አቶ ዳውድ ኢብሳ የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ተጥሎባቸው የነበረው የእንቅስቃሴ እቀባ ተነሳላቸው

ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀ-መንበር የሆኑት የአቶ ዳውድ ኢብሳ ቤት በፌደሬል ፖሊስ መከበቡንና ከቤታቸው መውጣትም ሆነ መግባት እንዳልቻሉ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች መግለጻቸው ይታወሳል።

ለሁለት ሳምንታት ያህል ከቤታቸው ሳይወጡና የሰልክ ግንኙነት ለማድረግ ሳይችሉ እንደቆዩ የሚናገሩት አቶ ዳውድ ኢብሳ ከትናንት አርብ ጀምሮ ከቤታቸው መውጣት እንደቻሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ዳውድ ተጥሎባቸው ስለነበረው የእንቅስቃሴ እቀባና እርሳቸው በሌሉበት በፓርቲያቸው ከፍተኛ አመራር አባላት ስለተካሄደው ስብሰባ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት አጭር ቆይታ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ “ሐምሌ 10 ላይ የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ፤ እኔ የፌደራል ፖሊስ አባላት ናቸው ብዬ ነው የማምነው፤ መልዕክት ተቀብለው የመጡ ናቸው ‘ለደኅነንትህ ሲባል ከቤት አትውጣ፤ በአካባቢውም ጥበቃ እናደርጋለን’ ሲሉ በጥሞና ነገሩኝ” ሲሉ ሁኔታውን ያስታውሳሉ።

አቶ ዳውድ ኢብሳም የጸጥታ ኃይሉ አባላት እንዳሉት የደኅንነት ጥበቃ ሊያደርጉላቸው እንደመጡ እንዳመኗቸውና የነገሯቸውንም እንደተቀበሉ ገልጸዋል።

በተጨማሪም በሳምንቱ ሐምሌ 17 ላይ “ቤት ውስጥ ያሉትም ወደ ውጪ እንዳይወጡ” የሚል ትዕዛዝ እንደደረሳቸው የገለፁት አቶ ዳውድ፤ ይህንንም ለደኅንነት ጥበቃ ነው ብለው በማሰብ እንዳመኑ ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ የዚያን ዕለት ከሰዓትና በማግስቱ የግል ስልካቸው መዘጋቱንና ግንኙነታቸው መቋረጡን በመግለጽ በደኅንነት ጥበቃ የተጀመረው ሁኔታ ወደ አሳሳቢ ሁኔታ መሻገሩን ጠቅሰዋል።

“ለጥበቃ የመጣው የፖሊስ ኃይልና ስልኬን የዘጋው አካል ግንኙነት ይኑራቸው አይኑራቸው የማውቀው ነገር የለም። ግን ስልኬ ከሐምሌ 17 ጀምሮ ተዘጋ” የሚሉት አቶ ዳውድ፤ “ሐሙስ ዕለት ከአሁን በኋላ ለደኅንነትህ ጥንቃቄ እያደረክ መንቀሳቀስ ትችላለህ መባላቸውን” ያስረዳሉ።

በዚህም መሠረት አርብ ዕለት ከቤታቸው ወጥተው ወደ የፓርቲያቸው ጽህፈት ቤት በመሄድ ጉዳያቸውን ከውነው እንደተመለሱ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የጽጥታ ኃይሎች በቤታቸው አካባቢ ተሰማርተው የደኅንነት ጥበቃ ማድረጋቸው ምናልባት አቶ ዳውድ እራሳቸው የሚያውቁት ስጋት ካለ በሚል ከቢቢሲ የተጠየቁት ሲሆን “ብዙ ጊዜ እየተደጋገሙ የሚመጡ ማስፈራሪያዎች፣ ማስረጃ መስሎ የሚመጣ ወሬ አለ። የዚህ ዓይነት መረጃ ተደጋግሞ ስለሚመጣ ትኩረት አልሰጠሁትም፤ ይህንን ፈርቼም ሥራዬን አላቆምኩም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

አቶ ዳውድ ባለፈው ሰሞን ባጋጠማቸው ሁኔታ ላይ ጥያቄ እንዳላቸውም ገልጸዋል።

“ስልኬ እንዲቋረጥ መደረጉን የደኅንነት ጉዳይ አድርጌ አልወሰድኩትም። ለሌላ ኦፕሬሽን እንደወሰዱት ነው የተረዳሁት። እነዚህ ሁለቱ ይገናኛሉ ብዬ ማመን ትንሽ ያስቸግረኛል፤ ነገር ግን ሊገናኙም ላይገናኙም ይችላሉ። ማወቅ አይቻልኩም” ያሉት አቶ ዳውድ፤ ቢቢሲ እስካናገራቸው ጊዜ ድረስ የእራሳቸው ስልክ እንደተዘጋ ሲሆን ለዚህ ቃለ ምልልስ እየተጠቀሙ ሌላ ቁጥር ነው።

በደኅንነት በኩል ስጋት እንዳለ ያልሸሸጉት አቶ ዳውድ ኢብሳ “ከአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች እና ከድምፃዊ ሃጫሉ ግድያ በኋላ፤ የሆነ ነገር ሊፈጠር እንደሚችል ማንም የሚረዳው ነገር ነው” በማለት ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት እንደሚንቀሳቀሱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እንዲህ ያለው ጥቃት በማንም ላይ ሊጋጥም ይችላል የሚሉት አቶ ዳውድ “ምክንያቱም መንግሥት የሕግ የበላይነትን አስከብራለሁ ብሎ ንፁሃን ዜጎችን ከማሰር ውጪ ለሕዝብ መረጃ አይሰጥም፤ የእነዚህ ሰዎች ገዳዮች እነማን ናቸው? የሚለውን ምርመራ አድርጎ ይፋ አያወጣም” በማለት “ስለዚህ ይህ በማንም ላይ በየትኛውም ጊዜ ሊመጣ እንደሚችል ተረድተን ነው የምንንቀሳቀሰው” ብለዋል።

አቶ ዳውድ ያልተገኙበት የፓርቲው ስብሰባ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ከመኖሪያ ቤታቸው እንዳይወጡ ተደርገዋል የሚለውን ዜና ተከትሎ፤ በግንባሩ ጽሕፈት ቤት የተካሄደው የድርጅቱ አመራሮች ስብሰባ “ሊቀ መንበሩን ለማንሳት ነው” የሚል መረጃ እንዲሰራጭ ምክንያት ሆኖ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም የግንባሩ አመራር ለሁለት የመከፈሉ ጉዳይ መነጋገሪያ ከመሆኑ በተጨማሪ አቶ ዳውድ ኢብሳ ከሊቀ መንበርነታቸው ተነስተው በአቶ አራርሶ ቢቂላ እንዲተኩ ተደርጓል የሚል ወሬም በስፋት ሲነገር ቆይቷል።

ይሁን እንጂ አቶ ዳውድ ኢብሳን እንዲተኩ ተመርጠዋል የተባሉት አቶ አራርሶ ቢቂላ “ዜናው ፍጽም ሐሰት ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

አቶ አራርሶ በኦነግ ጽሕፈት ቤት የተካሄደው ስብሰባ የሊቀ መንበሩ አቶ ዳውድ ኢብሳ እውቅና የነበረው መሆኑን በመናገር አሁንም የድርጅቱ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የግንባሩ ሊቀ መንበር በከተማው ውስጥ እያሉ በሚመሩት ድርጅት ስብሰባ ላይ ሳይገኙ ስብሰባው ስለመደረጉ አቶ ዳውድ የሚያውቁት ነገር ስለመኖሩ ከቢቢሲ ለተጠየቁት ጥያቄ፤ አቶ አራርሶ ቢቂላ በሰጡት መልስ “አቶ ዳውድ የተለየ ጉዳይ ስለገጠማቸው እየተንቀሳቀሱ የዕለተ ከዕለት ሥራቸውን ማከናወን አልቻሉም። ስለዚህም ስብሰባችን ላይ መገኘት አልቻሉም” በማለት ስለስብሰባው ከአቶ ዳውድ ጋር መነጋገራቸውን ገልጸው ነበር።

አቶ አራርሶ ቢቂላ ይህንን ይበሉ እንጂ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ገዳ ኦልጅራ (ዶ/ር) ግን “በአቶ አራርሶ ቢቂላ የተመራው ሰብሰባ የድርጅቱ እውቅና የለውም” በማለት ስብሰባው በግንባሩም ሆነ በሊቀ መንበሩ የማይታወቅ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ቢቢሲ ይህንኑ ውዝግብ ያነሳንላቸው አቶ ዳውድ፤ ስብሰባ መደረጉን እንደማያውቁ ገልፀው ከግንኙነት ውጪ ስለነበሩ ምን እንደተደረገ መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

“አሁን ገና ነው የማጣራው፤ የፓርቲውን አመራሮችም ሆነ አባላት የዕለት ተዕለት ሥራዎችን በጥሞና የሚከታተል በጉባዔ የተመረጠ የሕግ ቁጥጥር ኮሚቴ አለ። የእነሱን ውሳኔ ጠብቆ በእነሱ ትዕዛዝ መንቀሳቀስ የድርጅቱ ግዴታ በመሆኑ እርሱን እጠብቃለሁ” ብለዋል።

ከሁለት ሳምንት በኋላ ትናንት አርብ ወደ ፓርቲያቸው ጽህፈት ቤት እንዳመሩ የገለፁት አቶ ዳውድ፤ ስለ ጉዳዩ የማጣራት ሥራ ውስጥ አለመግባታቸውን በመግለፅ “በሚዲያ የሚናፈሰውን መድገም አልፈልግም” ሲሉ ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የአመራር ሹም ሽር ተካሂዷል ስለመባሉም “ስብሰባ አደረጉ የተባሉት አመራሮች፤ ጉዳዩ እዚያ ደረጃ እንዳልደረሰና እንዲህ ዓይነት እርምጃ እንዳልተወሰደ ነው የተናገሩት። ይህንንም ኮሚቴው ነው የሚያጣራው” በማለት ሹም ሽር እንዳልተካሄደ ግን ራሳቸው አቶ አራርሶ ቢቂላ ለመገናኛ ብዙሃን መናገራቸውን ጠቅሰዋል።

የፓርቲው አመራሮችና አባላት እስር

አቶ ዳውድ በየጊዜው የፓርቲው አመራሮችና አባላት እንደሚታሰሩባቸው ይናገራሉ። ይህንንም በተመለከተ ለምርጫ ቦርድ፣ ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ለዐቃቤ ሕግ ጽ/ቤት በየጊዜው ማመልከቻና የእስረኞችን ዝርዝር ማስገባታቸውን ይገልፃሉ።

ላቀረቡት ቅሬታ ምርጫ ቦርድ እንቅስቃሴ ያደረገ ቢሆንም “የሚጠበቅበትን ግዴታ ተወጥቷል ብለው እንደማያምኑ” ይናገራሉ። ከሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም ሆነ ከሌሎች አካላት ግን ምላሽ አላገኘንም ብለዋል።

ከድምፃዊ ሃጫሉ ግድያ ጋር ተያይዞም የፓርቲው አመራሮችና አባላት መታሰራቸውን የሚገልፁት አቶ ዳውድ፤ የ103 አመራሮችና የቢሮ ኃላፊዎች ስም ዝርዝር ከታሰሩበት ቦታና የት እንደታሰሩ የሚያሳይ ማመልከቻ ለዐቃቤ ሕግና ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ማስገባታቸውን፤ የተቀሩት አባሎቻቸውም የት እንዳሉ እንዲጣራላቸው ለቀይ መስቀል ማሳወቃቸውን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በፓርቲያቸው ጽህፈት ቤት ላይም ጥቃት መፈፀሙን በመጥቀስ “ይህ ባህል እየሆነ ነው፤ መስዋዕትነት ቢኖርም አሁንም እንቀጥላለን” ሲሉ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

BBC

1 COMMENT

 1. Dawud got released just to see where he goes and who he associates with. He knew he was being followed and tried to outrun those spies that were tracking him following him , he got arrested and been put back on house arrest again after he failed to ditch those that were tracking him.
  Dawud got arrested again accused of him and his associates boarding the light rail train transportation without paying the fare.
  Many said Dawud and his associates were seen running from the spies that were following them at the time they tried to enter the light rail train. He was let go from the house to find out where he goes who his contacts are. Since the spies knew Dawud knew he was being followed more police waited for Dawud & associates at the next light rail train station arrested them , taken to a house arrest again.
  It has been said more than half of the passengers of the Addis Ababa light rail train don’t pay the fares , the spies and the police only arrested Dawud and his associates, not everyone that did not pay the light rail train fares making this arrest a politically motivated action rather than a simple penality for fare evasion of the light rail train in Addis Ababa.

  አቶ ዳውድ ኢብሳ በድጋሚ በጸጥታ ኃይሎች ወደ ቤታቸው መወሰዳቸውን ግንባሩ አስታወቀ

  Nazret › index.php › 2016/02/25
  Web results
  Ethiopia: Of Light Rails and Famine: By the Mitmita Girls – nazret.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.