ሕብረተሰቡ ፖሊስ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሊተባበር ይገባል – ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው

ሕብረተሰቡ ፖሊስ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በሚያደርገው እንቅስቃሴ ትብብር እንዲያደርግ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው ጣሰው ጠየቁ።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ ሜክሲኮ አደባባይ ገነት ሆቴል አካባቢ በሚገኘው የቀድሞው የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሥራ ጀምሯል።
የቀድሞው የማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ከተዘጋ በኋላ ካዛንቺስ በሚገኝ ህንጻ ላይ ተጠርጣሪዎችን ሲመረምር እንደነበር ታውቋል።
ኮሚሽኑ ሕንፃውን ላለፉት ሶስት ወራት እድሳት ሲያደርግ ቆይቷል።ጥራታቸውና ደህንነታቸውን የጠበቁ የተጠርጣሪዎች የቃል መቀበያና ማቆያ እንዲሁም የጠበቆችና የባለጉዳዮች መቀበያ ክፍሎችንም አዘጋጅቷል።
ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኮሚሽኑ ሕንጻውን ከተረከበ በኋላ ያከናወነው እድሳት የቀለምና የቁሳቁስ ብቻ አልነበረም።
ይልቁንስ ተጠርጣሪዎች ያለማንም አስገዳጅነት በራሳቸው ፍላጎት ከፍርሃት ነጻ ሆነው የሚመረመሩበት የአስተሳሰብ እድሳት ጭምር ነው ብለዋል።
በመሆኑም ኅብረተሰቡ ፖሊስ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የሚደርገው የወንጀል ምርመራ የዜጎችን ክብር በጠበቁ መልኩ መሆኑን በመገንዘብ እንዲተባበረው ጠይቀዋል።
የኮሚሽኑ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ በበኩላቸው የምርመራ ሥራዎች በዘመናዊ መንገድ የሚያከናውንበት እድሳት መደረጉን ገልጸዋል።
ቢሮው ሰዎች ሲያዩት የሚፈሩት ሳይሆን፤ በነጻነት ሃሳባቸውን የሚገልጹበት አደረጃጀት እንዲኖረው ተደርጓልም ብለዋል።
ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም፥ በቢሮው የተጠረጠረ ማንኛውም ግለሰብ ከቤተሰቦቹም ሆነ ከጠበቆቹ ጋር መገናኘት ይችላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኤፍ.ቢ.ሲ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.