ለቸኮለ! የዛሬ ዐርብ ሐምሌ 3/2012 የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1. ድምጻዊ ሐጫሉ ሁንዴሳን በመግደል የተጠረጠሩ 2 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አዳነች አቤቤ ዛሬ በብሄራዊው ቴሌቪዥን ቀርበው ተናግረዋል፡፡ ሐጫሉን በጥይት ተኩሶ በመግደል የተጠረጠረው ጥላሁን ያሚ፣ አብዲ ዐለማየሁ ከተባለ ተባባሪው ጋር ተይዟል፡፡ ሁለተኛውን ተባባሪውን ከበደ ገመቹን ደሞ ፖሊስ ገና እያደነው ነው፡፡ ዋና ተጠርጣሪው የግድያ ተልዕኮውን የተቀበለው ከኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን እንደሆነ ለፖሊስ ቃሉን ሰጥቷል፡፡
2. በኦሮሚያ ክልል አርሲ እና ባሌ ዞኖች ስለደረሱት ገድያዎች እያጣራ እንደሆነ ሂውማን ራይተስዎች ገልጧል፡፡ መንግሥት ኢንተርትን መዝጋቱ ግን በድርጅቱ ሥራ ላይ ብዙ ችግሮች ፈጥሯል፡፡ በዜጎች ላይ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መከላከል ግን የመንግሥት ሃላፊነት መሆኑን፣ የድርጅቱ አፍሪካ ቀንድ ሃላፊ ላቲሺያ ባይደር ለቪኦኤ በሰጡት ቃል አስምረውበታል፡፡
3. በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ በባሌ እና አርሲ ዞኖች ባሉ ከተሞች የተጠለሉ ተፈናቃዮች መንግሥት እንዲደርስላቸው ጥሪ እያደረጉ እንደሆነ ኢሳት ዘግቧል፡፡ በባሌ ዞን አጋርፋ ኮሌጅ ከ1 ሺህ በላይ ዜጎች እስካሁን ከመንግሥት የምግብ እና አልባሳት ዕርዳታ እንዳላገኙ ተናግረዋል፡፡ ነውጠኞች በርካታ ሰዎችን በእሳት አቃጥለዋል፤ በግፍ የተገደሉ ዜጎችን እንዳይቀብሩ ከልክለዋቸዋል፡፡ አሁንም የደኅንነት ዋስትና እንደሌላቸው እየታወቀ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ግፊት እየተደረገባቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
4. ወደ ሕዳሴ ግድብ ውሃ መግባት እንደጀመረ ቪኦኤ ከሳተላይት ምስሎች ማየቱን ጠቅሶ ትናንት ዘግቧል፡፡ መንግሥት ግን ዘገባውን አላረጋገጠም፡፡ ከግብጽ በኩልም የተሰማ አዲስ ነገር የለም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በአፍሪካ ኅብረት አስተናባሪነት የሚካሄደው የሦስተዮሹ ድርድር ቀጥሏል፡፡ ተደራዳሪዎች ድርድሩን በተቀመጠው ገደብ በያዝነው ሳምንት ሲያጠናቅቁ፣ የደረሱበትን ውጤት ለኅብረቱ መሪዎች ኮሚቴ ያቀርባሉ፡፡
5. መንግሥት በመላ ሀገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎትን ከዘጋ ዛሬ 10ኛ ቀኑን ይዟል፡፡ በዛሬው ዕለት ግን፣ ፋና ብሮድካስት ቴሌቪዥን በፌስቡክ ሥርጭት መጀመሩን ተመልክተናል፡፡ ለውጭ ሀገራት ኢምባሲዎች ኢንተርኔት እንደተለቀቀላቸው የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ ትናንት ተናግረው ነበር፡፡ ኢንተርኔቱ መቼ ሙሉ በሙሉ እንደሚለቀቅ መንግሥት አሁንም ቁርጥ ያለ ቀን አልሰጠም፡፡
6. ለአሜሪካው ዜና ማሰራጫ ቪኦኤ የሚሰሩ የውጭ ሀገር ዜጎች የሆኑ ጋዜጠኞችን ቪዛ ከእግዲህ እንደማያድስ የአሜሪካ ብሮድካስቲንግ ኤጀንሲ መወሰኑን ኤንፒአር ዘግቧል፡፡ ቪኦኤ በኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አማካኝነት ከሀገረ አሜሪካ ከሚያሰራጫቸው የሬዲዮ ሥርጭቶች ውስጥ፣ የአማርኛ፣ ትግሬኛ እና ኦሮምኛ ቋንቋ ሥርጭቶች ይገኙበታል፡፡ ኤጀንሲው ለዘገባው ማረጋገጫ አልሰጠም፡፡
7. የሱማሊያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐሊ ካይር የጥቅምቱን ፓርላሜንታዊ ምርጫ ማራዘም የፖለቲካ፣ ጸጥታ እና ሕገ መንግሥት ቀውስ እንደሚያስከትል እንዳስጠነቀቁ ሆርን ዲፕሎማት በድረገጹ ዘግቧል፡፡ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ፎርማጆ ጠቅላይ ሚንስትሩ የሚመሩትን ካቢኔ ውሳኔ እንደሰሙ በውሳኔው እንደሚስማሙ ተናግረዋል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.