ለቸኮለ! የዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 9/2012 የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1. የትግራይ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ለክልሉ ምርጫ ኮሚሽን ሃላፊዎችን እንደሾመ የክልሉ ዜና ምንጮች ዘግበዋል፡፡ አቶ ሙሉወርቅ ኪዳነ ማርያም የኮሚሽኑ ሰብሳቢ፣ ጽጌረዳ ዲበኩሉ ደሞ ምክትል ሰብሳቢ ሆነዋል፡፡ ዶ/ር ጸጋ ብርሃን፣ መሐመድ ሰዒድ እና መረሳ ጸሃዬ ደሞ የኮሚሽኑ አባላት ሆነው ተሹመዋል፡፡
2. የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) አመራሮች በቀለ ገርባ እና ጀዋር ሞሐመድ ዛሬ ፍርድ ቤት እንደቀረቡ የመንግስት ዜና አውታሮች ዘግበዋል፡፡ ችሎቱ ዛሬ የተሰየመው ፖሊስ በጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ነው፡፡
3. ግብጽ ስለ ሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ከኢትዮጵያ ኦፊሴላዊ ማብራሪያ እንደጠየቀች የሀገሪቱ ጋዜጦች ዘግበዋል፡፡ ግብጽ ማብራሪያውን የጠየቀችው መንግሥታዊው ቴሌቪዥን የግድቡ ውሃ ሙሌት ተጀምሯል በማለት ትናንት መዘገቡን ተከትሎ ነው፡፡ ዘግየት ብሎ ግን ግድቡ ላይ የሚታየው ውሃ ከፍተኛ ዝናብ የፈጠረው እንደሆነ ውሃ እና መስኖ ሚንስትሩ መናገራቸውን በመጥቀስ፣ ዘገባ የተሳሳተ መሆኑን ጣቢያው ገልጦ ይቅርታ ጠይቋል፡፡ ከጣቢያ ማስተባበያው ውጭ፣ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር እስካሁን በይፋ የሰጠው ማስተባበያ የለም፡፡
4. ሱዳን የጥቁር አባይ ወንዝ ፍሰት መጠን በቀን 90 ሚሊዮን ኪውቢክ ሜትር እንደቀነሰ ትናንት ማስታወቋን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ የሀገሪቱ የውሃ እና መስኖ ሚንስቴር የወንዙ ውሃ መጠን ስለመቀነሱ መግለጫ ያወጣው፣ ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን ውሃ መሙላት እንደተጀመረች መንግሥታዊው ቴሌቪዥን በዘገበ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ነው፡፡
5. በሀገር ውስጥ እና በመላው ዐለም ያሉ ኢትዮጵያዊያን ለሕዳሴ ግድብ ባንድ ላይ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ የሚያስችል መርሃ ግብር እንደተዘጋጀ የሀገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል፡፡ መርሃ ግብሩ የሚዘጋጀው ሊፍት ኢትዮጵያ በተሰኘ የግብረ ሰናይ ድርጅት እና በግድቡ ሕዝባዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ብሄራዊ ምክር ቤት ትብብር ነው፡፡ በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ለ20 ደቂቃ እንዲተላለፍ የታሰበው መርሃ ግብር፣ “ድምጻችን ለግድባችን” የተሰኘ መሪ ቃል ይኖረዋል፡፡
6. የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) አመራር አባሉ ኂሩት ክፍሌ ትናንት እንደታሰሩበት ፓርቲው በትዊተር ገጹ አስታውቋል፡፡ ኂሩት የፓርቲው ብሄራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የፓርቲው የሙያ ማኅበራት ተጠሪ ናቸው፡፡ ፖሊስ ኂሩትን ለምን እንዳሰራቸው ለፓርቲው ያሳወቀው ነገር የለም፡፡
7. የቱርኩ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዛሬ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ልዩ መልዕክተኛ እና ከቀድሞው ርዕሰ ብሄር ሙላቱ ተሾመ ጋር ተገናኝተው እንደተወያዩ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡ በውይይቱ የሁለቱ ሀገራት ባለሥልጣናት የሁለትዮሽ ጉብኝቶች፣ የጋራ ምክክሮች እና የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትስስሮች እንዲጠናከሩ ተስማምተናል ብለዋል፡፡
8. በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ተማሪዎች ባላጠናቀቋቸው ወሰነ ትምህርቶች እየተለዩ ማካካሻ ትምህርት እንደሚሰጣቸው የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር ዛሬ በፌስቡክ ገጹ ባሰራጨው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ተማሪዎች ወደ ተቋሞቻቸው ገብተው ማካካሻ የሚያገኙት በ2 ዙር የጊዜ መርሃ ግብር ይሆናል፡፡ ለማካካሻው እና ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች ወደፊት የጊዜ መርሃ ግብሩ ይገለጻል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.