የለንደን ፖሊስ የአጼ ኃይለ ሥላሴ ሐውልትን ያፈረሱትን እየተከታተለ መሆኑን አስታወቀ

በደቡብ ምዕራብ ለንደን ዊምብሌደን በሚገኝ ፓርክ የነበረው የቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ አጼ ኃይለ ሥላሴ ሐውልት በተወሰኑ ሰዎች መፍረሱ ይታወቃል፡፡

ፖሊስም ማክሰኞ ዕለት ምሽት በካኒዛሮ ፓርክ የተፈጠረውን ይህንን ወንጀል እየመረመረ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ሐውልቱ ያፈረሱት 100 የሚጠጉ ሰዎች አንድ ላይ በመሰባሰብ እንደሆነ የዐይን እማኞች ተናግረዋል፡፡

የዊምብልደን ነዋሪ የሆኑት አንድሪው ሞሪስ፤ ከውሻቸው ጋር የእግር ጉዞ እያደረጉ ሳለ በፓርኩ ውስጥ የተሰባሰቡ ሰዎች መመልከታቸውንና ግለሰቦቹ መፈክሮችን እና በራሪ ወረቀቶችን ይዘው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

አንድሪው አክለውም ሐውልቱ ሲፈርስ ድምጽ መስማታቸውን ጠቅሰው ምን እንደተፈጠረ ግን በዐይናቸው አለማየታቸውን አስረድተዋል፡፡

የከተማዋ ፖሊስ መረጃ የማሰባሰብና የምርመራ ሂደቱ እንደቀጠለ መሆኑንና እስካሁን ግን በቁጥጥር ሥር የዋለ ሰው እንደሌለ ገልጿል፡፡

ድርጊቱ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ ከተፈጠረ ተቃውሞ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

የድምጻዊውን መገደል ተከትሎም በሐረር የሚገኘው የአጼ ኃይለ ሥላሴ አባት ልዑል ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል ሐውልትም ለታቃውሞ በወጡ ቡድኖች ፈርሷል፡፡

አጼ ኃይለ ሥላሴ በጎርጎሮሳዊያኑ 1936 የጣሊያንን ወረራ ተከትሎ ለስደት እንግሊዝ ባመሩበት ወቅት የቆዩት እንግሊዝ ውስጥ ነበር፡፡ በዚያም ከእውቋ እንግሊዛዊት ቀራጺና ደራሲ ቤተሰቦች ጋር ይኖሩ በነበረበት ወቅት ሐውልታቸው በቀራጺዋ የተሰራ ሲሆን በኋላ ላይም በካኒዛሮ ፓርክ እንዲቆም ተደርጓል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በድምጻዊው ሞት የተቆጡና ብረትና ተቀጣጣይ ነገር ያዙ ወጣቶች በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዳያስፖራና የሚዲያ ኃላፊ የሆኑት አቶ ያለው ከበደ ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ወጣቶቹ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማን በማውረድ ለማቃጠል መሞከራቸውን በምትኩ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሰንደቅ አላማ መስቀላቸውንና በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ጨምረው አስረድተዋል።

በኤምባሲው የቆንስላ ክፍል ውክልና ለመስጠት መጥቶ የነበረ አንድ ተገልጋይን ሲወጣ በማግኘት መደብደባቸውንም ጨምረው ተናግረዋል።

የወጣቶቹ ዋና አላማ ኤምባሲው በመግባት ጉዳት ማድረስ እንደነበር ያመላከቱት አቶ ያለው ተቀጣጣይ ነገርና ብረት ይዘው እንደነበር ለቢቢሲ አስረድተዋል፡፡

1 COMMENT

  1. አይ የነጻነት ጥያቄ እንደ እንቁራሪት አንድ ሲጮህ አብሮ መጮህ። በራስ አስቦ ነገር አመዛዝኖ መኖር አለመቻል እንዴት አለመታደል ነው። የኦሮሞ ጽንፈኛ ፓለቲከኞች ከወያኔ ጋር በማበር ሃገሪቱን አፍርሰው ሪፕብሊኳን ኦሮሚያ ለመገንባት በሃገርም በውጭም ሰው ማመስ መንገድ መዝጋት፤ ንብረት ማውደም ስራዬ ብለው ይዘውታል። እኔ እንግሊዞችን ብሆን ጠፍሬ ወደ እየመጡበት ነበር የምልካቸው። እዚያው በሃገራቸው ላይ ይፋለሙ። እንዴት ሰው ግን አእምሮውን አጥቷል?
    የሃይለሥላሴን ሃውልት በለንደን፤ የአባታቸውን በሃረር የሚያፈርሱት እነዚህ እቡዪች እውነትን ለማወቅ አይፈልጉም። ማን ነው ሃጫሉን የገደለው? ማን ነው እልፍ ሰዎችን በየስፍራው በቆንጨራና በእሳት እየለበለበ የገደለው? ማን ነው ሰዎችን ወደ ገደል የወረወረው? እስቲ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ይመስክር። ሌላው ኢትዮጵያዊ እነዚህን የቁም በድኖች ዝም ብሎ ማየት የለበትም። በህግ ሁሉንም መስመር ማስገባት ይቻላል። ለምሳሌ ከውጭ ሆነው ሰው እንዲጫረስ በገንዝብም ሆነ በሃሳብ የሚቆሰቁሱትን በመረጃ በተደገፈ ክስ መመስረትና ከሃገር ሁሉ እንዲባረሩ ማድረግ ይቻላል። ይሂድና እዛው በጎጣቸው ያቅራሩ። ውጭ ሃገር ተኖረ፤ ሃገር ውስጥ ተኖረ የአስተሳሰብ ለውጥ አልተገኘ። ዝም ብሎ መናቆር ነው።
    የጊዜውን መምሸትና የወያኔ የዘር ፓለቲካ እንዴት ሥር እንደ ሰደደ ለማየት በሃጫሉ ሞት እልል የሚሉ፤ ትግሬን ግደል፤ አማራን ግደል በማለት ቅስቀሳ የሚያደርጉ በየድህረ ገጾች ተለጥፈው ማየት ሃበሻ መሆንን ያስጠላል። ታዲያ እኛ ችጋራም ብንሆን ይፈረዳል? እንደ በረሃ እንስሳ በየዘራችን ተሰልፈን ሰው መሆናችን የጠላን? ዝንተ ዓለም ስንገዳደል የምንኖር። የለንደን ፓሊስ እነዚህን የጅምላ ፓለቲከኞች አድኖ ህግ ፊት በማቅረብ ቅጣት እስካልሰጣቸው ድረስ ነገ ሰው ይገድላሉ፤ ቤት ያቃጥላሉ፤ ሌላም ነገር ያደርጋሉ። ችግሩ የአስተሳሰብ እንጂ የፓለቲካ ቁጣ አይደለም። ግን እኮ እነዚህ የፓለቲካ እብዶች የሃጫሉን አጎት በአምቦ የገደሉ ናቸው። የሚገርመው ኦነግ፤ ኦፌኮ ወዘተ የሚባሉት የኦሮሞን ህዝብ መብት እናስጠብቃለን የሚሉት ሁሉ የሰጡት መግለጫ ከራሱ ጋር የሚጋጭ መሆኑ ነው። ግን ሞኝነት ነው እንጂ ማንም ቢሆን ዝም ብሎ እንደ ከብት እየታረደ አይሞትም። ግን ጥገኝነት የሰጣቸውን ሃገር የሚያምሱ እነዚህ ወደ ሃገራቸው ተመልሰው በዚያው እንደፈለጉ ቢሆኑ ላስጠለላቸው ሃገር እፎይታ ይሆናል። ችግሩን የሚያባብሰው ሶሻል ሚዲያ ነው። የፈጠራም ሆነ እውነትነት ያለውን ቪዲዮ በመጫን ገንዘብ የሚገኝበት መንገድ እስካልከሰመ ድረስ ሰው በሰው ደምና ሰቆቃ መነገድ አይቀሬ ነው። ችግሩ የሃውልት መፍረሱ አይደለም። ያስተሳሰባችን ድክመት እንጂ። እያደርን ቁልቁል። አታድርስ ነው!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.