ለቸኮለ! የዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 29/2012 የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1. የኦሮሞ ሜዲያ ኔትወርክ ጋዜጠኛ መለሰ ድርቢሳ በ3 ሺህ ብር ዋስትና እንዲፈታ ፍርድ ቤት እንደወሰነ አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል፡፡ ከጀዋር ሞሐመድ መኖሪያ ቤት ተይዘው የታሰሩት ጪብሳ አብዱልከሪም፣ ፈይሳ ባሳ፣ ሀሰን ጅማ እና ኬንያዊው ጋዜጠኛ ያሲን ጅማም ዋስትና ተፈቅዶላቸዋል፡፡ በጃምቦ ሁሴን መዝገብ ደሞ፣ የጀዋር ሞሐመድ ቤተሰቦች እና ጠባቂዎችን ጨምሮ፣ ሌሎች ስደስት ተጠርጣሪዎችም በ4 ሺህ ብር ዋስትና እንዲወጡ ተወስኖላቸዋል፡፡ ችሎቱ ለታሳሪዎቹ ዋስትና የፈቀደው፣ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ውድቅ በማድረግ ነው፡፡
2. የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ ብሄራዊ ሥራ አስፈጻሚ አባል ኂሩት ክፍሌ ዛሬ ከእስር እንደተለቀቁ ፓርቲው በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡ ፖሊስ ያቀረበውን ይግባኝ ውድቅ በማድረግ፣ ታሳሪዋ በ6 ሺህ ብር ዋስትና እንዲለቀቁ የወሰነው ከፍተኛው ፍርድ ቤት ነው፡፡ ሰኞ’ለት ፖሊስ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ውሳኔን በመጣስ ነበር ታሳሪዋን ሳይፈታ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ የጠየቀባቸው፡፡
3. ባለፉት 24 ሰዓታት ምርመራ፣ 459 ሰዎች ኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው ጤና ሚንስትር ሊያ ታደሠ በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡ 13 ሰዎች ደሞ በኮረና ቫይረስ አማጩ በሽታ ሕይወታቸው አልፏል፡፡
4. የሕዳሴው ግድብ ሦስተዮሽ ድርድር ወደቀጣዩ ሳምንት ተራዝሟል፡፡ ኢትዮጵያ ለሕዳሴው ግድብ ውሃ አሞላል ያወጣችውን ደንብ ለሁለቱ ሀገራት እንዳቀረበች የውሃ እና ኢነርጅ ሚንስቴር በትዊተር ገጹ ባሰራጨው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ምዕራፍ ውሃ ሙሌት ስምምነት በቶሎ ፈርማ፣ አጠቃላይ ስምምነት በሂደት ለመድረስ ድርድሩ እንዲቀጥል እንደምትፈልግም ተገልጧል፡፡ ድርድሩ በመጭው ሰኞ ይቀጥላል- ብሏል የሚንስቴሩ መግለጫ፡፡ ግብጽ በበኩሏ ውስጣዊ ምክክር ለማድረግ፣ ሱዳን ደሞ ኢትዮጵያ ሁሉን ዐቀፍ እና አስገዳጅ ስምምነት ላለመፈረም አቋም መያዟን በመቃወም ድርድሩን እንዳቋረጡ በየፊናቸው አስታውቀዋል፡፡
5. ግብጽ እና ሱዳን ኢትዮጵያ ለሕዳሴው ግድብ ውሃ አሞላል ያቀረበችውን ደንብ እየተቃወሙት እንደሆነ የሀገራቱ ዜና አውታሮች ዘግበዋል፡፡ ኢትዮጵያ ያቀረበችው ምክር ሃሳብ፣ ስለ ግድቡ አሞላል እንጅ፣ ስለ ግድቡ አስተዳደር፣ ስለ አስገዳጅ ስምምነት እና ስለ አስገዳጅ የወደፊት ውዝግብ አፈታት ሥርዓት ምንም የያዘው ነገር የለም- ብለዋል ግብጽ እና ሱዳን፡፡
6. በኢትዮ ቴሌኮም ከፊል ሽያጭ ላይ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ ባዘጋጀው ምጥን የፖሊሲ ሃሳብ ላይ ውይይት እንዳዘጋጀ ፓርቲው በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡ በመጭው ቅዳሜ በሚካሄደው ውይይት፣ አንጋፋዎቹ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በፍቃዱ ደግፌ (/ዶ/ር) እና ዐለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) ጥናታዊ ወረቀቶችን ያቀርባሉ፡፡ ፓርቲው በዚሁ ጉዳይ ላይ ያዘጋጀውን ምጥን የፖሊሲ ሃሳብ ቀደም ብሎ ይፋ ያደርጋል፡፡
7. የኬንያ መንግሥት ለራስ ገዟ ሱማሌላንድ የሀገርነት ዕውቅና ለመስጠት እየተነጋገረበት እንደሆነ የሱማሊያው ጋሮዌ ድረገጽ ውስጠ አዋቂ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ ካቢኔው ያዋቀረው የቴክኒክ ቡድን በቅርቡ ጥናቱን አጠናቆ ያቀርባል ተብሏል፡፡ በቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት የሱማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ወደ ኬንያ እንደሚያቀኑ እና እንደ ሉዓላዊ ሀገር መሪ አቀባበል እንደሚደረግላቸው ዘገባው አክሏል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.