ለቸኮለ! የዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 30/2012 የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1. ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ዛሬ ለፓርላማው ቀርበው ስለ ቀጣዩ ዐመት በጀት፣ ስለ አባይ ግድብ እና ሌሎች ጉዳዮች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል እየተጠራ ስላለው አመጽ ተጠይቀው፣ በውጭ ሀገር ተቀምጠው አምጽ ማነሳሳት አንዳችም ድል እንደማያስገኝ ተናግረዋል፡፡ ያለቀው ሕዝብ ያልቃል እንጅ ከብልጽግና ጉዟችን አንገታም፤ እናም አመጽ የሚጠሩ ሃይሎች ቆመው ማሰብ አለባቸው ብለዋል፡፡ ለ30 ዐመታት ለኦሮሞ ብሄር ነጻነት ታግያለሁ፤ አሁን ሕዝቡ ነጻነቱን ስላገኘ የሚያስፈልገው ብልጽግና ብቻ ነው በማለትም አክለዋል፡፡
2. የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጥልቅ ግምገማ ሊጀምር እንደሆነ ዋዜማ ሰምታለች፡፡ ግምገማው በፓርቲው ውስጥ መሃል ሰፋሪዎችን እና ከሽብር ቡድኖች ጋር የዐላማ ትስስር ያላቸውን በመለየት እና ማስወገድ ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ እና በመከላከያ ሚንስትር ለማ መገርሳ መካከል ያለው ልዩነት አለመፈታቱ፣ በፓርቲው ውስጥ ጥርጣሬ እንዲሰፍን አድርጓል፡፡ ለማ አቤቱታቸውን ግምገማ ላይ የማቅረብ ፍላጎት እንዳላቸው ተሰምቷል፡፡ Link-https://bit.ly/38vFiRB
3. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬ ስበሰባው የ2013 ዓ.ም በጀትን ዛሬ አጽድቋል፡፡ ውይይት ሲካሄድት ከርሞ ዛሬ የጸደቀው በጀት 476 ቢሊዮን 12 ሚሊዮን ብር ያህል ነው፡፡ ለአዲሱ ሲዳማ ክልልም በጀት ተይዞለታል፡፡
4. መንግሥት የጥላቻ ቅስቀሳ የሚያደርጉ መገናኛ ብዙኻንን ከሥርጭት ለማሳገድ እንቅስቃሴ መጀመሩን ዋዜማ ሰምታለች፡፡ በውጭ ሀገራት ተመሳሳይ ድርጊት ላይ የተሠማሩ መገናኛ ብዙኻንም ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድባቸው ለማድረግ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አዳነች አቤቤም ትናንት በሰጡት መግለጫ ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡ የትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ጣቢያ እና ድምጸ ወያኔ ትናንት ሥርጭታቸውን ከሚያስተላልፉበት የፈረንሳይ ሳተላይት እንደወርዱ እንደተደረጉ ቢገልጹም፣ ብሮድካስት ባለስልጣን ግን እጄ የለበትም ይላል፡፡
5. ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ዛሬ ለፓርላማው በሰጡት ማብራሪያ፣ ኢትዮጵያ ዘንድሮ የሕዳሴ ግድብን ውሃ ካልሞላች፣ ግደቡ እንዲፈርስ እንደወሰነች ይቆጠራል ሲሉ መናገራቸውን DW ዘግቧል፡፡ የሦስተዮሹ ድርድር ውጤት እያሰገኘ እንደሆነም በማብራሪያቸው አውስተዋል፡፡ መንግሥት የውጭ ጫናን በመከላከል እና ድርድሩን ወደ አፍሪካ ኅብረት በማምጣት ረገድ ትኩረት ሰጥቶ ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን ሰርቷል፡፡
6. በድምጻዊ ሐጫሉ ግድያ 10 ተጨማሪ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አዳነች አቤቤ ትናንት በብሄራዊ ቴሌቪዥን በተላለፈ መግለጫቸው ተናግረዋል፡፡ ቀደም ሲል ከተያዙት 4 ሰዎች ጋር በድምሩ 14 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ግድያው ታስቦበት በዝግጅት የተፈጸመ እንደሆነ መረጃዎች ተገኝተዋል፡፡ ወደ አምቦ ጉዞ ጀምሮ የነበረውን የሟቹን አስከሬን ወደ አዲስ አበባ አስገድደው የመለሱ ሃይሎች፣ ጦር መሳሪያ እና መገናኛ ዘዴዎችን ተጠቅመዋል፡፡
7. ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በ6 ወረዳዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች የ34 ሰዎች ሕይወት እንደጠፋ ቪኦኤ የዞኑን አስተዳደር ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ ጥቃት ፈጻሚዎቹ ለጥቃት የተሰማሩት ስም ዝርዝር ይዘው ነው፡፡ ባብዛኛው ጥቃቶቹ የተፈጸሙት ሐይማኖት እና ብሄር በመለየት ነው፡፡ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ግን ሟቾቹ ከአማራ ብሄረሰብ ብቻ ሳይሆኑ፣ ከሌሎች ብሄረሰቦች ጭምር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ጥቃቱ ከጸጥታ ሃይሎች አቅም በላይ እንደነበርም አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡
8. በኦሮሚያ ክልል ወጣቶች (ቄሮ)ሌላ ዙር አመጽ እንደጠሩ በውጭ ሀገራት ያሉ ኦሮሞ ብሄርተኞች በማኅበራዊ ሜዲያ በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ አመጹ ያነጣጠረው ከኦሮሚያ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚያመሩ ዋና ዋና መንገዶችን መዝጋት ላይ ነው፡፡ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አዳነች አቤቤ ትናንት በሰጡት መግለጫ ግን፣ ከሀገር ውጭ የጥፋት ጥሪ የሚያደርጉ አካላትን ጭምር ለሕግ እናቀርባለን ብለዋል፡፡
9. የትግራይ ክልል ምክር ቤት ትናንት የምርጫ እና የምርጫ ስነ ምግባር ረቂቅ አዋጆችን እንዳጸደቀ DW ከስፍራው ዘግቧል፡፡ ምክር ቤቱ አዋጆቹን ያጸደቀው፣ ክልላዊውን ምርጫ እስከ መስከረም ለማካሄድ ቀደም ሲል በወሰነው መሠረት ነው፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]

https://youtu.be/CW21AATlKT4

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.