በወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታ የተሰጠ ምክንያታዊ ድጋፍና ሂስ ! – ከንጉሤ አሊ

በወንድማችን አርቲስት ሀጫሉ ሀንዴሳ ግዲያና ያንን ተከትሎ በተፈጸመው አሰቃቂ ጭፍጨፋ ላለቁ ወገኖቻችን የተስማንን መሪር ኃዘን እየገለጽን ለቤተሰብ ፣ ለዘመድ አዝማድና ለመላው ሕዝባችን መጽናናትን ፈጣሪ አምላክ እንዲሰጥና ለሞቱትም ነፍሳቸውን በአጽደ ገነት እንዲያኖር ጽሎቴ ነው።

ዘር ተኮር እልቂት በመፈጸም ሕዝብ ለመለያዬትና ሀገር ለማፍረስ የተሰማሩ አክራሪዎችና ተባባሪዎቻቸውን ለፍርድ ለማቅረብ በመንግሥት የተጀመረውን እርምጃ እየደገፍኩኝ ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ተፎካካሪ ፖለቲከኞችን አብሮ ማሰሩ ለወንጀለኞች ሽፋን መስጠትና ጉዳዩን ለማድበስበስ የሚደረግ ሴራ ያለ ከማስመስሉም በተጨማሪ ለልዩ የፖለቲካ ግብ በንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ አይነት ጫዋታ የሚፈልጉ ባለስልጣናት የለውጡን ባቡሩ ከሃዲዱ እንዳያስወጡት መንግሥት ጥንቃቄ እንዲያደርግና ያለአግባብ የታሰሩትን እንዲለቅ እጠይቃለሁ ።

የዘገዬ ፍትህ እንደለለ ስለሚቆጠር መንግሥት ካሁን በፊት የተፈጸሙ ወንጀሎችን ጭምር አጣርቶ ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡና የፍትህ አካሉም አፋጣኝ ወሳኔ እንዲሰጥ ለማሳሰብ እወዳለሁ ።

በህገወጥ መንገድ በህቡዕ ተደራጅተው ኮሽ ባለ ቁጥር በየቦታው የሰው ህይወት የሚቀጥፉ ፤ ንብረት የሚያወድሙና ሽብር የሚፈጥሩ አካላት ድርጊቱን ከፈጽሙ በኋላ መንግሥት እንደ እሳት አደጋ ለማጥፋት ከመሯሯጥ ይልቅ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስባለሁ ።

ማንም ግለሰብ ተፈጥሯዊና ህገመንግሥታዊ መብቱን ለማስጠበቅ በሲቪክ ወይንም በፖለቲካ የመደራጀት መብቱ የተጠበቀ ነው ነገር ግን የሚደራጀው በፓርቲ ለስልጣን ፤ በሲቪክ ማህበራት የተለያዩ መብቶችን ለማስከበር መሆኑን የሚያረጋግጥ ፕሮግራምና ደንብ አቅርበው በህገመንግሥቱ ድንጋጌ መሰረት ህጋዊ ፈቃድ ይዞ እንጂ ማንም ግለሰብ ከምድር ተነስቶ ተከበብኩ ድረሱልኝ ባለ ቁጥር በመንጋ ተነስቶ እንደ አንበጣ የሚወር መሆን የለበትም ። ስለሆነም በህገወጥ የተደራጁ ማንኛቸውም ስብስቦችን ማገድና ህጋዊ እውቅናን አግኝተው እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር ነው ።

በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ አክራሪ ግለሰቦችና ቡድኖች ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር ሳይቀር ግንባር ፈጥረው በመንግሥት ላይ ጫና በመፍጠር ወንጀለኞችን ለማሰመለጥ የሚያካህዱትን ዘመቻ አጥብቄ እቃወማለሁ እኩይ ተግባራቸውንም ለዓለም ሕብረተሰብ በማጋለጥ የድርሻዬን እወጣለሁ ።

ካሁን በፊት የተፈጸሙ አሰቃቂ ወንጀሎችም ሆኑ አሁን እየተፈጸሙ ያሉ ዘር ተኮር ሽብሮች በግለሰብ ላይ ያነጣጠሩ ሳይሆኑ በሀገርና በሕዝብ ደህንነት ላይ ስለሆነ ችግሩ የሚፈታው በህግና በህግ ብቻ እንጂ ከወንጀለኞች ጋር በመደራደርና በዕርቅ ባለመሆኑ ይህንን የማወናበጃ አጀንዳ አማራጭ ያቀረቡ መስለው ሕዝቡንና የአገር ሽማጊሌዎችን ለማሳስት የሚሞክሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች በንጹኃን ደም መቀለዳቸውን እንዲያቆሙ እጠይቃለሁ ።

የዘር ጥቃት ሲፈጸምና ሀብት ንብረታቸው ሲወድም በግብርና ታክስ ከፋዩ ገንዘብ የሚተዳደሩ የመንግሥት ባለሥላጣናት ፣ የፖሊስና የጸጥታ አካላት ድርጊቱ ከመፈጸሙ በፊት መከላከል ባይችሉ እንኳ ወዲያውኑ ለሕዝቡ ቢደርሱ የጉዳቱ መጠን በቀለለ ነበር በተቃራኒው ግን ቆመው ከማየት በዘለለ ተባባሪ የነበሩ እንዳሉ ከተጠቂዎች አፍ ሰምተናል ይህ በተለይ ኤየሚመለከተው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትን በመሆኑ ከሀዘን መግለጫ በዘለለ ቢያንስ ህግና ስርአት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን አለመወጣቱን አምኖ ይቅርታ ለመጠየቅ አለመድፈሩ ጥርጣሬአችንን የሚያጎላው ሆኖ አግኝቻለሁ ። ይህንን አስመልክቶ የፌደራል መንግሥት የጀመረውን ህጋዊ እርምጃ እደግፋለሁ ።

ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት ሆንብለው ሲቀሰቅሱ የነበሩ የዜና አውታሮችና ከሙያዊ ስነምግባር ውጭ ጸረ ሕዝብ የሆነ ፕሮፓጋንዳ ሲያስተጋቡ የነበሩ የሚዲያ ሰራተኞች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው ።

የጥቃቱ ሰለባ በመሆን ከቄያቼው የተፈናቀሉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ንጹኃን ዜጎቻችን ዋስትና ተሰጥቷቸው ወደ ቦታቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እንዲያደርግና ለወደመው ንብረት ካሳ እንዲከፍል እጠይቃለሁ ።

መንግሥት የህዳሴ ግድቡን ስራ አስመልክቶ በወቅቱ የተከሰቱትን ችገሮች አርሞና አስተካክሎ በእቅዱ መሰረት የውስጥና የውጪ ተጽእኖ ሳይበግረው የኢትዮጵያ ታላቁ ኅዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ የውሃ ሙሊት ማከናወኑን እያደነኩኝ ከተፋሰስ አገሮች ጋር የሚካሄደውንም ድርድር የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ እንዲጠናቀቅ እየተደረገ ያለውን ጥረት በቅርበት እየተከታተልኩ የሚፈለግብኝን የዜግነት ጊዴታየንም እንደምወጣ ለማረጋገጥ እወዳለሁ ።

መንግሥት የጀመረው ሀግ የማስከበርና ወንጀለኞችን ለፍርድ የማቅረቡ ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ዘላቂና ብቸኛው አማራጭ አለመሆኑን ተገንዝቦ በተጓዳኝ ለፖለቲካዊ መፍትሄ ሳይውል ሳያድር ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲጀምር መጠቆም እወዳለሁ ።

በባህር ማዶ ሃገራት የሚኖሩ አክራሪ የኦሮሞ ፖለቲከኞችና ግብረአበሮቻቸው ‹‹ኢትዮጵያ ትውደምና ሌሎች እዚህ ለመጥቀስ የሚያስጽይፉ ቃላትን›› ያለ ይሉኝታና ሀፍረት በአደባባይ እየተጠቀሙ የኦሮሞ ህዝብን ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ለመነጠል የሚያደርጉትን የፖለቲካ ሴራና የኦሮሞን ሕዝብ የማይመጥን እጅግ ኋላቀር ተግባር ሀቀኛ የኦሮሞ ልጆች ማጋለጥና መመከት ይኖርባቸዋል፡፡

የአርቲስት ሀጫሉ ሀንዴሳን ግዲያ ተከትሎ አቶ እስክንድር ነጋንና ባልደረቦቹን ፣ ወይዘሮ አስቴር ስዩምን፣ ወይዘሮ ሒሩት ክፍሌን ፣ ኢንጅነር ይልቃል ጌትነትንና፣ አቶ ልደቱ አያሌውን ከጅዋር መሃመድና በቀለ ገርባ የጀኖሳይድ አቀናባሪዎች ጋር ቀላቅሎ በተመሳሳይ ወንጀል ጠረጠርኩ ብሎ ማሰር የሴራ ፖለቲካ መገለጫ ከመሆኑም በላይ የመንግሥትን ተአማንነትና የሕዝብ ተቀባይነትን የሚሸረሽር በመሆኑ ያላግባብ የታሰሩ የህሊና እስረኞች ያለ ቅድመ ሁኔታ ሊለቀቁ ይገባል ፡፡

በእኔ እምነት የባልደራስ ፓርቲ ሕዝቡ ራሱንና ንብረቱን እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማትን ከጥፋትና ከውድመት እንዲጠብቅ ማሳሰቡ አዲስ አበባ ዳግማዊ ሻሽመኔ እንዳትሆን ስላደረጋት እንዲያውም በዶክተር ዓቢይ አስተዳደር ሊመሰገን ሲገባው ሊበሏት ያሰቧትን ወፍ ጅግራ ነች አሏት እንዲሉ ከጽንፈኞች ጋር ተናበዋል ብሎ በቁጥጥር ስር ማዋሉ ማንንም ሊያሳምን አይችልም ። እንዲህ አይነቱን የሀሰት ውንጀላ የሚፈበሪኩ የትህነግ ግርፍ ካድሬዎች ከመንግሥት የኃላፊነት መዋቅር ገና ያልተወገዱ በመሆናቸው ለውጡን አደጋ ላይ እንዳይጥሉ ዶክተር አብይ ዐይናቸውን ከኳሷ ላይ ባያነሱ ይመረጣል ።

በማጠቃለያ ህወኃት የመገንጠል ዓላማውን እውን አድርጎ በሰላም መኖር የሚችለው ኢትዮጵያን ሲበታትናት ብቻ በመሆኑ ይህንኑ እውን ለማድረግ ያለፍላጎቱ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የጫነውን በታኝ ህገመንግሥት በሕዝብ ተሳትፎና ፍላጎት በተዘጋጀ ህገመንግሥት እስካልተቀየረ ድረስ ጎራ ለይቶ መተላለቁን ማስቆምና ዘርፈ ብዙ ችግሮቻችንን አስወግደን በጋራ ማደግና መበልጸግ ከምኞት የዘለለ ሊሆን ስለማይችል ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ።

ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷና የሕዝቧ አንድነት ተጠብቆ ለዘላለም ትኑር

ከንጉሤ አሊ

1 COMMENT

  1. የአማራ ክልል ህወሓትን በፀብ አጫሪነት ከሰሰ:: 27.07.2020
    ባህርዳር በተጀመረው የክልሉ 5ተኛ ዓመት 15ተኛ መደበኛ ጉባኤ
    የአማራ ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ፣ አቶ ተመስገን ጥሩነህ የክልሉ ህዝብ ራስን ለመከላከል የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንዲደግፍም አሳስበዋል፡፡ በህገወጥ መንገድ ተደራጅተው የክልሉን ሰላም ሲያናጉ ነበሩ የተባሉ ከ1300 በላይ ሰዎች ደግሞ በሰላማዊ መንገድና በኃይል ወደ መንግስት መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡
    የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የትግራይ ክልልን የሚያስተዳድረውን ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)ን «በጠብ ጫሪነት» ከሰሱ። የርዕሰ መስተዳድሩ ክስ የተሰማው ዛሬ በጀመረዉ የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር፣ 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 15ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ነዉ። ርዕሰ መስተዳድሩ ህወሓት «የሀሰት መረጃ እየለቀቀ ለዘመናት በአብሮነት የኖረውን የቅማንት እና የአማራ ሕዝብ ወደ ግጭት እንዲያመራ እየሰራ ነው» ሲሉም ወንጅለዋል። የትግራይ ክልል የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ሊያ ካሳ ግን የርዕሰ መስተዳድሩን ክስ አጣጥለዋል። በህገወጥ መንገድ ተደራጅተው የክልሉን ሰላም ሲያናጉ ነበሩ የተባሉ ከ1300 በላይ ሰዎች ደግሞ በሰላማዊ መንገድና በኃይል ወደ መንግስት መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡ ይሁንና በአዋሳኝ ክልሎች የአመራር ለአመራር ለሕዝብ ዉይይት ማካሄድ ስለመቻሉ ተመሥገን ጥሩነኽ ተናግረዋል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን ወደ ቀያቸው መመለስ እንደተቻለም አቶ ተመሥገን አሳውቀዋል።

    የአማራ ክልል ህወሓትን በፀብ አጫሪነት ከሰሰ::

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.