የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ የቀብር ሥነ ሥርዓት አምቦ ውስጥ ተፈጸመ

የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ የቀብር ሥነ ሥርዓት በአምቦ ከተማ በሚገኘው የገዳመ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተፈጸመ።

ይሁን እንጂ አሁንም ድምጻዊው መቀበር ያለበት በአዲስ አበባ ነው በሚል ተቃውሟቸውን የሚያሰሙ በርካቶች ናቸው።

ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በመገኘት ሽኝት አድርገዋል።

በስታዲየሙ የተገኘው ሰው ቁጥር አነስተኛ እንዲሆን የተደረገው በደኅንነት ስጋት መሆኑ ተነግሯል።

• ከሃጫሉ ግድያ በኋላ ቢያንስ የ67 ሰዎች ህይወት መጥፋቱ ተገለጸ

• የሰኔ 15ቱ አይነት ግድያን ለመድገም ታቅዶ እንደነበር የፌደራል ፖሊስ ገለፀ

• በአምቦ የሃጫሉ አጎትን ጨምሮ አምስት ሰዎች መሞታቸው ተነገረ

ለቀብር ከአምቦ ዙሪያ የሚመጡ ሰዎች ወደ ከተማው እንዳይገቡም ተከልክለዋል። የመንግሥት የጸጥታ ኃይል መንገደኞች ወደ ከተማው እንዳይገቡ እና ወደ መጡበት እንዲመለሱ ለማድረግ አስለቃሽ ጭስ ሲተኩስ ነበር ተብሏል።

አንዳንድ ሰዎችም አስከሬኑ ወደሚቀበርበት ቦታ የሚወስዱ መንገዶችን የመዝጋት ሙከራዎች እንደነበሩና ቀብሩ ሊፈጸም የነበረበት ጉድጓድን መልሶ የመድፈን ሙከራዎችም መደረጋቸውንም የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ትናንት በጥይት ተመትተው ህይወታቸው ያለፈው የሃጫሉ አጎት ቀብር በዛሬው ዕለት ቀደም ብሎ ተፈጽሟል።

ከአምቦ ከተማ ነዋሪዎች እንደሰማነው የክልሉ ፕሬዝድንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ይገኛሉ ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም መገኘት አለመቻላቸውን ተነግሯል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.