ለቸኮለ! የዛሬ ሰኞ ሰኔ 29/2012 የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1. የድምጻዊ ሐጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ ነውጠኞች በአርሲ ዞን በፈጸሙት ጥቃት 23 ሰዎች እንደሞቱ ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል፡፡ 2 የዞኑ ፖሊስ አና ሚሊሽያ አባላት ናቸው፡፡ ጥቃት አድራሾቹ ገጀራ፣ ስለት እና ዘመናዊ ጦር መሳሪያ ተጠቅመዋል፡፡ ቀርሳ ሙኔሳ፣ አርሲ ነገሌ፣ ዴራ፣ ቀርሳ በተባሉ አካባቢዎች፣ ነዋሪዎች በሐይማኖት እና ብሄር እየተለዩ እንደተጠቁ ይናገራሉ፡፡ ከጥቃቱ ያመለጡት በቤተክርስቲያናት ተጠልለዋል፤ የአስተዳደር አካላት ግን እስካሁን አላናገሯቸውም፡፡
2. የድምጻዊ ሐጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ ሻሸመኔ ከተማ ከባድ ውድመት እንደደረሰባት ቪኦኤ ንብረት የወደመባቸውን ባለሃብቶችን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ የአትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴን ሆቴል ጨምሮ፣ በርካታ ሆቴሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ መደብሮች፣ መኖሪያ ቤቶች እና ሕንጻዎች ወድመዋል፡፡ አብዛኛዎቹ የጥቃት ሰለባዎች የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ ያልሆኑ ዜጎች ናቸው፡፡
3. በኦሮሚያ ክልል በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ጥቃት በማድረስ የተጠረጠሩ ከ1 ሺህ 80 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌታቸው ባልቻ ለአባይ ሜዲያ ተናግረዋል፡፡ ፖሊስ እና ልዩ ሃይል ጥቃቱን ለመከላከል ጥረት አድርገዋል፤ የጸጥታ ክፍተቶች ግን ወደፊት ይገመገማሉ- ብለዋል ኮሚሽነሩ፡፡ ጥቃቱ በበርካታ ብሄረሰቦች አባላት ላይ የተፈጸመ በመሆኑ፣ የዘር ማጥፋት ብሎ መፈረጅ እንደሚያስቸግርም ገልጠዋል፡፡
4. በአማራ ክልል ኦሮሚያ ልዩ ዞን የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ጥቃት እንደፈጸሙ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ ለብሄራዊ ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡ ጥቃቱ የተፈጸመው በደዌ አረዋ ወረዳ እና ባቲ ከተማ ነው፡፡ በባቲ ከተማ ታጣቂዎቹ በጣሉት ቦምብ 5 ሰዎች ቆስለዋል፡፡ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በተደረገ ተኩስ ልውውጥ የቡድኑ መሪ ሲገደል፣ የተወሰኑ ታጣቂዎች ተይዘዋል፡፡
6. በኢትዮጵያ በተፈጠረው ሁከት የሟቾች እና ታሳሪዎች መብዛት እንዳሳሰበው የጀርመን ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ መግለጹን DW ዘግቧል፡፡ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ልዩነታቸውን ከሃይል በመለስ በውይይት ብቻ እንደፊቱ መስሪያ ቤቱ አሳስቧል፡፡ ሃይል የተቀላቀለበት አምጽ ግን ተገቢውን ርምጃ ይሻል፡፡ መንግሥት የጀመራቸው የለውጥ ሂደቶች ቀጣይነት አስፈላጊ እንደሆነ መግለጫው ጠቁሟል፡፡
7. ትናንት ወደ ግብጽ ያቀኑት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ዛሬ ከግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ጋር ተገናኝተው እንደተወያዩ ቃል አቀባያቸው የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡ ሁለቱ መሪዎች የሁለትዮሽ ትብብሮችን ለማጠናከር እና የጋራ ጥቅሞቻቸውን የሚያስጠብቁ ርምጃዎችን ለመውሰድ ተስማምተዋል፤ ቀጠናዊ ውጥረቶች በፈጠሩት ችግር ላይም ተነጋግረዋል፡፡
8. የአፍሪካ ኅብረት ኮሚቴ እና ታዛቢዎች ከኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ ጋር በተናጥል እንደሚመክሩ ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል፡፡ የተናጥል ውይይቱ የታቀደው፣ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር ዐርብ እና ቅዳሜ በተካሄዱት የሦስትዮሹ ድርድሮች ውጤት ስላልተገኘባቸው እንደሆነ ዘገባው ገልጧል፡፡
9. በግንቦት ወር ከግብጽ ወደ ሱማሊያ በአውሮፕላን የተጓጓዘ ጦር መሳሪያ ጭነት ወደ ግብጽ ተመላሽ እንደተደረገ ቴሌግራፍ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ አውሮፕላኑ 2 ሺህ ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎች፣ ሮኬት ማስተኮሻዎች፣ አልሞ መተኮሻ ጠመንጃዎች፣ ሽጉጦች እና ሞርታሮችን የጫነ ነበር፡፡ የጦር መሳሪያው የመጨረሻ መዳረሻ የት እንደታሰበ ግን ዘገባው አልገለጸም፡፡ ሆኖም ወደ ግብጽ ተመላሽ የተደረገው ሱማሊያ የኢትዮጵያ እና ግብጽ ፍጥጫ አካል መሆን ስለማትፈልግ እንደሆነ ጠቅሷል፡፡
10. የሱማሊያ 5 ፌደራል ክልሎች ለቀጣዩ ጥቅምት በተያዘው የፓርላማ ምርጫ ላይ በመጭው ሐሙስ በጋራ እንደሚመክሩ ሬዲዮ ዳልሳን ዘግቧል፡፡ በስብሰባው ፌደራል መንግሥቱ አይሳተፍም፡፡ ስብሰባውን የጠሩት ፑንትላንድ እና ጁባላንድ ራስ ገዞች እና ሌሎች 3 የፌደራሉ ክልሎች ናቸው፡፡ የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ኮሮና ወረርሽኝን እና የጸጥታ ችግሮችን በመጥቀስ፣ የጥቅምቱ ምርጫ ወደ ቀጣዩ የፈረንጆች ዐመት መጋቢት ወር እንዲራዘም ከሳምንት በፊት ለፓርላማው ጥያቄ
አቅርቧል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.