ለቸኮለ! የዛሬ ሰኞ ሐምሌ 27/2012 የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1. የትግራይ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ በፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ለተጻፈው ደብዳቤ ዛሬ በሰጡት ምላሽ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ለክልሉ ምርጫ አታካሂዱ ብለው የመጻፍ ሥልጣን እንደሌላቸው አሳስበዋል፡፡ ደብዳቤው የተጻፈው የፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ በሌለበት እና ክልሉ ምርጫ ይራዘምልኝ ብሎ ባልጠየቀበት ሁኔታ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ ክልሉ የምርጫ ሕግ የማውጣት፣ ምርጫ ኮሚሽን የማቋቋም እና ምርጫ የማካሄድ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን እንዳለው የጠቀሰው ደብዳቤው፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ እና ፌደራል መንግሥት በክልሉ ሕገ መንግሥታዊ መብት ጣልቃ እየገቡ እንደሆነ እና በዚሁ ጣልቃ ገብነት ለሚፈጠረው ችግር ተጠያቂዎቹ እነሱው ናቸው ሲል አስጠንቅቋል፡፡
2. የሕዳሴ ግድብ የቴክኒክ እና ሕግ ጉዳዮች ተደራዳሪዎች ነገ በግድቡ ውሃ ሙሌት እና አስተዳደር ላይ ውይይት እንደሚጀምሩ የግብጽ ጋዜጦች የሀገሪቱን የውሃ እና መስኖ ሚንስቴር ጠቅሰው ዘግበዋል፡፡ ነገ እና ከነገ ወዲያ የሚደረገው ድርድር፣ ሐሙስ በሦስትዮሽ የሚንስትሮች ስብሰባ ይገመገማል፡፡ ድርድሩ የሚቀጥለው መሪዎቹ ባለፈው ሳምንት በሰጡት አቅጣጫ መሠረት ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ድርድሩ የተቋረጠው የሱዳን ተደራዳሪዎች ድርድሩ እንዲራዘምላቸው በመጠየቃቸው ነበር፡፡ ቀደም ሲል የታቀደው ግን ድርድሩ ዛሬ እንዲጀምር ነበር፡፡
3. የትግራይ ክልል የልዩ ሃይል እና ሚሊሽያ ትናንት በመቀሌ ከተማ ወታደራዊ ትዕይንት እንዳደረጉ ከክልሉ ብዙኀን መገናኛ ዘገባ ተመልክተናል፡፡ ቀላል እና ከባድ መሳሪያ የታጠቁ እና ወታደራዊ ደንብ ልብስ እና መለዮ የለበሱት የልዩ ሃይሉ እና ሚሊሽያ አባላት ትዕይንቱን ያደረጉት በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች እና በመቀሌ ስታዲየም ነው፡፡ የሰልፉ ዐላማ ምን እንደሆነ ግን የክልሉ መንግሥት ያለው ነገር የለም፡፡
4. ባለፉት 24 ሰዓታት በተደረገ ምርመራ በኢትዮጵያ 583 ሰዎች ኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው ጤና ሚንስትር ሊያ ታደሠ በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡ 26 ሰዎች ደሞ በበሽታው ሕይወታቸው አልፏል፡፡ በሀገሪቱ በጠቅላላ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ19 ሺህ አልፏል፡፡
5. ሕወሃት በወልቃይት ጠገዴ አካባቢ የትግራይ እና አማራ ሕዝቦችን ለማጋጨት እያሴረ ነው ሲል የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ እንደከሰሰ ኢዜአ ዘግቧል፡፡ ሕወሃት የጦርነት ቅስቀሳ እያደረገ እና ሽብር እየፈጠረ በመሆኑ፣ ፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ ገብቶ ሁኔታውን እንዲያስቆም ኮሚቴው ጠይቋል- ብሏል ዜናው፡፡
6. የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከብሮድካስት ባለሥልጣን ማስጠንቀቂያ እንደደረሰው ዋዜማ ሰምታለች፡፡ መንግሥታዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ ማስጠንቀቂያ የደረሰው፣ በቅርቡ ያስተላለፋቸው ፕሮግራሞች የስነ ምግባር ጉድለት የታየባቸው፣ የሕግ ጥሰት ያለባቸው እና የብሮድካስት አዋጁን የጣሱ ሆነው በመገኘታቸው ነው፡፡ ጣቢያውን ለማስጠንቀቂያ የዳረጉት፣ በተለይ የድምጻዊ ሐጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ በሠራቸው ፕሮግራሞች እና ባቀረባቸው ቃለ ምልልሶች ነው፡፡
7. በነሐሴ ወር የመጀመሪያዎቹ 2 ሳምንታት 200 ሺህ የኮሮና ቫይረስ ናሙናዎችን ለመመርመር ዝግጅት እንደተደረገ ጤና ሚንስትር ሊያ ታደሠ ለኢቢሲ ተናግረዋል፡፡ የሀገሪቱን ምርመራ አቅምም በቀን አሁን ካለበት 11 ሺህ ወደ 15 ሺህ ለማሳደግ ታቅዷል፡፡ በሀገሪቱ በዚህ ሳምንት 3 ተጨማሪ መመርመሪያ ላቦራቶሪዎች ሥራ እንደሚጀምሩ ይጠበቃል፡፡ አሁን ሥራ ላይ ያሉት 46 ላቦራቶሪዎች ብቻ ናቸው፡፡
8. የኢትዮጵያ መርከብ እና ሎጅስቲክ ድርጅት የመንገደኞች መጓጓዣ ሊጀምር እንዳቀደ ካፒታል አስነብቧል፡፡ ድርጅቱ አዲስ የሚጀምረው የመጓጓዣ አገልግሎት፣ የውቂያኖስ ዳርቻ ላላቸው የአፍሪካ ቀንድ እና መካከለኛው ምሥራቅ ሀገሮች ካንድ የወደብ ከተማ ወደ ሌላ ወደብ ከተማ ሸቀጦችን እና ሰዎችን ማጓጓዝ ነው፡፡ ድርጅቱ ለመጭዎቹ 5 ዐመታት ያወጣውን ዕቅድ ለማሳካት፣ 2 መካከለኛ የማጓጓዣ መርከቦችን ለመግዛት አቅዷል፡፡ ድርጅቱ ካሁን በፊት ለመርከብ ግዥዎች የተበደረውን ብድር በጊዜው ሲከፍል ስለቆየ፣ ለአዲሶቹ መርከቦች ግዥ ዐለማቀፍ ብድር አጣለሁ የሚል ስጋት እንደሌለው ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ተብሏል፡፡
9. በሱማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ሃይል (አሚሶም) አዲስ ወታደራዊ ዋና አዛዥ እንደሾመለት አሚሶም በትዊተር ገጹ አስታውቋል፡፡ አዲሱ ተሹዋሚ ቡሩንዲያዊው ሌትናል ጀኔራል ዳዩሚድ ንዴግያ ናቸው፡፡ ዋና አዛዡ ሃላፊነቱን የተረከቡት፣ ከአምና ጥር ወር ጀምሮ ሰላም አስከባሪ ጦሩን ከመሩት ኢትዮጵያዊው ሌትናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ ነው፡፡[ዋዜማ ራዲዮ]

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.