በደቡብ ክልል የተነሡ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማስተናገድ የተጀመረው እንቅስቃሴ ጥሩ መልክ እየያዘ መምጣቱን ርዕሰ መስተዳድሩ አስታወቁ

የደቡብ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባኤ በሀዋሳ በመካሄድ ላይ ይገኛል። በክልሉ በየአካባቢ የተነሡ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ለማስተናገድ የተጀመረው እንቅስቃሴ ጥሩ መልክ እየያዘ መምጣቱን ርእሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ በክልሉ ውስጥ በሚታየው የአለመረጋጋት ሁኔታ፣ የአደረጃጀት፣ የወሰን ማካለል እና የማንነት ጥያቄዎች፣ የመሠረተ ልማት አቅርቦት ፍትሐዊነት፣ የግብዓት ዕዳ አመላለስ፣ የሥራ እድል ፈጠራ፣ ሕገ ወጥ የኢንቨስትመንት እና የከተማ መሬት ወረራ፣ የሰላም እና ፀጥታ ሁኔታ፣ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች እና ሌሎችም አንገብጋቢ ጉዳዮች እና የሕዝብ ስጋቶች ላይ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ አመልክቷል።
በሰላም እና ፀጥታ በኩል ግጭቶችን፣ አለመግባባቶችንና የሕዝብ ጥያቄዎችን በአግባቡ ያለመያዝ ሁኔታ ችግር መፈጠሩ ላይ በየአካባቢው የሚታዩ መደበኛ ያልሆኑ አደረጃጀቶች እና አንዳንድ አመራሮች ድርሻ አላቸው ብሏል።
የምክር ቤቱ አባላት የክልሉ ሕዝብ የልማት እና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲመለሱ የሚያደርጉት ጥረት እንዳለ ሆኖ እነዚህን የሕዝብ ፍላጎቶች ከበጀት ውስንነት ጋር አያይዘው ሊመለከቱ ይገባል ሲሉ ርእሰ መስተዳድሩ ምላሽ ሰጥተዋል።
ክልሉ በበርካታ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች እና አስቸጋሪ ወቅታዊ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖም በተለያዩ ዘርፎች ያስመዘገበው የእቅድ አፈጻጸም ውጤት አበረታች መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በተለይም ደግሞ ክልሉን ወደነበረበት የተረጋጋ ሰላማዊ ሁኔታ በመመለስ የሕዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ የተደረገው ጥረት ስኬታማ እንደነበር አቶ ርስቱ ተናግረዋል።
በክልሉ በአብዛኛው የሚታዩ ግጭቶች መንስኤ የመዋቅር ጥያቄ ቢሆንም ከፍተኛ መሻሻሎች እንዳሉም ተብራርቷል።
ርእሰ መስተዳደሩ ግጭቶችን በአግባቡ የመያዝ እና ለሚነሡ ጥያቄዎች ወቅታዊ ምላሽ የመስጠት አሠራሮች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከደቡብ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።
ምክር ቤቱ በሦስት ቀናት ቆይታው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ውይይት በማድረግ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።
አብመድ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.