ኢትዮጵያኖች በህዳሴው ሳቢያ ግብጽ ውስጥ ይጠቃሉ – ታምሩ ገዳ

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው በሚገኘው በህዳሴው ግድብ ሳቢያ በከፍተኛ ጸረ ኢትዮጵያ ዘመቻ ላይ የምትገኘው ግብጽ በግዛቷ ውስጥ የሚገኙ ተገን ጠያቂ ኢትዮጵያኖች ለተለያዩ ጥቃቶች መጋለጣቸውን አምርረው ገለጹ።
ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው ብቻ ሰሞኑን በግብጽ ህገወጦች ጥቃት ከደረሰባቸው መካከል አንዱ የሆነው እድሜው በሰላሳዎቹ አጋማሽ የሚገኘው ኢትዮጵያዊው እብዲል መጂድ አል ካራኪ ታናሽ ወንድሙ ሰሞኑን ካይሮ ከተማ ውስጥ ተንቀሳቃሽ ስልኩን ፣ከሱቅ የሸመተው እቃው እንደተዘረፈበት ፣ እንደ ተደበደበ እና በውሻ የማስበላት ጥቃት እንደገጠመው ለአል ሞኒተር ጋዜጣ ገልጿል።
እንደ አብዲል መጂድ ወንድም ገለጻ ስርአት አልበኞቹ እና ጋጠወጦቹ የግብጽ ወጣቶች ሲደበድቡት “ኢትዮጵያ የአባይ ውሃን ብቻዋን እንድትጠቀም አንፈቅድላትም “የሚል ማስፈራሪያ ያሰሙ እንደነበር ታዝቧል።
በግብፅ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ተጠሪ የሆኑት ጣሂር ኦማር በኢትዮጵያኖች ላይ የተለያዩ ጥቃቶች እየደረሱ መሆናቸውን መረዳታቸውን የገለጹ ሲሆን” በተገን ጠያቂዎቹ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰው ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፣ግብጶች የሚያስቡት እዚህ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ በሙሉ ከህዳሴው ግድብ ግንባታ ጋር ንክኪነት እንዳላቸው አድርገው ነው ።”በማለት የሁኔታው አስከፊነትን ገልጸዋል ።
ታናሽ ወንድሙ በግብጻዊያን ወረበላዎች የተደበደበበት፣ንብረቱ የተነጠቀበት፣በውሻም የተበላበት ኢትዮጵያዊው እንዲል መጂድ በአሁኑ ወቅት በመንገድ ላይ ጥቃት እንዳይደርስበት በመስጋት እውነተኛ ዜግነቱን ከመግለጽ “ሶማሊያዊ ነኝ፣ሱዳናዊ ነኝ” ለማለት መገደዱን አክሎ ተናገሯል።
በግብጽ ውስጥ ከአስራ ስድስት ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያኖች ይገኛሉ ተብሎ የሚታመን ሲሆን በደል ሲደርስባቸው በአገሪቱ የጸጥታ ኃይሎች በቅጡ ጥበቃ እንደማይደረግላቸው ቸል እንደሚባሉ የተለያዩ ዘገባዎች ይገልጻሉ።ፕ/ት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ቀደም ባለ ጊዜ በአገራቸው የሚገኙ ስደተኞች በማንነታቸው ጉዳት እንደማይደርስባቸው ቃል መግባታቸው እና አጥብቀው መናገራቸው ይታወሳል።
(ታምሩ ገዳ/ህብር ራዲዮ)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.