ለቸኮለ! የዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 1/2012 የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1. የድምጻዊ ሐጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ፣ በኦሮሚያ ክልል 239 ሰዎች እንደሞቱ የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ የክልሉን ተጠባባቂ ፖሊስ ኮሚሽነር ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ 14ቱ የፖሊስ እና ሚሊሽያ አባላት ናቸው፡፡ በሁከቱ የተጠረጠሩ 3 ሺህ 500 ሰዎች ደሞ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ሃላፊነታቸውን ባግባቡ ያልተወጡ ጸጥታ አካላትን የመለየት ሥራ እየተሰራ ነው፡፡
2. የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ትናንት ለድምጻዊ ሐጫሉ ግድያ ሕወሃትን ተጠያቂ የሚያደርግ መግለጫ አውጥቷል፡፡ ሕወሃት በድምጸ ወያኔ አመጽ ሲቀሰቅስ ሰንብቷል፤ የሕዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌት እንዲሰናከል በሚያደርግ የባንዳነት ተግባር ላይ ተሰማርቷል- ብሏል በኢቢሲ የተሰራጨው መግለጫው፡፡ ኦነግ ሸኔ እና ሕወሃት በትብብር እየሰሩ እንደሆነም መግለጫው ጠቁሟል፡፡ ለተፈጸመው ወንጀል የሕግ የበላይነት ብቻ እንጅ ሽምግልና ቦታ አይኖረውም፡፡ በመግለጫው በሕወሃት/ኢሕአዴግ ዘመን በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ዘርዝሯል፡፡
3. ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ዛሬ በሰጠው መግለጫ በሃሰት ውንጀላ የታሰሩ አመራሮቹ ሕክምና እንዳላገኙ መግለጹን ዘግቧል፡፡ የፓርቲው ሊቀመንበር እስክንድር ነጋ እና ምክትሉ ስንታየሁ ቸኮል በፖሊስ ሲያዙ ድበደባ እንደተፈጸመባቸው ቀደም ሲል ፓርቲው አስታውቆ ነበር፡፡ አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት ፓርቲ በበኩሉ በሰጠው መግለጫ፣ ከሰሞኑ ቀውስ ጋር አንዳች ግንኙነት ሳይኖራቸው የታሰሩት አመራሩ ይልቃል ጌትነት ባስቸኳይ እንዲለቀቁ ጠይቋል፡፡ ይልቃል ከታሰሩ ጀምሮ ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡም ገልጧል፡፡ መንግሥት ፕሮፓጋንዳውን ትቶ የዜጎችን ደኅንነት እንዲያስጠብቅም ፓርቲው አሳስቧል፡፡
4. ግብጽ ለሕዳሴ ግድብ ውዝግብ አዲስ ሃሳብ እንዳቀረበች ዐረብ ኒውስ ዘግቧል፡፡ ግብጽ አዲሱን ሃሳብ ያቀረበችው የኢትዮጵያን ውሃ ይዞታ እና ሕዝቡ ለሕዳሴ ግድብ ያለውን ስሜት ካጠናች በኋላ ነው፡፡ ምክረ ሃሳቡ ግብጽ ኢትዮጵያ ማመንጨት የምትፈልገውን ሃይል የሚያሳካ፣ በ2015ቱ መርሆዎች መግባቢያ ማዕቀፍ በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገሮች ላይ ከባድ ጉዳት አለማድረስን የሚጠይቅ እና ወደፊት ናይል ላይ የሚገነቡ ፕሮጀክቶች ከዐለም አቀፍ ሕግ ጋር የተናበቡ እንዲሆኑ የሚጠይቅ ነው- ብሏል ዘገባው፡፡ ግብጽ ከላይኛው የወንዙ ተፋሰስ ሀገራት ጋር የሚያስተሳስራትን መሰረተ ልማት በገንዘብ የመደገፍ ፍላጎት አላት፡፡
5. ሰሞኑን ደም አፋሳሽ ሁከት በተቀሰቀሰባቸው የኦሮሚያ ክልል ከተሞች የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጤና ሚንስቴር መግለጹን ቪኦኤ ዘግቧል፡፡ በመጭዎቹ ቀናት ሚንስቴሩ በእነዚህ አካባቢዎች የሚመረምራቸውን ናሙናዎች ቁጥር ያሳድጋል፡፡ ሰሞኑን ሁከት በተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች የምርመራው መጠን ቀንሶ ሰንብቷል፡፡
6. በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች የኩፍኝ ወረርሽኝ እንደተከሰተ ጤና ሚንስቴር ሊያ ታደሠ በሰጡት መግለጫ ማስታወቃቸውን ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል፡፡ በወረርሽኙ ተጋላጭ የሆኑት ከ5 ዐመት በታች ያሉ ሕጻናት ናቸው፡፡ ለወረርሽኙ መስፋፋት ምክንያት ከሆኑት ውስጥ፣ አለመከተብ እና ክትባትን ጀምሮ ማቋረጥ ይገኙበታል፡፡ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ክትባቱ በሁሉም ክልሎች እየተሰጠ ነው፡፡ እስካሁን ከ5 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ተከትበዋል፡፡
7. ኬንያ አሚና ሞሐመድን ለዐለም ንግድ ድርጅት ዳይሬክተር ጄነራልነት ዕጩ አድርጋ እንዳቀረበች ዘ ኢስት አፍሪካን ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ ከ7 ዐመት በፊት ተፎካካሪያቸው የነበሩት ብራዚላዊው የድርጅቱ ዳይሬክተር የሥልጣን ዘመናቸው ከማለቁ በፊት በመጭው ነሐሴ ከሃላፊነት ይለቃሉ፡፡ አሚና ካሁን ቀደም የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሆነው ያገለገሉ ናቸው፡፡ ዕጩ ካቀረቡ 6 ሀገሮች መካከል ግብጽ ትገኝበታለች፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.