ኮሎኔል ደመቀ ያችን ሰዓት

ሀምሌ 5 ቀን 2008 ዓ/ም
እስከዚያች ታሪካዊ ቀን ድረስ በተለያየ አቅጣጫ ወደ ጎንደር በሚስጥር የገቡት የትግራይ አፋኝ ቡድኖች፤ በከተማው በሚገኙ ሰላዮቻቸው ጥናት ሲያደርጉ ሰንብተው ተፈላጊ የወልቃይት ኮሚቴዎችን በእያሉበት ከበቡ፥ በውድቅት ሌሊት እጅ ስጡ በማለት ዋናዋናዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል ጀመሩ።
በዚያች ቀን ጎንደር ድንገት የታፈኑት የወልቃይት የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባላት፥ አቶ አታላይ ዛፌ አቶ ጌታቸው አደመ አቶ መብራቱ ጌታሁን እና አቶ አለነ ሻማ ነበሩ፥ ቀስ በቀስ አብዛኛዎቹ በተገኙበት ተይዘዋል፤
አንድ ጀግና ግን ቀርቷል፤ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ፤ ኮሎኔሉ ሃያል የጦር ሰው ነው፥ እነሱም ያውቁታል። እሳት የላሰ ነፍጠኛ ተዘጋጅቶ እንደሚጠብቃቸው ያውቃሉና፥ የእሱ ጉዳይ እጅግ አስጨንቋቸዋል፥ በሰላም እጁን እንዲሰጥ ለማግባባት አቶ መብራቱ ጌታሁን ወሳኝ የስልክ ጥሪ እንዲያደርግለት አዘዙት።
አቶ መብራቱ ደውሎ እኔ ተይዣለሁ አንተ የምታደርገውን አድርግ ብሎት በጀግና ቋንቋ መልስ ሳይጠብቅ ስልኩን ዘጋበት፥ ብቻ ተግባብተዋል።
አፋኞቹም የወልቃይቴውን ማንነት ስለሚያውቁ የታዘዘውን ለማድረግ እንዳልፈቀደ ገባቸው፥ ስህተት ሰራን መጠንቀቂያ ጊዜ ሰጠነው እንደሚሉ እርግጠኛ ነኝ፥ ለማንኛውም በያዙት መሳሪያና ቀናት በጨረሰው ዝግጅታቸው ተማምነው፥ አቶ መብራቱን ከሌሎቹ ጓዶቹ ጋር አስረው ወደ ኮሎኔል ቀጠሉ።
በኮሎኔል ደመቀ በር ተኮልኩሎ ምልክት ይጠብቅ የነበረው አፋኝ ኮማንድ ጠጋ ብሎ በሩን በማንኳካት ለኮሎኔል ትፈለጋለህ እጅ ስጥ የሚል ትዕዛዝ ሰጠ፤ ቆፍጣናው ወታደር ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ግን በጣም በተረጋጋ ወታደራዊ ስነምግባር እጅ መስጠት አይሞከርም!
ጥያቄ ካላችሁ ሲነጋ አነጋግሩኝ የሚል ቁርጥ ያለ መልስ ነበረና ሁኔታዎች ከመቅጽበት ተለወጡ።
ሰሞኑን ጸጉረ ልውጥ ኃይሎች ገብተዋል ተብሎ በጭምጭምታ የሰማው ወሬ እውነት መሆኑ ገባው ጀግናው ፥ ጠበንጃውን አነሳ፥ ትጥቁ የተሟላ ወታደር ነው፥ ለዛውም የወልቃይት ጠገዴ ነፍጠኛ፥ ከመይሳው አገር፣ ከአጼዎች ከተማ ጎንደር፥ እዚህ ላይ ተኩስ ቢነሳ ምን ይሆናሉ በሚል የቤተሰቦቹ ነገር ልቡን እያስጨነቀው ብዙ ነገር በጭንቅላቱ ይርመሰመሳል፥
የተኛችውን ህጻን ልጁንና እንደ አራስ ነብር ተሶርፋ የቤቱን ዙሪያ በዓይኖቿ እየቃኘች የባሏን እንቅስቃሴ የምትመለከተውን ሚስቱን አይዞሽ በሚል እይታ በዓይኖቹ ያነጋግራታል፥ የጀግና ሚስት የባሏን ልብ ታውቃለች፣ ቀሚሷን እጥር መቀነቷን ጠበቅ አድርጋ ታጥቃ መዳንም መሞትም ከፈጣሪ ነው፥ ቢሆንስ ሞት እርስት ነው! እንደምትል እርግጠኛ ነኝ።
ሰውየው ጨክኗል፥ ለአንዳንድ የቁርጥ ቀን ወዳጆቹ የስልክ መልክት አስተላልፎ፣ ልጆቹንና ሚስቱን ስሞ፥ የጠበንጃውን ቃታ ወድሮ በመትረየስ ፊት ተጣደ።
ጥቂት ሳይቆይ በቤቱ በር ላይ በከባድ መሳሪያ ኃይለኛ ተኩስ ተከፈተበት፤ ኮሎኔል መሬት ይዟል፣ ትንፋሹን ዋጥ አድርጎ መሬት ላይ ተጎዘጎዘ፥ እነደ ቀትር እባብ እየተቋጠረ እየተፈታ ይተኩሳል፥ ጀግናው የሚቀመስ አይደለም፥ ጊቢ ጥሶ የገባውን አፋኝ ኃይል አንድ ባንድ በጥይት ያኮማትረዋል። ከውጭ ያለውንም የመትረየስ ጥይት በመጣበት እያሾለከ ግንባር ግንባሩን ይፈለጠዋል፥ በላይ እሳት በታች እሳት ነደደ፥ የኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ቤት የጦር ሜዳ ሆነች።
የአልሞት ባይ ተጋድሎውን በእልህ ተያይዞታል፥ ኮሎኔሉ ከባድ ተዋጊ ነው፥ በዚያ ቤት ውስጥ ብዙ ጦር ያለ ይመስላል ጀግናው ቤቱ ተደፍሮበት እጅግ ተቆጥቷል፤ እንደ አንበሳ እንደ ነብር አድርጎታል። የጥይት ባሩድ አስክሮታል፥ በዚህ ሁሉ የተኩስ ማእበል ሚስቱ ከጎኑ አልተለየችም፥ ከመሬት ፈግፍጋ ተኝታ የጎደለውን ታቀብላለች እሷም ጦረኛ ናት።
መሬት ቀለጠ፤ ቀበሌ 18 በጥይት ተኩስ አቧራው ጨሰ፤ የተኩስ ሩምታ የቀሰቀሰው የጎንደር ህዝብ ግራ ተጋብቶ በእየስርቻው መሽጓል፤ ትጥቅ ያለው ቀስ ብሎ እየተንኳተ ወደ ጥይቱ ድምጥ ይጠጋል፥ አሁን ሊነጋ ቀርቧል፥ ጎህ እየቀደደ ነው።
የኮሎኔል ጓደኞች መታፈኑ የገባቸው እነ አቶ ሲሳይ ታከለ አፋኙን ጦር ከኋላ ቀርበው መተግተግ ጀምረዋል፥ እነ ሰጠኝ ባብል ከጥቂት ጓዶቹ ጋር ገስግሰው ደርሰዋል፥ ፊት ለፊት ገጥመው እያጣደፉት ነው፥ አጥር ዘለው እጅ ሊይዙ የገቡት እዛው ቀርተዋል፥ በሰውየው ፊት መቆም አልቻሉም። ከመቀሌ የመጣው የወያኔ ጦር ሱሪው ላልቷል።
እነ ጎቤ መልኬ ከአርማጭሆ የተነቃነቀውን የገበሬ ጦር እየመሩ የተዘጋውን ኬላ በጥይት በርግደው ወደ ጎንደር ገቡ፥ ቡሉኮ ደርሰዋል። እነ ደጀኔ ማሩ ከኋላ የወልቃይት ጠገዴን ወጣት እየመሩ እየመጡ ነው
በአርማጭሆ በር፣ በመተማ በር፣ በበለሳ መግቢያ ጎንደር በገበሬ ጦር ተከበበች፤ ምድር ቀውጢ ሆኗል፥ የአርማጭሆ ጀግና ገነት ተራራ ዙሪያውን ተጠምጥሞ ያቅራራል፤ በለሳ በላይ፣ ወገራ በታች፣ አረ ማነው ወንዱ ይላል፤
ጎቤ የጦር መሪ ሆኗል፥ ሰልፉ አምሯል፥ ወጣቱ ትዕዛዝ ይጠባበቃል።ኮሎኔሉ ስራውን ሰርቶ ጨርሶ ማነው ሚደፍረኝ እያለ በቤቱ ጊቢ ይንጎራደዳል፤ ግዳይ በግዳይ ሆኗል፤ ሚሞት ሞቶ የቀረው ነብሴን አውጭኝ ሽሽት አድርጓል፣ የወያኔ ጦር ከሬሳ በቀር በስፍራው የለም፤ ተኩሱ በረድ ብሏል።
ጎንደር የከተማው ፖሊስ ከሽማግሌዎች ጋር ተባብሮ ለማረጋጋት እየሞከረ ነው፥ ከንቲባ ተቀባና የጸጥታ ሃላፊዎች ኮሎኔል ደመቀን እየሸመገሉ ላይ ታች ይላሉ፡፡
ወያኔዎች ለያይተነዋል ያሉት የጎንደር ህዝብ ቅማንት አማራ ሳይል፥ የመጣውን የገበሬ ጦር እጁን እየሳመ ከእናንተ በፊት ያርገን ይላል፤ ሴቱ እልልታውን ያቀልጠዋል፤ ወንዱ በሽለላ “ማን ና ብሎታል ከጀግና አገር፤ ጃርት የበላው ዱባ መስሎ ሊቀር” እያለ ይንደቀደቃል፥ ምናለፋችሁ ጎንደር የታየው ትዕይንት እጹብ ድንቅ ነበር፡፡
እንዳያልፍ የለም ያ ፈታኝ ቀን ተገባደደ፥ ኮሎኔል በገላጋይ ከጉድቡ ተነሳ፥ ወንጀል አልሰራሁም አልሸሽም፥ ሰላማዊ ታጋይ ነኝ አልሸፍትም ብሎ የአደራ እስረኛ ሆነ። የወደቀ ሰው ሲቆጠር ከጠላት ወደ 19 ሬሳ ተለቀመ፤ ከእኛ ወገን አቶ ሲሳይ ታከለ እና ጀግናው ሰጠኝ ባብል መሰዋታቸው ተሰማ፥ ከባድ ሃዘን ሆነ፥ በመላው ጎንደር ታላቅ ቁጣ ተቀሰቀሰ።
ፉከራው፣ ቀረርቶው፣ ሽለላውና ጥይቱ እንደ ጉድ ሲወርድ ውሎ፥ ከቆላው ከደጋው ጀግና በእያይነቱ ተሰብስቦ በጀግንነት የወደቁትን በክብር ሸኛቸው። ቅማንትና አማራ በአንድ ምሽግ ከጠላቱ ጋር ተናንቆ አብሮ እንደሚዋደቅ አስመሰከረ፥ በዚች ቀን የአማራ ተጋድሎ ጎንደር ላይ ፈነዳ፥ የአርማጭሆ፣ የበለሳ፣ የወገራና የደንቢያ ጀግና ወደ ቤቱ ላይመለስ ተማማለ፥
በህወሃት የተወሰደውን ሕገወጥ እርምጃ በማውገዝ መሬት አንቀጥቅጥ ሰላማዊ ሰልፍ ጎንደር ላይ ተደረገ፥ ወጣት ንግስት ይርጋ አማራ ሕዝብ አሸባሪ አይደለም በማለት በአደባባይ አወጀች። ንግስቷ እንደ ጸሓይ ደምቃ እንደ ራስ ዳሸን ተራራ ገዝፋ ዋለች፥ የአማራ ሕዝብ ያሰማው የተቀናጀ ድምጽና ጠንከር ያለ ቁጣ በመንግስት ላይ ሽብር ለቀቀበት። የኦሮሞ ደም የእኛ ደም ነው የሚለው ዘመን ተሻጋሪ መፈክር በዓለም ሁሉ አስተጋባ፥ ኢትዮጵያዊ የተባለ ሁሉ በደስታ ፈነደቀ።
ጎንደር የነገስታት አገር፥ ታላቁ ህዝብ ተነስቷልና የወያኔ ግብዓተመሬት እንደቀረበ በመላው ኢትዮጵያ ተነገረ፥ ጀግናው አማራ ከደብረታቦር፥ ባህርዳር፣ ከፍኖተ ሰላም ደብረ ማርቆስ በአንድ ድምጽ ተነቃነቀ፥ የአማራ ወጣት አመርሮ ለለውጥ ተነሳ፥ ፍርሃት ጠፋ፥ በጥይት ፊት መራመድ ጀመረ፥ ሰልፈኞች በጅምላ ተረሸኑ። እነ ንግስት ይርጋን ጨምሮ ሴቱ ወንዱ ሸፈተ፥ አማራ ወጣት ሁሉ ማደኛ ወጣበት፥ ቄስ መነኩሴ ሳይቀር ብዙዎች ታሰሩ።
ሰሜን ጎንደር አርማጭሆ ወልቃይት ጠገዴ ቋራ፥ ከእብናት በለሳ እስከ ዳባት እንቃሽ ጃናሞራ ድረስ ወያኔን ሊገጥም የአማራ ጦር በጎበዝ አለቃ ተሰማራ፥ እነ ጎቤ መልኬ፣ እነ ደጀኔ ማሩ፣ መሳፍንትና አረጋ ወጣቱን ይዘው በወራሪው ወያኔ ላይ ጦርነት ከፈቱ፥ ቀድመው ዱር ቤቴ ያሉ አርበኞች እነ አበራ ጎባው ወያኔን በጫካው አዝለከለኩት፥ ብዙም ሳይቆይ የአስቼካይ ጊዜ አዋጅ ታወጄ፥ በኮማንድ ፖስት ወታደራዊ አገዛዝ ተጀመረ፥ ይህ የለውጡ ዋዜማ ነበረ፥
ምንጭ
ኢትዮጵያ ዛሬ ብሎግ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.