ለቸኮለ! የዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 2/2012 የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1. መንግሥት ኢንተርኔት እና ስልክ ብሎም የትግራይ ክልል፣ ድምጸ ወያኔ እና ቻናል 29 ቴሌቪዥን ጣቢያዎችን መዝጋቱን የሕወሃት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ትናንት ባወጣው መግለጫ ኮንኗል፡፡ ሥልጣን የያዘው አምባገነን አሃዳዊ ቡድን ሀገሪቱን ወደ መፈራረስ እየወሰዳት እንደሆነ ጠቅሷል፡፡ ከሰላማዊ ፖለቲካው የተገፉ ሃይሎች ሌሎች አማራጮችን እየፈለጉ ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ በተጠንቀቅ በመቆም፣ ከአሃዳዊ ቡድኖች የተቃጣበትን ጥቃት እንዲመክትም ጥሪ አቅርቧል፡፡
2. የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ሰሞኑን በሀገሪቱ ለተፈጠረው ሁከት እና ግድያ ታሪካዊ ዳራ የሚሰጥ መግለጫ ትናንት አውጥቷል፡፡ አንዳንድ የግል እና የክልል መገናኛ ብዙኻን እና ጸረ ሰላም ሃይሎች ጠቅላይ ሚንስትሩ የጥንቱ ነፍጠኛ ሥርዓት አራማጅ እንደሆኑ ቅስቀሳ ማድረጋቸውን መግለጫው አትቷል፡፡ ይህን የሃሰት ትርክት በተለይ በአሜሪካ እና አውሮፓ የሚኖሩ ግለሰቦች በኦሮሞ እና አማራ ብሄሮች መካከል ግጭት ለመቀስቀስ አውለውታል፡፡ በአማራ ላይ በሄር ተኮር ጥቃቶች የታዩትም፣ ወጣቶች አማራን ከነፍጠኛ ጋር እንዲያስተሳስሩ በመደረጋቸው ነው፡፡ አሁን መንግሥት ሁኔታውን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረው በመሆኑ፣ በሀገሪቱ ተቃውሞዎች እንዳሉ የሚወራው የሁከት ፈጣሪ ሃይሎች ወሬ ብቻ ነው- ብሏል መግለጫው፡፡
3. በኦሮሚያ ክልል የሻሸመኔ ከንቲባ ተማም ሁሴን እና የጸጥታ እና አስተዳደር ሃላፊው ናደው አምቦ ትናንት በቁጥጥር ስር እንደዋሉ DW የከተማዋን አስተዳደር ምንጮች ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ ባለፈው ሳምንት በከተማዋ ነውጠኞች ከባድ የንብረት ውድመት ሲያደርሱ እና ሕይወት ሲያጠፉ፣ ሁለቱ ሃላፊዎች ሃላፊነታቸውን ባግባቡ አልተወጡም ተብለው ተጠርጥረዋል፡፡
4. በሰሞኑ ሁከት ከ4 ሺህ 700 በላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር እንደዋሉ የጠቅላይ ሚንስትሩ ቃል አቀባይ ንጉሱ ጥላሁን ትናንት በብሄራዊው ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ተጠርጣሪዎች በአዲስ አበባ ዙሪያ እና ኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ሁከቱን ያቀዱ፣ የመሩ እና የተሳተፉ ናቸው፡፡ ድምጻዊ ሐጫሉን የገደሉ ሃይሎች የውጭ ተልዕኮ ወሰዱ ናቸው፡፡ መንግሥት የደረሰውን ጉዳት እና ወደፊት መወሰድ ያለበትን ርምጃ የሚያጠና አንድ ቡድን ተዋቅሯል፡፡
5. የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሰላም ስምምነት ከተፈረመ ዛሬ 2ኛ ዐመቱን ደፍኗል፡፡ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ቃል አቀባይ የማነ ገ/መስቀል በትዊተር ገጻቸው ባሠፈሩት መልዕክት፣ ሕወሃት በእኩይ ድርጊቱ የተገኘውን ሰላም ለመቀልበስ ቢሰራም፣ እስካሁን የተገኙት ውጤቶች ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው ብለዋል፡፡ መፍትሄ ያላገኙ ከባባድ ፈተናዎች ቢኖሩም፣ ከሁለቱም በኩል ባለው የፖለቲካ ፍቃደኝነት ወደፊት ይፈታሉ፡፡
6. የሕዳሴ ግድብ ሦስትዮሽ ድርድር ዛሬም ለሰባተኛ ቀን ቀጥሎ ውሏል። ባሁኑ ዙር ድር ድር ማብቂያ፣ ተደራዳሪዎች የደረሱበትን ውጤት ለአፍሪካ ኅብረት ሪፖርት ያደርጋሉ። ግብጽ ሁሉን ዐቀፍ ያልሆነ ስምምነት ላይ ላለመድረስ አቋም ይዛለች። በተያያዘ፣ ሩሲያ ለውዝግቡ ጠዋሚ ቴክኒካዊ ድጋፍ ለመስጠት ሦስቱን ሀገራት እንደጠየቀች የግብጹ ዴይሊ ኒውስ ዘግቧል።
7. በቀደም ከሳተላይት እንደወረደ ገልጦ የነበረው የትግራይ ክልል ቴሌቪዥን በሌላ ሳተላይት ተመልሻለሁ ብሏል። ጣቢያው ከሳተላይት ያስወረደው መንግሥት እንደሆነ ገልጾ ነበር። ይህንኑ ውንጀላ የሕወሃት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴም ትናንት ባወጣው መግለጫ ደግሞታል።
7. ፑንትላንድ እና ጁባላንድ ራስ ገዞችን ጨምሮ የ5 የሱማሊያ ፌደራል ክልሎች ፕሬዝዳንቶች ዛሬ የጋራ ስብሰባ እንደተቀመጡ የሀገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል፡፡ ክልላዊ ፕሬዝዳንቶቹ የሚወያዩት የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ወደ ቀጣዩ የፈረንጆች ዐመት እንዲተላለፍ በቅርቡ ሃሳብ ባቀረበበት በጥቅምት በታቀደው ሀገር ዐቀፍ ፓርላሜንታዊ ምርጫ ላይ ነው፡፡ ክልሎቹ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ቅራኔ ውስጥ ያሉ ናቸው። [ዋዜማ ራዲዮ]

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.