ለቸኮለ! የዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 7/2012 የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1. የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ውሃ መያዝ መጀመሩን ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች፡፡ ውሃ ሙሌቱ ግድቡ በዘንድሮው ክረምት መያዝ ያለበትን 4.9 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪውብ እንዲይዝ ዐላማ ያደረገ ነው፡፡ ትናንት በሰኮንድ 4 ሺህ 400 ሜትሪክ ኪውቢክ ውሃ እንደገባ ታውቋል፡፡ ግድቡ በቀጣዩ ዐመት በ2 ተርባይኖች ሃይል እንዲያመነጭ ታቅዷል፡፡ የግድቡ ሙሌት ስለመጀመሩ መንግሥት በይፋ ማረጋገጫ አልሰጠም፡፡ Link- https://bit.ly/32rN6mv
2. በሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውሃ ሙሌት ላይ ሲደረግ የሰነበተው ድርድር ትናንት ምሽት ያለ ስምምነት እንደተጠናቀቀ የውሃ እና ኢነርጂ ሚንስቴር ዛሬ በፌስቡክ ገጹ ባሰራጨው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ሦስቱ ሀገራት እስካሁን የደረሱበትን ደረጃ ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዛሬ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ የኅብረቱ ሊቀመንበር፣ የኅብረቱ ሥራ አሥፈጻሚ ቢሮ አባል ሀገራት እና የሦስቱ ሀገራት መሪዎች ሪፖርቱን ገምግመው በሚሰጡት አቅጣጫ መሰረት፣ ድርድሩ እንደገና እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡
3. ኢትዮጵያ ከሕዳሴ ግድብ በላይ ባለው ተፋሰስ ላይ የሚኖራት የወደፊት ውሃ አጠቃቀም መርሆዎች በድርድሩ ዋናው የልዩነት ነጥብ እንደሆነ የውሃ እና መስኖ ሚንስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ አውስቷል፡፡ የግብጽ እና ሱዳን ማለቂያ የሌለው ፍላጎት ስምምነት እንዳይደረስ እንቅፋት እንደሆነም መግለጫው ጠቁሟል፡፡ በተያያዘ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ሌላ ግንባታ እንዳታካሂድ ከግብጽ የቀረበውን ሃሳብ፣ ኢትዮጵያ ውድቅ እንዳደረገችው ዋዜማ ሰምታለች፡፡
4. የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ገዱ አንዳርጋቸው የሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ተጀምሯል በሚል የተሰራጩ ዘገባዎችን እንዳስተባበሉ የግብጹ አሕራም ዘግቧል፡፡ እንዲህ ያለ የተሳሳተ ዘገባ ያሰራጩ መገናኛ ብዙኻንን መንግሥት በሕግ እንደሚጠይቅም ተናግረዋል- ብሏል ዘገባው፡፡ ገዱ ይህን ተናገሩ የተባለው አል-አይን ለተሰኘ የዐረብ ድረገጽ ነው፡፡ ከሳተላይት ምስሎች በግድቡ ላይ የሚታየው ውሃ፣ ከወንዙ የገባ ወይስ ከዝናብ የተገኘ ስለመሆኑ ርግጠኛ እንዳልሆኑ የግብጽ ጋዜጦች ሲዘግቡ ውለዋል፡፡
5. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባደረገው ስብሰባ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አዋጅን እንዳሻሻለ ኢቢሲ ዘግቧል፡፡ በማሻሻያው የኮሚሽኑ አመራሮች አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ተጨማሪ ሥራ መስራት ይችላሉ የሚለው የአዋጁ አንቀጽ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ ማሻሻያው ያስፈለገው የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ሥራ ሙሉ ጊዜ ስለሚፈልግ እንደሆነ ተወስቷል፡፡
6. በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በተከሰተው ሁከት ንብረታቸው ለወደመባቸው ወገኖች መንግሥት ካሳ ሊከፍል እንደሚገባ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ጠይቋል፡፡ ኢዜማ ዛሬ በፌስቡክ ገጹ ባሰራጨው መግለጫ፣ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ ሃላፊነቱን ባለመወጣቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች እና ሕዝቡን ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል ብሏል፡፡
7. የሱማሊያው ጠቅላይ ሚንስትር ሐሰን ኬይር ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ቅራኔ ውስጥ ከገቡት 5 የፌደራሉ ክልሎች ፕሬዝዳንቶች ጋር ፊት ለፊት ሊነጋገሩ እንደሆነ የሀገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከ5ቱ የክልል ፕሬዝዳንቶች ጋር የሚመክሩት፣ ክልሎቹ ለጥቅምቱ የሀገር ዐቀፉ ፓርላማ ምርጫ የአንድ ሰው አንድ ድምጽ ምርጫ ሥርዓትን እንደማይቀበሉ ትናንት በጋራ ማሳወቃቸውን ተከትሎ ነው፡፡ ውይይቱ ለሀገሪቱ ምን ዐይነት አዲስ የምርጫ ሥርዓት ይዘርጋ? በሚለው ላይ ነው፡፡
8. ኬንያ ባንድ ቀን ብቻ 497 በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎችን እንዳገኘች የሀገሪቱን ጤና ሚንስቴር ጠቅሶ የሀገሪቱ ሲትዝን ቲቪ ዘግቧል፡፡ 5 ታማሚዎች ደሞ በቫይረሱ አማጭ በሽታ ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ዛሬ የተመዘገበው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እስከ ዛሬ ከታየው ሁሉ ከፍተኛው ነው፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.