይ አሳሳቢ ነው። በሶሻል ሜዲያ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ትልቅ ዘመቻ እየተደረገበት ነው። ይሄን ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ መስራት የነበረበት መንግስት ነበር። ግን መንግስት ያንን ማድረግ አልቻለም። በዚህ ጉዳይ ግለሰቦችን የድርሻቸውን ማድረግ ቢችሉም፣ ስራው በጣም ትልቅ ነው። መንግስት ሃላፊነት ወስዶ ፣ በቂ ባጀት መድቦ መሰራት ነው ያለበት።

መንግስት ስራውንና ሃላፊነቱን መወጣት እንዲችል ትልቅ ግፊት ማስደረግ ብቻ ሳይሆን ማስገደድ መቻል አለበት። አዎን ዶር አብይ አህመድ መጠየቅ አለበት። ሆኖም ግን ከዶር አብይ በላይ መጠየቅ ያለባቸው የአዴፖ/ብአዴን ስዎች ናቸው። በቅርበት በጣና ያለውን ነገር አይተው፣ አጥንተው፣ በክልልና በፊዴራል ደረጃ ትኩረት እንዲሰጠው ማድረግ ነበረባቸው። ግን ያንን ማድረግ አልቻሉም።

በነገራችን ላይ አዴፓዎችና ብአዴኖች በጣና ጉዳይ ብቻ አይደለም፣ በታገቱ ተማሪዎች ዙሪያ ሕዝብ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥቶ፣ ጥያቄ አቅርቦላቸውም፣ እስከ አሁን ምን ያደረጉት ነገር የለም። ተማሪዎቹ ከታገቱ ስድስት ወራት አለፋቸው።

በአዲስ አበባ ከተማ የኦህዴድ ሹመኞች፣ ከኦሮሞ ክልል ሰዎችን እያመጡ በአዲስ አበባ ዴሞግራፊን ለመቀየር ሲያሰፍሩ፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ግን ቤት እያፈረሱ ዜጎችን ሜዳ ላይ ሲጥሉ፣ ከአማራ ክልል የመጡትን ከተማዋ ሲያስወጡ፣ ዝምታን ነው የመረጡት። እነ አቶ አቶ ደመቀ መኮንና ሆነ በምክትል ከንቲባነት ማእረግ የሚሰራው እነ ኢንጂነር እንዳውቅ አብጤ ድምጻቸውን አላሰሙም። ኢንጂነሩ ፣ ከአንድ አመት በፊት አንዳንድ የታከለ ኡማ አሰራሮችን ደፍሮ ይተች ነበር። ግን በኋላ ከነ ደመቀ መኮንን፣ “ከስራህ ትባረራለህ” የሚል አይነት ማስጠንቀቂያ ተሰጠው መሰለኝ አሁን ዝም ብሏል።

አንድ በግሌ ወደ ትልቅ ድምዳሜ ያደረሰኝ ነገር የምለው ቢኖር፣ ራሱን የአማራ ክልል የብልጽግና ቅርንጫፍ ብሎ የሚጠራው የብአዴን ቡድን ፣ ለአማራ ክልል ነዋሪዎች፣ ከአማራ ክልል ውጭ ለሚኖሩ ራሳቸውን አማራ ብለው ለሚጠሩ ወይንም አማርኛ ተናጋሪ ለሆኑ ማህበረሰባት እና ማንነታችን ኢትዮጵያዊነት ነው ለሚሉ ዉህድ ኢትዮጵያውን ፣ ለአዲስ አበቤዎች ጥቅምና መብት እንዲሁም እኩልነት በጭራሽ የቆመ እንዳልሆነ ነው። በአማራ ክልል ያለውን ከሚሴን፣ አዲስ አበባን፣ ድሬዳዋን፣ ሃረርን፣ እንደ አዳማ፣ ቢሾፍቱ …ያሉ አካባቤዎችን ሙሉ ለሙሉ ለኦህዴድ አሳልፎ ሰጥቷል። በዚያ እየተፈጸሙ ያሉ ዘረኛና አፓርታይዳዊ አሰራሮችን እያየ ዝም ብሏል። በነዚህ ቦታዎች ብአዴን ምን እንደማያገባው በመቁጠር።

ብአዴን ውስጥ ጥሩ ልብ ያላቸው፣ ሃቀኞች የሆኑ አሉ። ሁሉንም፣ በጅምላ መክሰስ አይቻልም። ግን እንደ ድርጅት ድርጅቱ የሞተና የማይረባ ድርጅት ሆኗል።

ይህ ድርጅት ነበር ሕወሃትን የጣለው። ይህ ድርጅት ባይኖር ኖሮ ሕወሃት አሁን አራት ኪሎን ታሽከረክር ነበር። እነ ዶር አብይ ወህኒ ነበሩ። ዶር አብይ ጠቅላይ ሚኒስተር አይሆንም ነበር። አዎን ሳይታገል የሚጥል የተባለለት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና የትግል ጓዶቹ በወቅቱ የሚያኮራ፣ ጥበብ የተሞላበት ትልቅ ስራ ነበር የሰሩት።

ነገር ግን ትግላቸው ለለውጥ፣ ለፍትህ፣ ለእኩልነት መሆኑ ቀርቶ ፣ ሕወሃትን ለመቀየር ብቻ የሆነ ትግል አስመሰሉት። ሕወሃት ስትሄድ፣ በሕወሃት ወንበር ኦህዴድን አስቀምጠው ነገር አለሙን የተዉት ነው የሚመስለው። ትላንት ሕወሃት ገንድሶ የጣለው ብአዴን አሁን ተሽመደመ። በራሱ የማይተማመን ድርጅት ሆነ። በበረከት ስምኦን ጊዜ የነበረዉን የአሽከርነትና የታዛዥነት መንፈስ ተላበሰ። ያኔ የሕወሃት አሽከር እንደነበረው አሁን ደግሞ የኦህዴድ ወይንም የኦሮሞ ክልል የብልጽግና ቅርንጫፍ አሽከር ሆነ። አጀንዳዎቹን፣ አላማዎቹን አንድ ሁለት ብሎ፣ አቅርቦ፣ ሞግቶ ማስፈጸም ተሳነው።

ድርጅቱ ከዚህ በኋላም ይለወጣል የሚል ተስፋ የለኝም። ሕግ መንግስቱና ፣ የፌዴራል አወቃቀሩ እንዲሻሻል ፣ አዲስ አበባ የነዋሪችዋ እንደሆነች የመሳሰሉ አቋሞችን ጠቅላላ ጉባያቸው ወስኖ ነበር። ግን የተወሰኑ ውሳኔዎችን አምስት ሳንቲም ተግባራዊ ማድረግ አልቻለም። አሁንም በተግባር ሕወሃትንና የሕወሃትን ሊጋሲ እየዘከሩ ነው። የሕወሃትና ኦነግ ሕገ መንግስት፣ የሕወሃትና የኦነግ የጎሳ አከላል እንደቀጠለ ነው።

አከላለሉንና ሕገ መንግስቱን ለመቀየር ሂደት አለው የሚል ሰበብ ሊሰጡ ይችላሉ። ግን በነርሱ እጅ ያለን በቀላሉ ማስተካከል የሚችሉትን እንኳን ማስተካከል አልቻሉም።

ሕወሃትን የሰጣቸውን አርማ ሕወሃት መቀሌ እንድትመሽግ ተደርጋም፣ የአማራ ክልል ባንዲራ አድርገው የሕወሃትን መንፈስ እያንጸባረቁ ነው።

ግንቦት 20 በማህበረሰቡ ላይ ምን አይነት ጥፋት እንዳመጣ፣ ምን ያህል በሕዝቡ የተረገመ ቀን ተደርጎ እንደሚቆጠር እየታወቀ፣ የክልሉ ዋና ከተማ ፣ የባህር ዳርን አይሮፕላን ማረፊያ “የግንቦት 20 አለም አቀፍ አይሮፕላን ማረፊያ” ተብሎ አሁንም እየተጠራ ነው።ሰዎቹ አሁን ሕወሃት ልባቸው ውስጥ ነው ያለችው። ምን አልባት ነገ ሕወሃት ተመልሳ ትምጣለች የሚል ስጋትም ሳይኖራቸው አይቀርም።

በዓማር አክልል በከሚሴ የኦሮሞ ዞን ነው ብለው በዚያ የሚኖሩ አማርኛ ተናጋሪዎች፣ በአማራ ክልል ውስጥ ልክ እንደ ኦሮሞ ክልል አድልዎ ሲፈጸምባቸው፣ በአማርኛ አገልግሎት እንዳያገኙ ሲደረግ፣ ያንን እንኳን ማስተካከል አልቻሉም።

እንግዲህ ምንም ማሽሞንሞን አያስፈለግም። በሕዝቡ ላይ የደረሰ ላለው መከራ ከኦህዴዶች ይልቅ በዋናነት መጠየቅ ያለባቸው ብአዴኖች ናቸው። እነ ዶር አብይንና እነ ታከለ ኡማ መተቸትና መቃወም ችግር የለውም። ግን እነ ዶር አብይንና እነ ታከለ ኡማን ENABLED ያደረጓቸው (የሚያደረጉትን እንዲያደርጉ የፈቀዱላቸው) ብአዴኖች እነ አቶ ደመቀ መሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል።

የአቶ ደምቀ መኮንን ጉዳይ ካነሳው ትንሽ ነገር ልበላችሁ። አቶ ደመቀ ፡

አንደኛ ፡ ሕግ መንግስቱ ይረቅ የነበረ ጊዜ ፣ የአዲስ አበባ ተወካዮች ሲቃወሙ፣ በአዲስ አበባ የኦሮሞ ልዩ ጥቅም ይጠበቅ በሚል ፣ ነፋሳቸው ይማር፣ ከነ ዶር ነጋሶ ጋር ተስማምቶ እጁን ያወጣ ሰው ነው። የአዲስ አበባ ህዝብን ጥቅም አሳልፎ የሰጠ።

በአቶ መለስ ዜናዊ ጊዜ የትምህርት ሚኒስቴርና የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል ሆኖ ሲሰራ የነበረ ነው። በዚያን ወቅት ይሰሩ የነበሩ በደሎችንና ግፎችንም አሜን ብሎ ተቀብሎ ሳይቃወም በወንበዱ ተንድላድሎ የቀጠለ ሰው ነው።

በአቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ጊዜ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ሰርቷል። በዚያን ወቅት ለተሰሩ ግፎችና በደሎችም ሃላፊነት አለመወሰደም ብቻ ሳይሆን ደፍሮ መሻሻሎች እንዲደረጉ ያደርገው ጥረት የለም።

እነ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ታችኛውንና መካከለኛቸው የብአዴን አመራሮች በመያዛቸው ሕወሃት መሸነፏን ሲያውቅ ፣ አቶ ደመቀ የኃይል አሰላለፍ ለውጥ መኖሩን፣ የሕወሃትን እድሜ ማጠሩን ተረድቶ ፍሬቻ አብርቶ ዞረ። ከነ አቶ ገዱ ጋር አብሮ ዶር አብይ እንዲመረጥ አደረገ። ከዚያም የተነሳ መቀመጫዉን ሳያጣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴርነት ቦታዉን እንደያዘ ቀጠለ። ግን እንደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ምን እየሰራ ነው የሚል ጥያቄ ቢቀርብ መልሱ “ሂድ ተብሎ የሚታዘዝበት ቦታ ሄዶ ፎቶ መነሳት ነው” የሚል ነው።

እንግዲህ እንዲህ አይነትን ሰው፣አሁን ወንበር ከማሞቅ ያላፈ ስራ ይሰራል ብሎ መጠበቅ አስቸጋሪ ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.