በመንግሥት አካላት ጥቃት ተፈጸመባቸው ግለሰቦች ሲታሰቡ

ትናንት በተለያዩ አካላት ስቃይ የደረሰባቸው ሰዎች የሚታሰቡበት እና ድጋፍ የሚደረግላቸው ቀን ነበር፡፡ ቀኑን በማስመልከት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ባስተላለፉት መልዕክት፤ “በሰዎች ላይ ስቃይ የሚፈጽሙ ሰዎች ከነበደላቸው መተው የለባቸውም፤ በሰዎች ላይ ስቃይ እንዲፈጸም የፈቀዱ ሥርዓቶችም መፍረስ ወይም ሥር ነቀል ለውጥ ሊካሄድባቸው ይገባል” ብለዋል።

የተለያየ መልክ ያላቸው እና ሆነ ተብሎ የሚፈጸሙ ስቃዮች፤ ዓላማቸው በሚሰቃየው ግለሰብ ላይ አካላዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ጫና ማድረስ ነው።

መሰል ጥቃት ከደረሰባቸው ሚሊዮኖች መካከል አንዱ ደግሞ ዮናስ ጋሻው ነው። ዮናስ በመንግሥት የጸጥታ አካላት በደሰበት ጥቃት ለከፋ ጉዳት መዳረጉ ይታወሳል።

ጥቂት ስለ ዮናስ

ዮናስ ጋሻው ተወልዶ ያደገው በፍኖተ ሰላም ከተማ ሲሆን በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አጠናቋል፡፡ ለእስር የተዳረገው ተመርቆ መስራት በጀመረ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ፣ በ2009 ዓ.ም ነበር፡፡

በእስር ቤቶች ውስጥም ለጆሮ የሚከብድ አሰቃቂ በደል እንደተፈጸመበት፣ ከእስር ከተለቀቀ በኋላ በአካል ቀርቦ ለተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ተናግሯል፡፡

የእግሮቹ ጣቶች ጥፍር በፒንሳ እንደተነቀሉ፤ ብልቱ ላይ በውሃ የተሞላ ኮዳ በማንጠልጠል ማኮላሸት እንደተፈጸመበት፤ ራሱን ችሎ መቆም እስከሚያቅተው ድብደባ እንደደረሰበት በዝርዝር አስረድቷል፡፡

በደረሰበት ድብደባ በጀርባው መተኛት እንደማይችልና ሽንት ቤት እንኳን ለመሄድ በሰው ድጋፍ እንደነበር በወቅቱ ለቢቢሲ ገልጿል፡፡

እርሱ እንዳለው በደሉ አካላዊ ብቻ ሳይሆን ሥነልቦናዊ ጉዳቱም ከፍተኛ ነው፡፡ በማንነቱ ይሰደብና ይዘለፍ ነበር፡፡

መንግሥትን በቃል ከመተቸት ውጪ፤ ለደረሰበት ስቃይ የሚያበቃ ተግባር ፈጽሞ እንደሆነ ራሱን እስከሚጠራጠር ድረስ ግፍ እንደተፈጸመበትም ተናግሯል፡፡

በደሉ በእርሱ ብቻ ሳያበቃ ቤተሰቡም በደል እንደደረሰባቸውና እናትና ወንድሙን በሞት እንዳጣ፤ አባቱ ደግሞ የት እንዳሉ እንደማያውቅ በተደጋጋሚ ገልጿል፡፡

የሽብር ክስ ተመስርቶበት የነበረው ዮናስ፤ ከእስር የተለቀቀውም የዶ/ር ዐብይ ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ ከሁለት አመታት በፊት ነበር፡፡

በወቅቱም “በቁሜ የሞትኩ ያክል ቢሰማኝም፤ ይህንን ለውጥ በማየቴ ደስተኛ ነኝ” ሲል ስሜቱን ገልጾ ነበር፡፡

ዮናስ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? በማን እገዛ?

ቢቢሲ ያነጋገረውና በአሁኑ ወቅት ለህክምና አሜሪካ የሚገኘው ዮናስ ጤናው እየተሻሻለ እንደሆነ ገልጾልናል፡፡

ሙሉ ጤናማ አካሉን ይዞ እስር ቤት የገባው እና ዊልቸር ላይ ሆኖ፤ ሰውነቱ እየተንቀጠቀጠ ከእስር የወጣው ዮናስ፤ አሁን ላይ በተደረገለት ህክምና የሰውነቱ መንቀጥቀጥ እንደቆመለት፤ አነጋገሩም እየተስተካካለ እንደመጣ ነግሮናል፡፡

አልታጠፍ አልዘረጋ ላለው እግሩም የህክምና ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ገልጾልናል፡፡

“ይህንን የፈጸሙብኝ አካላት ለጥቅማቸው ሲሉና ሥልጣናቸውን በመፈለግ በእኔ ላይ ያደረጉት ነገር ይኖራል፤ በሌላ በኩልም እኔ እንደዚያ መሆኔ ምንም አድርጌ ባይሆንም፤ ለከፈልኩት ዋጋ ሕዝብ ስለካሰኝ ደስ ብሎኛል፡፡” ይላል፡፡

በደል ስለፈጸሙበት ሰዎች ያለውን ስሜት የተጠየቀው ዮናስ፤ “እነሱ ላደረጉት ነገር እግዚአብሔር ይቅር ይበላቸው፤ እነርሱ ያደረሱብኝን ጉዳት ሕዝቡ እንድረሳ አድርጎኛል፤ ሁሉንም ሰው በእኩል ዐይን አላይም” ሲል መልሷል፡፡

ዮናስ ከደረሰበት ጉዳት እንዲያገግም ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ሰዎች የገንዘብ መዋጮ አድርገውለታል። ለዮናስ ህክምና ገንዘብ ሲያሰባስቡ ከነበሩት መካከል ዮሐንሰ ሞላ አንዱ ነው።

ዮናስ በወቅቱ ድጋፍ አድርጉልኝ ብሎ አለመጠየቁን የሚያስታውሰው ዮሐንስ ፤ በግሉ ተነሳሽነት በፌስቡክ ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራ እንደጀመረ ያስታውሳል፡፡

“ጓደኞቼን አስተባብሬ ገንዘብ ማሰባሰብ ጀመርኩ፤ ከዚያም ባልጠበቅኩት መንገድ በርካታ ሰዎች ገንዘብ ለገሱ” ይላል፡፡

ገንዘቡ ከፍ እያለ ሲመጣም ለዮናስ እንደነገረውና እርሱም ደስተኛ እንደነበር ገልጾልናል፡፡ ከዚያም ገንዘብ ማሰባሰቡ ቀጥሎ 98 ሺህ ዶላር ደረሰ፡፡

አሜሪካ ሄዶ እንዲታከም ለማድረግም የሚያስፈልጉ ነገሮችን በማሟላት ከተባበሩት መካከል ዶ/ር ጌታቸው ወልደሄር የተባሉ ግለሰብን ይጠቅሳል፡፡

ይህን ተግባር ለመፈጸም ምን እንዳነሳሳው የተጠየቀው ዮሐንስ፤ “ጥቃቶች በሰው ልጆች ላይ ይደርሳሉ፡፡ ጥቃት አድርገን የማንወስዳቸው ሁሉ ጥቃቶች ይደርሱብናል፡፡ እኔ ራሴ ለመኖር በማደርገው የህይወት መስተጋብሮች ሃሳቤን መግለጽ እየፈለኩ፣ ሃሳብህን መግለጽ አትችልም እየተባልኩ ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፌያለሁ፡፡ ህመሙ ይገባኛል. . . ” ሲል ምላሹን ሰጥቷል።

አክሎም “. . .ዮናስ ደግሞ ከጥቃት ያስጥለኛል ብሎ ያመነው መንግሥት፤ ይህን በደል አድርሶበታል፡፡ የደረሰበት በደልም አንድ ሰው ላይ ሊደርሱ የሚገቡ ናቸው ብሎ ማሰብም ይከብዳል፡፡” በማለት ከደረሰበት አካላዊ ጥቃት ባሻገር እናቱና ወንድሙ በዚሁ ጉዳይ መሞታቸውን፤ አባቱ ያሉበት አለመታወቁን ሲሰማ የራሱን ጭንቀት ለማስታመም እንዲሁም አይዞህ ለማለትና ሰው እንዳለ ለማሳየት ያደረገው እንደሆነ ያስረዳል፡፡

ከፍተኛ ስቃይ እና ህመምን ያሳለፈው ዮናስም “ሰዎች ከህመሜ እንድድን ያደረጉትን ጥረት ሳይ፤ የበደሉኝን ይቅር እንድላቸው አድርጎኛል” ብሏል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በእስረኞች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸም እንደነበር ጠቅሰው ይቅርታ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡

በኢትዮጵያ እስር ቤቶች ውስጥ ለስቃይና ለእንግልት የተዳረጉ እነዚህ የቀድሞ እስረኞችም መንግሥትን ካሳ እንጠይቃለን ብለው ነበር፡፡

የሰብዓዊ መብት ተከራካሪና የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ አምሃ መኮንንም፤ በወቅቱ ተጎጂዎች ካሳ የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት እየሰሩ እንደሆነና ጉዳያቸው በአገር ውስጥ ፍርድ ቤቶች መልስ የማያገኝ ከሆነም ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ድረስ ለመሄድ እንደተዘጋጁ መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.