‘’አማራ ያለ ኦሮሞ፤ ኦሮሞ ያለ አማራ ሙሉ አይሆንም’’– ረዳት ፕሮፌሰር አበባው

‘’አማራ ያለ ኦሮሞ፤ ኦሮሞ ያለ አማራ ሙሉ አይሆንም’’ ይላሉ የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው። የታሪክ ተመራማሪውና የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በኢትዮጵያ ሕዝቦች ውስጥ ያለው መልካም እሴት አንዱ ጋብቻ ነው ይላሉ።

ጋብቻ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በዘር፣ በብሔር ማንነት ሳይሆን፤ በመደብ ወይም በኢኮኖሚና በሙያ ላይ እንደሚመሰረትም ይገልጻሉ። በተለይም በመሳፍንቱ በኩል ከአካባቢ አራርቆ የመዳር ባህል በኢትዮጵያ ታሪክ ዘንድ ”ትልቅ” ሥፍራ ያለው ባህል እንደሆነ ጠቅሰው፤ የሰሜኑ ለደቡቡ፣ የደቡቡም ለሰሜኑ በጋብቻ የተሳሰረበት ኢትዮጵያዊነት የተገመደበት ታሪክ ያደርጉታል።

በዚህም በኢትዮጵያ ታሪክ ትግሬው ለበጌምድሬው፣ ሸዋው ለወለጋ፣ ጎጃም ለሸዋ፣ ወለጋ ለሐድያ እየተጋባ ትስስሩ የተቆራኘበት እንደሆነ ገልጸው፤ በኢትዮጵያ ማህበረሰብ ውስጥ የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ ስብጥር ደግሞ ትልቁን ሥፍራ መያዙን ያነሳሉ። የኦሮሞ ሕዝብ እንቅስቃሴ ከጀመረበት ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ለ400 ዓመታት ሁለቱ ሕዝቦች ሁለንተናዊ ውህደት ያለበት መልከ ብዙ ትስስር የተፈጠረበት እንደሆነም ይገልጻሉ።

በአፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግስት የኦሮሞ ሕዝብ ሲንቀሳቀስ በየስፍራው ያገኘውን ሕዝብ በሞጋሳና ጉዲፈቻ ባህሉ ማንነቱን እያወረሰ መምጣቱን ያብራራሉ። በዚህም አማራው፣ ጋፋቱና ወርጂ የሚባሉ ሕዝቦች የአሮሞ ሕዝብ ማንነት መውረሳቸውን፤ በአንጻሩ መሪና ተመሪ እኩል የነበረበት ኦሮሞ በኢኮኖሚ የባላባት መደብ ሥርዓት መልመዱን ይጠቅሳሉ።

በሌላ በኩል በ19ኛው ክፍለ ዘመን በነበረው የሸዋ ነገሥታት የግዛት ማስፋፋት የማስገበር ሂደት በተመሳሳይ ህዝባዊ ስብጥር መፍጠሩን ይናገራሉ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው። በየዘመናቱ ሂደት በተደረጉ ጦርነቶች የመሳፍንት ገዥዎች ካልሆነ በቀር የሕዝቦች ጉዳይ እንዳልሆነ ያነሳሉ።

በየትኛውም ዓለም ጦርነት ተጎጂና ተጠቃሚ ወገን ሊኖር እንደሚችል ቢታመንም፤ በግዛት ማስፋፋት አንድን ሕዝብ ለመጨቆን አማራው በኦሮሞ፣ ኦሮሞው በአማራ ላይ ያደረገው ጦርነት እንደሌለ ይናገራሉ። በአጠቃላይ ላለፉት 400 ዓመታት በነበረው የሁለቱ ሕዝብ ግንኙነት ሶስት ሊነጠሉ የማይችሉ በሶስት የሚተነተኑ ግንኙነቶች መፈጠራቸውን ያነሳሉ ምሁሩ። የመጀመሪያው ደማዊ ትስስር ሲሆን፤ ዛሬ ላይ የብሄር ትኩሳት የሚነሳባቸው አካባቢዎች ሳይቀር ወደኋላ ትውልድ ቢቆጠር ኦሮሞው አማራ፣ አማራውም ኦሮሞ ደማዊ ማንነት እንዳለው ያስረዳሉ።

ሁለተኛው የሕዝብ ትስስር ደግሞ የጋራ ታሪክ ሲሆን፤ ከመካከለኛው ዘመነ መንግሥት ከአፄ ሠርጸ ድንግል የወቅቱ ባህረ ነጋሽ ወይም የዛሬዋ ኤርትራ በነበረው የቱርኮች መስፋፋት ጦርነት ጀምሮ ‘አማራና ኦሮሞ ያልተጋሩት ታሪክ የለም’ ይላሉ። በ19ኛው ክፍለ ዘመንም ቢሆን በዛሬው ፖለቲካ በክፉ የሚነሱት ራስ ጎበና ዳጬ መሃዲስቶችን ድል በማድረግ የአገር ሉላዊነት ያስከበሩት በኦሮሞና አማራ ጥምረት እንደሆነ ይናገራሉ።

በዚህም “አማራና ኦሮሞ ያልተጋሩት ታሪክ፣ ይሄ ያንተ ታሪክ ይሄ የኔ ታሪክ የሚሉት የትኛው ነው” በማለት ይጠይቃሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ። ሶስተኛውና መልከ ብዙ ህዝባዊ የጋርዮሽ ማንነት የተገነባበት ደግሞ የባህል፣ የሃይማኖትና ሌሎች ማህበራዊ መስተጋብሮች እንደሆኑ ይጠቅሳሉ። ዛሬም በተጎራባችም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች አማራና ኦሮሞ የማይለዩባቸው ማህበራዊ ክዋኔዎች እንዳሏቸው ያነሳሉ።

ዛሬ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ቅራኔ በመፍጠር አማራና ኦሮሞ እንደ ጨቋኝና ተጨቋኝ ትሁት ትርክት በመፍጠር የተሰራበት የሕወሃት ፖለቲካዊ ሴራ እንጂ፤ የመንዝና የወለጋ ባላገሮች ቅራኔ እንዳልሆነ የታሪክ ተመራማሪው ይገልጻሉ ።

የሕወሃት ከፋፋይ ሰዎች ከመጸነሳቸው በፊት የኢትዮጵያ ብሄር/ብሄረሰቦች እንደነበሩ የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፤ ላለፉት 27 ዓመታት አንዴ የሕዝብ አንዴ የመደብ በማድረግ እርስ በርስ ለማጋጨት ያለመ ፖለቲካዊ ስሌት ነው ይላሉ።

በየትኛውም ዘመን፤ በየትኛውም ጦርነት አንዱ አንዱን ለመጉዳት ወይም ለመጥቀም የተደረገ ታሪካዊ ሁነት እንደሌለ ገልጸው፤ በኢትዮጵያ ታሪክ አንድ ሕዝብ ሌላውን ሕዝብ ጨቁኖ እንደማያውቅም ይናገራሉ።

በየትኛውም ‘የገብር፤ አልገብርም’ ዘመቻም አማራና ኦሮሞንም ሆነ ሌሎችንን ያሳተፈ እንጂ፤ የአንድ ብሔር ጉዳይ እንዳልሆነ አንስተዋል ምሁሩ።

ለዚህም አብነት በአርሲና ባሌ የማስገብር ጦርነት የነበረው የራስ ዳርጌ ሠራዊት አማራ ሳይሆን፤ በብዛት የሰላሌ ኦሮሞ እንደነበር ይጠቅሳሉ።

ታሪክ መጥፎም ጥሩም ጎን እንዳለው የጠቀሱት ምሁሩ፣ ትናንት ላይ ተመስርቶ ቁርሾ በመዝራት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ መሞከር ግን ከንቱነት እንደሆነ ይገልጻሉ።

በትናንት ፖለቲካ ከሰራንም ወደፊትም አንድ እርምጃ አያራምድም ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፣ ከትናንት ይልቅ ዛሬን የሚሟገት፣ ነገን የሚተነብይ ፖለቲካ ያሻል ነው ያሉት።

ፖለቲካ ልሂቁ እውነተኛ ፖለቲካ ለመስራት መሬት ላይ ያለውን እውነታ ማየት እንዳለበት ገልጸው፤ ከሕዝብ ጥያቄ ውጭ የሆኑ ፖለቲከኞች ጆሮ ሊሰጣቸው አይገባም በማለትም ያስገነዝባሉ።

አንዴ ትምክህት፤ ሌላ ጊዜ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት በሚል የሕወሃት ከፋፋይ ሥርዓት የትግራይን ሕዝብ እንኳን እንዳልጠቀመ በመግለጽ፤ ዛሬ በሕዝቦች መካከል ቅራኔ እንዳለ የሚተረከው ከዕውነታው በራቀ መልኩ እንደሆነ ገልጸዋል።

“አሮሞ ያለ አማራ፤ አማራውም ያለ ኦሮሞ ብቻውን አይቆምም፤ ኢትዮጵያም ሙሉ አትሆንም” ብለዋል።

1 COMMENT

  1. የጆዋር Al-Queorroo ይህን ያህል የዘር ጭፍጨፋና የንብረት ውድመት ማድረስ የቻለው በባለስልጣኖቾ እየታገዘ እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም። ከላይ እስከታች ያሉ አመራሮችና ካድሬወች ተመንጥረው ወጥተው በህግ መጠየቅ አለባቸው። ከተማውንና ህዝብን የመጠበቅ ሀላፊነታቸውን አልተወጡም። አይናቸው እያየ አገር ሲወድም ህዝብ ሲታረድ ዝም ማለታቸው የወንጀሉ ተሳታፊ ያደርጋቸዋል። ወንጀል መሠራቱን ማስተባበል ወይም መሸፋፈን አይቻልም። ፍትህ ። ፍትህ ለታረዲት፣ እሬሳቸው ለተጎተተው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.