ሁለት ወዶ አይቻልም፣ ወይ ሕገመንግስቱን ማክበር አሊያም መቀየር ግድ ነው – ግርማ ካሳ

“እነዚህ የአውሮፓ ወይም የአፍሪካ ሀገራት ባንዲራዎች አይደሉም፤ ተጨማሪ ክልል ሊሆኑ ያኮበኮቡ ባንዲራዎች ናቸው፤ የህገ መንግስት ተብዬው ትሩፋቶች ” ይላል ጦማሪ ወንድማገኝ አንጃሎ ሲሳይ።

አሁን የብልጽግና ፓርቲ ሰዎች “ሕገ መንግስታችን” የሚሉት ሕወሃትና ኦነግ የጻፉት ሕገ መንግስት በግልጽ አስቀምጦታል። የኢትዮጵያ የባለቤትነት ስልጣን የተሰጣቸው እነርሱ “ብሄር ብሄረሰብ ሕዝቦች” የሚሏቸው ጎሳዎች ናቸው። ጎሳቸው የራሳቸው ክልል መሆን ሳይሆን የራሳቸውም አገር መመስረትም ይችላሉ። የብልጽግና ገዢዎች የክልል ጥያቄዎችን መነሳቱን ማፈን ሆነ መከልከል አይችሉም። “ሕገ መንግስታችን” ያሉት አይፈቅድላቸውም።

በዚህ ጉዳይ ጦማሪ ዮናታን ተስፋዬ ፣”የክልልነት ጥያቄ ከፌደራሊዝሙ አወቃቀር አንፃር ተገቢ ነው!” ብሎ የጻፈው አለ።

“ኢህአዴግ ከሚገርሙኝ ነገሮች አንዱ 300 ሺ አካባቢ ለሚሆነው ለሀረሪ ህዝብ ክልል ፈቅዶ ወላይታ፣ ሀድያ፣ አላባ፣ ስልጤ፣ ጉራጌ፣ ከምባታ… ወዘተ የከለከለበት ምክንያት ነበር። ከህዝብ ቁጥር አንፃር ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱ ፌደራል አወቃቀር ቋንቋን መሰረት ያደርገ ሆኖ ሳለ 80 ቋንቋ ባለበት ሀገር 9 ክልሎች ብቻ መኖራቸው አድሏዊ እና በዜጎች ላይ የተፈፀመ ሸፍጥ ተደርጎ ሊታይ ይችላል” ሲል ከጅምሩ የነበረውን አከላለል ነቅፏል።

“ዛሬ እነዚህ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪዎች የክልልነት ጥያቄ ቢያነሱ እጅግ ተገቢ ነው። ሀገሪቷ አሁን በተዋቀረችበት አኳኋን ሁሉም የየራሱ ቋንቋ ያለው ማህበረሰብ የየራሱ ክልል ይገባዋል። መብቱ ነው – የአንዱ ቋንቋ ተናጋሪ ብዙ ስለሆነ ክልል ሆኖ ሌላው ተናጋሪው በቁጥር አነስተኛ ስለሆነ ክልል የሚከለከልበት ምንም አሳማኝ ምክንያት አይኖርም – ከግብዝነት እና ከኢፍትሃዊነት ሌላ! እያንዳንዱ ቋንቋ ተናጋሪ የየራሱ ክልል የመመስረት መብት አለው!” ሲል በሕገ መንግስቱ መሰረት መንግስት የክልል ጥያቄዎች ከማስተናገድ ውጭ ምንም አማራጭ እንደሌለው ነው ያስቀመጠው።

በብዛት ክልሎችን መፍጠር የራሱ ትልቅ ችግር እንዳለውና አገሪቷን ወደ ትልቅ አደጋ ሊጥላት እንደሚል መገመት አያስቸግርም። ሆኖም ግን የዚህ ችግር ምክንያቱ የክልል ጥያቄ አቅራቢዎች ሳይሆን ሕገ መንግስቱ ነው።

አንደኛ በደቡብ ክልል ወደ 55 በጠቅላላው በኢትዮጵያ ወደ 83 ብሄረሰቦች አሉ።ነገሮች ገፍተው ከሄዱ ቢያንስ 83 ክልሎች ይኖራሉ ማለት ነው።፡ያ ብቻ አይደለም የአንድ ብሄረሰብ አባላት በአንድ አካባቢ ብቻ ታጥረው አይደለም የሚኖሩት። ለምሳሌ አዳማ፣ አሰላ የመሳሰሉትን እንውሰድ። እነዚህ ከተሞች ውስጥ የሚኖሩት ብዙዎቹ ኦሮሞ ስላልሆኑ ከኦሮሞ ክልል ውጭ የራሳችን ክልል ይኑረን ቢሉ መብታቸው ነው። ከሚሴ ያሉ ኦሮሞዎችም የራሳቸው ክልል ቢጠይቁ መብታቸው ነው። ስለዚህ የአማራ ወይንም የኦሮሞ ክልሎች ሊበዙም ይችላሉ ማለት ነው። በዚህ ምክንያት ዘር እየታየ መካለል ከተጀመረ ከመቶ በላይ ክልሎች መፈጠር ይኖርባቸዋል።

ሁለተኛ በአንድ አካባቢ የተለያዩ ብሄረሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ። አሁን ችግር እየፈጠሩ ያሉትን አንዳንድ አካባቢዎች ማየት እንችላለን። ሞያሌ፣ ዲላ፣ ድረዳዋ፣ ወልቃይት፣ ባቢሌ፣ ሃረር፣ ጉርሱም፣ ሜኤሶ፣ ራያ የመሳሰሉት። በነዚህ ቦታዎች አንድ ጎሳ ብቻ አይደለም የሚኖሩባቸው። ታዲያ ለማን ሊሰጡ ነው ?

በድሬዳዋ፣ የኦሮሞ ክልል “ድረዳዋ የኔ ነው” ይላል። የሶማሌ ክልል አያስማም። የኔ ነው በሚል ውዝግብ፣ ይኸው 28 አመት የድሬደዋ ችግር አልተፈታም። ሶማሌዎችና ኦሮሞዎች እየተፈራረቁ ነው ድሬዳዋን የሚያስተዳድሩት። የከተማዋ 40% ጥቅም ለኦሮሞ፣ 40% ለሶማሌ፣ 20% ደግሞ ለሌላው ተብሎ። የዲላ ከተማ ለሁለት ተከፍላ ግማሹ ወደ ኦሮሞ ክልል ግማሹ ወደ ደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን ተወስዷል። የሞያሌ ከተማ መሐል ላይ ነው የተከፈለችው። ከአዲስ አበባ ወደ ኬኒያ ሲኬድ፣ በሞያሌ ከተማ መሐል ሲታለፍ በስተቀኝ ኦሮሞ ክልል ነው፣ በስተግራ ደግሞ ሶማሌ ክልል ነው። የትግሬና የአማራ በሚል፣ ጠገዴና ጸገዴ፣ ጠለምትና ጸለምት በሚሉ ስሜዎች አንድ ወረዳ/አውራጃ የነበሩ ለሁለት ተከፍለዋል።

ሶስተኛ የጎሳዎች የድንበር ግጭትና የይገባኛል ጥያዎች ለርስ በርስ ከፍተኛ የደም መፋሰስ፣ መጋበዙ አይቀርም።

በአጭሩ አገሪቷ ወደ ባሰ ችግር ውስጥ የመግባትና የመከፋፈል እድሏ የበዛ ነው። አሁን በሕገ መንግስቱ መሰረት፣ በሕግ መንህግስቱ የተቀመጠውን መብት በመጠቀም እየተኬደ ያለው አካሄድ በጣም አደገኛ አካሄድ ነው የምንለው።

በአንድ በኩል ለአንዱ ፈቅዶ፣ ለሌላው መከልከል፣ በሕግ መንግስቱ መሰረት የሚጠየቁ ጥያቄዎችን አንቀበልም ማለት አይቻልም። በሌላ በኩል ይህ አካሄድ ከቀጠለ ለአገር አደጋ ነው። ታዲያ መፍትሄው ምንድን ነው ?

መፍትሄው ፕሮፌሰር መስፈን ድሪቶ ያሉትን ሕገ መንግስት መቀየር ነው። ጎሳና ዘርን ከሕግ መንግስቱ ማውጣት ነው። “መንግስት ይህን ማድረግ የማይችል ከሆነ አጠቃላይ የሀገሪቷን አወቃቀር መፈተሽ እና አዲስ የክልልነት መመዘኛ መስፈርቶች ማስቀመጥ ግድ ይለዋል” እንዳለው ዮናታን ። ሁለት ወዶ አይቻልም፣ ወይ ሕግ መንግስቱን ከማክበር አሊያም ከመቀየር ውጭ ሌላ አማራጭ የለም።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.