ለቸኮለ! የዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 23/2012 የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1. ታዋቂው የኦሮምኛ ድምጻዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ ትናንት ምሽት በአዲስ አበባ ከተማ ባልታወቁ ታጣቂዎች በተተኮሰበት ጥይት መገደሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ትናንት ለኢቢሲ ተናግሯል፡፡ ድምጻዊው ምሽት 3፡30 ላይ የተገደለው ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ገላን አካባቢ ነው፡፡ ፖሊስ የተወሰኑ ገዳይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል፣ ምርመራ እያደረገ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

2. በድምጻዊ ሐጫሉ ሞት ሳቢያ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ ዛሬ በተቀሰቀሰ ሁከት 5 ሰዎች በጥይት ተመተው ሕይወታቸው ማለፉን ቢቢሲ አማርኛ የከተማዋን ሆስፒታል ምንጮች ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ 75 ሰዎች ደሞ ቆስለው ሕክምና ላይ ይገኛሉ፡፡ አንዳንድ የመንግሥት ሕንጻዎችም ቃጠሎ እንደደረሰባቸው የዐይን እማኞች ተናግረዋል፡፡

3. የሟች ድምጻዊ ሐጫሉ አስከሬን ከቀትር በኋላ በሄሊኮፕተር ወደ አምቦ እንደተወሰደ ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል፡፡ ይህን ለኦቢኤን ቴሌቪዥን የገለጹት የኦሮሚያ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ናቸው፡፡ የሟች ቤተሰብ ፍላጎት አስከሬኑ ወደ አምቦ እንዲላክ ነው፡፡ ጧት ላይ ግን አስከሬኑ ወደ አምቦ ጉዞ ሲጀምር፣ አደባባይ የወጡ ተቃዋሚዎች በፈጠሩት ጫና ተመልሶ በአዲስ አበባ በኦሮሚያ ባሕል ማዕከል አርፎ ነበር፡፡

4. የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) አባል እና የኦሮሞ ብሄር መብት ተሟጋቹ ጃዋር ሞሐመድ እና የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር በቀለ ገርባ በጸጥታ ሃይሎች ተይዘው እንደታሰሩ የኦሮሞ ሜዲያ ኔትወርክ (ኦሜን) ዘግቧል፡፡ የፌደራል ጸጥታ ሃይሎች የጃዋርን የግል ጠባቂዎች ትጥቅ አስፈትተዋል፡፡ ፖሊስ እስካሁን ስለ እስሩ ይፋዊ ማረጋገጫ አልሰጠም፡፡

5. የኦሮሞ ሜዲያ ኔትወርክ ፌደራል ፖሊሶች ወደ አዲስ አበባ ስቱዲዮው ሰብረው በመግባት ሠራተኞቹን እንዳሰሩበት በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡ ድምጻዊ ሐጫሉ ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደሉን ተከትሎ፣ ጣቢያው በአደባባይ ለተካሄዱ ተቃውሞ ሰልፎች ሽፋን ሲሰጥ እና የሕዝብ አስተያየቶችን ሲያሰራጭ ነበር፡፡ ከቀትር በኋላ የጣቢያው የአዲስ አበባ ስቱዲዮ ሥርጭቱን አቋርጧል፡፡

6. የድምጻዊ ሐጫሉን ሞት እንደ አጋጣሚ በመጠቀም፣ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ እና የሕዝብ እና መንግሥት ንብረቶችን የሚያወድሙ አካላት በሕግ እንደሚጠየቁ ም/ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን በፌስቡክ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት አስጠንቅቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ እና የኦሮሚያ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በድምጻዊው ሞት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል፡፡

7. በድምጻዊ ሐጫሉ ሞት ሳቢያ በአዲስ አበባ፣ አምቦ፣ ጅማ፣ ሐረር፣ አዳማ እና ሌሎች ከተሞች ተቃውሞ መቀስቀሱን ተከትሎ በሀገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል፡፡ ጧት የድምጻዊው አስከሬን ሽኝት እንቅስቃሴ ሲደረግ፣ አድናቂዎቹ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ተጋጭተዋል፡፡ በሐረር ከተማ አደባባይ የወጡ ተቃዋሚዎች የራስ መኮንን ሐውልትን እንዳፈረሱ በማኅበራዊ ሜዲያ ከተሰራጩ ምስሎች ተመልክተናል፡፡ የአደባባይ ተቃውሞዎች እና ሁከቶች ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት እንደደቀኑ ዋዜማ ካሰባሰበቻቸው መረጃዎች ተረድታለች፡፡

8. የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ተናንት በሕዳሴው ግድብ ውዝግብ ላይ ተነጋግሯል፡፡ በምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ታዬ አጽቀ ሥላሴ የመንግሥታቸውን አቋም በጽሁፍ አሰምተዋል፡፡ ጸጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን ለማየት ትክክለኛ አካል አይደለም- ብለዋል መልዕክተኛው፡፡ በድንበር ተሻጋሪ ወንዝ የልማት ውዝግብ ላይ ምክር ቤቱ መወያየቱ አደገኛ ምሳሌ ጥሎ እንደሚያልፍ አስጠንቅቀዋል፡፡

9. በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን የላይ ጋይንት ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ትናንት ማንታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች እንደተገደሉ የክልሉ ብዙኻን መገናኛ ዘግቧል፡፡ አስተዳዳሪው ታረቀኝ ዮሴፍ የተገደሉት ከቢሯቸው ውጭ መንገድ ላይ ነው፡፡ ፖሊስ ገዳዮችን ለመያዝ ክትትል እያደረገ ነው፡፡

10. ሱማሊያ የበረሃ አንበጣን ጉዳት እንድትቋቋም ዐለም ባንክ ዛሬ 40 ሚሊዮን ዶላር አስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ እንዳጸደቀ ባንኩ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል፡፡ የአንበጣ መንጋው በ2.6 ሚሊዮን የሀገሪቱ ዜጎች ምግብ ዋስትና ላይ አደጋ ደቅኗል፡፡ ገንዘቡ ተጎጅ አባውራዎች የአስቸኳይ ምግብ አቅርቦት እንዲያገኙ እና ጥሪታቸውን እንዳያጡ ይከፋፈላል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.