በኢትዮጵያ ያልነበሩ የአክራሪ እስልምና ጠባያትና አዳዲስ ጥያቄዎች

አክራሪዎቹ እስልምናና ክርስትና በኢትዮጵያ ውስጥ የነበሯቸው የአብሮነት እሴቶችን የመናድ፣ ያልነበሩ የአክራሪነት ጠባያትን የማሳየትና አዳዲስ ጽንፈኛ ጥያቄዎችንም መሰንዘር ጀምረዋል!

  • ‹‹ክርስቲያኖች ቀና ካሉ አንገታቸውን በሜንጫ ነው የምንላቸው!›› እያሉ የዛቱትም በመካ መዲና ሳይሆን እስልምናን አክብራ በእንግድነት በተቀበለችና በነቢያቸውም አንደበት ‹‹አትንኳት›› በተባለችው በዚህቺው ሀገር ውስጥ ነው፤ እንደተናገሩትም ደግሞ ይህንኑ አድርገዋል!
  • በነባር የክርስትና ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ጭብጦች ላይ ትንኮሳዎችን መሰንዘር ጀምረዋል፡- ‹‹የጥንቱ ክርስትና ከእስልምና ጋር አንድ ነበር››፣ ‹‹የኢየሱስ ሐዋርያት ሙስሊሞች ነበሩ››፣ ‹‹ኢትዮጵያ ዓመተ ምሕረት የሚል አቆጣጠር መከተል የለባትም›› እያሉ ነው፤ ክርስቲያናዊ እሴቶችን በእስልምና መነጽር ለማየት እየሞከሩ ነው፤ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን እንደ አመጽ መሪ ፖለቲከኛ ይከሳሉ፤ የቤተ ክርስቲያን ታሪክን የማፋለስና የማጠልሸት ሥራዎች ላይ ተጠምደዋል፤ ‹‹አንዱ በጋሻ፣ ሌላው በትከሻ›› የሚል አዲስ የይዞታ ጥያቄና ክስም እያስተጋቡ ነው!
  • የኢትዮጵያ ታሪክን በአዲስ መልክ ለመከለስ በርካታ ጥረቶችን እያደረጉ ነው፡- እስልምና የበላይ የሆነባት ‹‹አዲሲቷን ኢትዮጵያ›› የመመሥረት ዓላማ አላቸው፤ ግራኝ መሐመድን እንደ ብሔራዊ ጀግና በማወደስና ዘመነ መሳፍንትን በማድነቅ ታሪካዊውን የኢትዮጵያ መከራ መናፈቅ ጀምረዋል፤ በታሪክ የማይታወቀውን ‹‹አልነጃሺ›› የሚባል ሙስሊም ንጉሥ በምናብ ስለው ለማንገሥ እየታገሉ ነው!
  • ኢትዮጵያዊ ሆኖ በአረብ ጭንቅላት ማሰብ፣ ያልተለመዱ የጭካኔ ጥቃቶችን በገዛ ወገን ላይ መሰንዘር፣ ታሪክን እያጣመሙ መጻፍና መሰል ትንኮሳዎችን መፈጸም የአንድነቱን ገመድ የሚያላላ፣ ነባሩንም የአብሮነት እሴት የሚያደበዝዝ ስለሆነ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሁሉ ቆም ብለው እንዲያስቡ ለመጠቆም እንወዳለን!!!
“““““““““““““““““““““““““““““““
እስልምና ውስጥ ከአገር አቀፍ እስከ ዓለም አቀፍ የገነኑ፣ እርስ በርስም መራራ ትግል የሚያካሂዱ ሁለት ርዕዮተ ዓለሞች አሉ፡- ወሃቢያ እና አል-አሕበሽ የሚባሉ፡፡
አንደኛው፡- እስልምና ፖለቲካዊ መሆን አለበት፣ እስልምና ከሌሎች ጋር አንድ ላይ መኖር የለበትም፣ እስልምናን ያልተከተለ በእስላም አገር መኖር የለበትም፣ ይህንን ለማስፈን አክራሪነት እና ኃይልን መጠቀም ያስፈልጋል፣ ክርስትያኖችና አይሁዶች የእስልምና ጠላቶችና የተጠሉም ናቸው፣ ኢትዮጵያ የእስላም አገር መሆን አለባት የሚል ውስጣዊ እንቅስቃሴን የሚመራ በዓላማ የሚንቀሳቀስ ዓለም አቀፍ ጽንፈኛ ቡድን ሲሆን፤ ይህ የዋሃቢያው ክንፍ ነው፡፡
ሁለተኛው፡- የመጀመሪያውን የሚነቅፍና እስልምና ከሌሎች ጋር መኖር ይችላል፤ እስልምና ፖለቲካዊ መሆን የለበትም፣ እስልምናን ያልተከተለ ተከብሮ መኖር አለበት፣ አክራሪነት የእስልምናን ስም ያስጠፋልና ትክክልም አይደለም፣ ከክርስትያኖችና ከአይሁዶች ጋር በሰላም መኖር እንችላለን የሚል፣ ኢትዮጵያ የመቻቻል ምሳሌ ናት የሚለውና በኢትዮጵያዊው ሼክ አብደላ የሚመራው የአል-አሕበሽ ክንፍ ነው፡፡
ከእነዚህ ሁለት የእስልምና አመለካከት ምድቦች መካከል ነባሩን የኢትዮጵያ እስልምና የሚወክለው ሁለተኛው ነው፡፡ ከነስያሜውም ‹‹ኢትዮጵያውያኖቹ›› ተብሎ የሚጠራ (“አል-ሐበሻ” ወይንም “አል-አህባሽ” የሚባል)፣ ከሐረር ፈልሰው አሁን በሊባኖስ የሚኖሩት ኢትዮጵያዊው ሼክ አብደላ ርእዮት ነው፡፡ በዚህ አገባቡ መሠረት ‹‹ሐበሻ›› የሚለው በአፍሪካ ቀንድ ያሉትን በሙሉ (ክርስቲያኖችን ብቻ ሣይሆን ሙስሊሞችን ጨምሮ) የሚያመልክት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ይህ ከየትኛውም ማኅበረሰብና የእምነት ክንፍ ጋር ተቻችሎ የመኖር ፍላጎትና አካሄድ ያለው ‹‹ሰላማዊ›› እስልምና ምድብ ነው፡፡ እናም ‹‹ኢትዮጵያን አትንኳት›› የሚለውን የነቢዩ መሐመድን ትእዛዝ የሚከተል አመለካከት ሊባል ይችላል፡፡
በአንጻሩ ደግሞ በጽንፈኛ የአረብ ሀገራት የሚዘወረው የዋሃቢዝም አክራሪ እስልምና እንቅስቃሴ በሳውዲ አረቢያ (እና መሰል የአረብ ሀገራት ውስጥ ጭምር) በትንቢት መልክ፡- ‹‹እነዚያ ቀጫጭን እግር ያላቸው ኢትዮጵያውያን በስተመጨረሻው ካኣባን /በመካ የሚገኘውን ጥቁር ድንጋይ/ ያጠፋሉ›› ተብሎ የተነገረውን ትንግርት እንደዋና ቁምነገር ይዘው ‹‹ኢትዮጵያ የእስልምና ጠላት ናት›› ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ እናም በኢትዮጵያ ምድር ላይ እየተካሄደ ያለው የእነዚህ ሁለቱ እስላማዊ ምልከታዎች ጦርነት ነው፡- ኢትዮጵያ ‹‹ልትነካ አይገባም›› በሚሉትና ‹‹መጥፋት አለባት›› በሚሉት መካከል፡፡
የዋሃቢዝም ዋና ትኩረት እስልምና ‹‹የሰላም ሃይማኖት›› ከሚለውም አስተምህሮ አልፎ ‹‹እስልምና ባለበት አገር ሁሉ የበላይነትን መያዝ አለበት›› የሚል መርሕን የሚከተል ነው፡፡ ይህንኑ አቋሙን እውን ለማድረግ ደግሞ የትኞቹንም የትግል አማራጮችን ለመጠቀም ይሞክራል፡፡ አሁን እንደ ‹‹አዲስ ክስተት›› በኢትዮጵያ ውስጥ የምናስተውለው፣ ከነባሩ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች እሴት ጋር በተቃራኒ የቆመው፣ ለዚህ ጽሑፋችንም መነሻ የሆነው ይኸኛው ቡድን ነው፡፡ ምክንያታችን ደግሞ እስልምናና ክርስትና በኢትዮጵያ ውስጥ የነበሯቸው የአብሮነት እሴቶችን የመናድ፣ ያልነበሩ የአክራሪነት ጠባያትን የማሳየትና አዳዲስ ጽንፈኛ ጥያቄዎችንም መሰንዘር ተጀምሯልና ‹‹እንደ ጥንተ አብሮነታችን ብንከባበር ይሻላል›› ለማለት፡፡ አክራሪ እስልምና በኢትዮጵያ ውስጥ ብቅ እያለ ነው ከምንልባቸው ማሳያዎች መካከል ዋና ዋናዎቹን እንደሚከተለው እንጠቁም፡-
1. አረባዊ ጠባያት፣ ጭካኔ የተሞላባቸው ጥቃቶች
==============================
ክርስትናም ሆነ እስልምና መነሻቸውን መካከለኛው ምሥራቅ ያድርጉ እንጂ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ግን አስተሳሰባቸውን፣ ጠባያቸውንና ድርጊቶቻቸውን ‹‹ኢትዮጵያዊ›› አድርገው ቀይረውታል እንጂ አይሁዳዊ ወይም አረባዊ አድርገው አላስቀጠሉትም፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ መሠረታዊውን አስተምህሮ እስካላቃወሰ ድረስ ተገቢና ቅቡልነትም ያለው ነው፡፡ በወሃቢዝም የሚዘወረው አክራሪ እስልምና መቀበል የማይፈልገው ግን ይህንን ሐቅ ነው፡፡
ዛሬ ላይ በሀገራችን ውስጥ የሚስተዋሉ አንዳንድ ወጣ ያሉ እንቅስቃሴዎች የጥንቶቹ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ዘይቤ ሣይሆን አረባዊ ጠባያትን የተላበሰ መሆኑ አሳሳቢ ነው፡፡ ‹‹ምላሽ ለእስልምና›› (answering-islam) የሚል ገጽ ላይ እንደተዘገበው ፕሮፌሰር አርሊች የተባለ የታሪክ ተመራማሪ፡- ‹‹የክርስትያን ኢትዮጵያ ዓይናችን እያየ አዲስ ትርጉም ልትይዝ ምንም አልቀራትም›› በማለት ስጋቱን ከአቅጣጫ ጠቋሚ እውነቶች ጋር ‘Saudi Arabia & Ethiopia’ በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ማቅረቡ ተዘግቧል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ አዲስ ትርጉም ልትይዝ ነው›› የሚሉትም እስላማዊ አገር እንድትሆን ከፍተኛና ሥር የሰደደ ታሪካዊ እንቅስቃሴ መኖሩን በመጠቆም ነው፡፡ ይህም ሲባል፡- በአለባበስ፣ በአስተሳሰብ፣ በአመጋገብ፣ በሥነ-ምግባር…ወዘተ. የኢትዮጵያውያኑ መልካም እሴቶች ተረስተው አረባዊ እየሆኑ መምጣታቸው ነው፡፡
ሌላው ገራሚ ነጥብ ደግሞ በድርጊታቸው አረባዊ ሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖሩ የሀገሪቱ ሕግና ሥርዓት ሁሉ ‹‹በእነርሱ ልክ›› እንዲሰፋ መፈለጋቸው ነው፡፡ ምክንያቱም፡- «የሀገሪቱ አካሄድ በአግላይ ፖሊሲዎች የተሞላ ነው…ምክንያቱም በርካታ (የኢትዮጵያ) መሥሪያ ቤቶች የሙስሊሙን እሴት ከግንዛቤ ያላስገቡ፣ የአለባበስ ሕግ እና ሃይማኖታዊ ግዴታዎቹንም እንዳይተገብር የሚያቅቡ ሕግጋት እና መመሪያዎችን በማውጣት ሙስሊሙ ራሱን እንዲያገል አድርገውታል» የሚል የቅሬታ ጽሑፍ ማስነበብ ጀምረዋልና (ቀሠም፤ መስከረም 2011 ዓ.ል፤ ቅጽ 1 ቁጥር 1)፡፡
እነዚህ አረባዊ ጠባያት እየተስፋፉና እየተለመዱ በመጡ ቁጥር ደግሞ በዚያው ልክ አረባዊ የጭካኔ ድርጊቶችም በኢትዮጵያ ውስጥ መታየት ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ በእርግጥ በአክራሪ ሙስሊሞች እየተደረጉ ያሉ ጥቃቶች በዋናነት ከአስተምህሮዎቻችን ልዩነቶች የተቀዱ ለመሆናቸው ምንም ጥርጥር የለውም፤ ‹‹መሞት ሰማዕትነት ነው›› ከሚለው የክርስትና አስተምህሮና ‹‹መግደል ያጸድቃል›› ከሚል የእስልምና አቋም፡፡ ይህ የአስተምህሮ ልዩነት የማሕቀፈ እሳቤና የአካሄድ፣ የአቋምና የድርጊት ልዩነቶችንም እንደሚያመጣ ይታወቃል!
በዋና አክቲቪስታቸው ጃዋር መሐመድ በኩል ሚዲያ ላይ ቀርበው፡- ‹‹ክርስቲያኖች ቀና ካሉ አንገታቸውን በሜንጫ ነው የምንላቸው!›› እያሉ የዛቱትም በመካ መዲና ሳይሆን እስልምናን አክብራ በእንግድነት በተቀበለችና በነቢያቸውም አንደበት ‹‹አትንኳት›› በተባለችው በዚህቺው ሀገር ውስጥ ነው፡፡ እንደተናገሩትም ደግሞ ይህንኑ አድርገዋል፡፡ በአክራሪ እስልምና አማካይነት በኢትዮጵያ ላይ (በተለይም በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ) የተቃጡ፣ ጭካኔን የተሞሉ ሰቅጣጭ ጥቃቶች ተቀንጭበው ራሱን በቻለ ክፍል የሚቀርቡ ይሆናል፡፡
2. በነባር ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ጭብጦች ላይ ትንኮሳዎችን መሰንዘር
========================================
ምንም እንኳን ክርስትናና እስልምና በሰላምና በመገነዛዘብ አብሮ መኖር አለባቸው በሚለው መርሕ ብንስማማም አብረን ለመኖር ስንል ልናስተካክላቸው የማይገቡ ሃይማኖታዊ ጭብጦች፣ በዘመናት ለውጥና በወቅታዊ ክስተቶች የማይከለሱ ሐቆች መኖራቸውን ግን ባለመካድ ነው፡፡
2.1. ‹‹የጥንቱ ክርስትና ከእስልምና ጋር አንድ ነበር››
——————————————————–
እንደ ዐብዱልጀሊል ያሉ አዳዲስ የፈጠራ ተራኪዎች የጥንቱ ‹‹አሃዳዊ›› ክርስትና (ሐነፊ) ከእስልምና ጋር አንድ እንደነበር፣ በጊዜ ሂደት ግን አንዳንድ የቤተ ክህነት ደባትራን ከጥንቱ አስተምህሮ አፈንግጠው እስልምናን እንደ አዲስ እምነት መቁጠር መጀመራቸውን ይተርኩልን ጀምረዋል፡፡ ለዚህ ድምዳሜአቸው እንደ ማሳያ የሚያቀርቡት ደግሞ ንጉሥ አርማሕ (በእነርሱ አጠራር ‹‹ነጃሺ››) በስደት ወደ ኢትዮጵያ የመጡትን የነቢዩን ተከታዮች ምን እንደሚያምኑ ጠይቆ ከተረዳ በኋላ ‹‹የእኛና የእናንተ ሃይማኖት ምንጭ ይቺን ያክል ልዩነት የለውም›› ብሏል የሚል ነው (ዐብዱልጀሊል ዐሊ፤ ተምኔታዊ ደሴት፤ 2012፡48)፡፡
በመሠረቱ ንጉሡ ይህንን ብሏል ከተባለ እንኳን በመልካም እሴትነቱ ተቀብሎ የተናገረበትን ትክክለኛ ዐውድ ማስተዋል ተገቢ ይሆናል፡፡ ምናልባት በወቅቱ በንጉሡ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት ለመጨመር ሲሉ እምነታቸውን ከክርስትናው ጋር አመሳስለው ነግረውት እንደሆንም መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ደግሞም የዛሬዎቹም ሙስሊሞች እንደሚናገሩት (ትርጓሜው ሌላ ቢሆንም) ‹‹በአንድ አምላክ እናምናለን፣ ጣዖት አምልኮን እንቃወማለን›› ብለውት ከሆነ ‹‹አምላክ›› የተባለውን አላህን እንደ እግዚአብሔር ተቀብሎ፣ ጣዖት አምልኮን መቃወማቸውንም አይቶ ‹‹አንድ ዓይነት እምነት አለን›› ቢል እንኳንስ ያኔ ዛሬም ላይ ስህተትነቱ ጎልቶ አይታይም፡፡
ችግሩ እስልምና በትክክል እነርሱ እንደገለጹት ነው ወይ? አላህና እግዚአብሔርስ አንድ ናቸው ወይ? የሚሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች ሲነሱ የጸሐፊው አመክንዮ መፈራረስ ይጀምራል፡፡ ለማንኛውም ይህን መሰል አዲስ ታሪክ ለመጻፍ እየሞከሩ ያሉት የእስልምናን ተቀባይነት ከፍ ለማድረግ ነው፡፡ ‹‹እስልምና ይሁዲነትንና ክርስትናን ወደ አብርሃማዊ አሓዳዊ እምነት ለመመለስ በተሐድሶነት የመጣ ሃይማኖት ነው›› የሚለው አገላለጻቸውም ይህንኑ የሚያመላክት ነው (ዐብዱልጀሊል፤ 2012፡36-37)፡፡
2.2. ‹‹የኢየሱስ ሐዋርያት ሙስሊሞች ነበሩ››
————————————————
ከላይ ከተነሳው ስኁት አመለካከታቸው ተነስተው እንዲያውም ‹‹የናግራን (ደቡብ የመን) ክርስቲያኖች ከነቢዩ መሐመድ የእስልምና ሕዳሴ በፊት የነበሩ አሃዳውያን ክርስቲያኖች (ሀነፊዎች ወይም ቀደምት ሙስሊሞች) ነበሩ›› ማለትም ጀምረዋል (ዐብዱልጀሊል፤ 2012፡35)፡፡ እናም ‹‹ሙስሊም›› የሚለው ቃል የነቢዩ መሐመድን ተከታይነትን የሚያመለክት አይደለም፤ ቃሉ ከነቢዩም በፊት ነበርና ሲልም ይገልጻል፡፡
መጽሐፉ ገጽ.37 ላይ የቁርዓንን ቃል ጠቅሶ ‹‹እምነታቸው እስልምና ነበር፣ እነርሱም ሙስሊሞች ነበሩ›› የሚላቸው፡- ኖህ፣ አብርሃም፣ እስማኤል፣ ያዕቆም፣ ሙሴ፣ ዮሴፍ፣ የኢየሱስ ሐዋርያት (አልቁርአን 3፡52)፣ ሰሎሞንና ንግሥተ ሳባ፣ ወዘተ፣ ነው፡፡ እንዲያውም በአጼ ካሌብ ዘመነ መንግሥት የነበረው ክርስትና አላህ ሙስሊሞች መሆናቸውን የመሰከረላቸው (አሃዳውን) ናቸው፤ ንጉሡም ከአክሱም ደቡብ የመን (ናግራን) ድረስ ዘልቆ ጥብቅና የቆመላቸው ለእነዚህ ነው እንጂ አሁን በኢትዮጵያ ‹‹ክርስትና ተብሎ ለሚታወቀው›› ተከታዮች አይደለም እስከማለትም ደርሷል (ዐብዱልጀሊል፤ 2012፡40)፡፡ ይህንን ከመሰሉ የፈጠራ ድርሰቶችና የትንኮሳ ትርክቶች በላይ የአክራሪ እስልምና ጥቃት ከየት ይምጣ! በአንድ በኩል ክርስቲያኖችን ለብቻ ለይቶ ‹‹የመጽሐፉ ባለቤቶች›› የሚል ቁርአናቸው በአንጻሩ ደግሞ ‹‹ጥንቱን ሙስሊም ነበሩ›› ብሎ አዲስ ተረት መፍጠር ለምን እንዳስፈለጋቸው እነርሱ ራሳቸው ያውቁታል፡፡
2.3. ዓመተ ምሕረት መባል የለበትም!
——————————————
ዐብዱልጀሊል ዐሊ ‹‹ተምኔታዊ ደሴት›› በሚለው የጽርፈት ድርሰቱ፣ ገና ከመጽሐፉ ዋና ገጽ ላይ ጀምሮ ዓ.ም (ዓመተ ምሕረት) ላለማለት ዓ.ኢ. (ዓመተ ኢትዮጵያ?) ይለዋል፡፡ በሌሎች የመጽሐፉ ውስጠኛ ገጾች ውስጥ ደግሞ ዓ.ል (ዓመተ ልደት) እያለ ይዘልቀዋል፤ የክርስቶስን መወለድ ብንቀበል እንኳን በእርሱ አማካይነት ዓለም ‹‹ምሕረት›› ማግኘትን ግን አንመሰክርም በሚመስል አገላለጽ፡፡
በመሠረቱ አብዛኛው የዓለማችን ሀገራት ‹‹ዓመተ ምሕረት›› የሚለውን የሚጠቀሙት የዘመናቱን ቀመር ለመለየት ብቻ፣ አብዛኛውም ሰው ስለተስማማበት እንጂ የግድ በአገላለጹ ስላመኑበት አልነበረም፡፡ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችም ይህንኑ ተገንዝበው በዚሁ አግባብ ሲጠቀሙ ኑረዋል፤ ‹‹በክርስቶስ አዳኝነት አምነናል›› ግን አላሉም፡፡ ይህንን የቀመር ዘይቤ መከተላቸውም የእስልምና እምነታቸውን እንዲጠራጠሩም ሆነ እንዲቀይሩ አላስገደዳቸውም፡፡ ኢትዮጵያዊ ስለሆኑ ብቻ ግን ሀገሪቱ በምትቆጥርበት የአቆጣጠር ዘዴ ሲጠቀሙ፣ ሃይማኖትን ከአረባውያኑ ጋር እንደሚጋሩት ሁሉ ባህልና ቀመረ አዝማናትን ደግሞ ከኢትዮጵያውያኑ ጋር ተጋርተው በሰላም ሲኖሩ ነበር፡፡ እናም መስከረም 1 ቀንን የጋራ ዘመን መለወጫቸው አድርገው ሲያከብሩ፣ ታኅሣሥ 29 ቀንን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደትን ምክንያት አድርገው ከክርስቲያን ወገኖቻቸው ጋር መዓድ ሲቆርሱና ጥር 11 ቀንን ወደ አደባባይ ወጥተው ታቦት ሲሸኙ የኖሩ ናቸው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች፡፡ አሁን ላይ ደርሶ ግን ‹‹ዓመተ ምሕረት›› ብለህ እንዳትጽፍ፣ እንዳታነብም ተገዝተሃል የሚሉ አክራሪዎቹ ብቅ ብለዋል፡፡ ነገሩ ቀላል ቢመስልም እያደር ግን ወደ ሌላ አቅጣጫ ሊያመራ እንደሚችል ማጤን ተገቢ ነው፡፡ ማንም ቢሆን በኢትዮጵያ ምድር ላይ እስከኖረ ድረስ እንደ ኢትዮጵያ አስቦና በሕገ መንግሥቷም ተገዝቶ ይኖር ዘንድ ግድ ይለዋልና፡፡
2.4. ክርስቲያናዊ እውነቶችን በእስልምና መነጽር ለማየት መሞከር
—————————————————————-
ዛሬ ዛሬ በአክራሪ ሙስሊሞቹ ዘንድ ‹‹የእስራኤል አምላክ›› የሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃልን ከኢትዮጵያዊ ክርስቲያን መስማት ሌላ ትርጉም እየተሰጠው ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ዶ/ር ሀብተ ማርያም አሰፋን (የኢትዮጵያ ባህሎችና ጥያቄዎች፤ 1986፡155) እንደ ምንጭ በመጠቀም ‹‹ክርስቲያኖች ‹የእስራኤል አምላክ› የሚለውን ቃል የሚጠቀሙት ራሳቸውን ከኢትዮጵያዊነት ለማሸሽ፣ ራሳቸውንም ከእስራኤላውያን ጋር ለማስተሳሰር የሚደረግ ሩጫ ነው›› በማለት ለመናገር ጀምረዋል፡፡ ምንም እንኳን የቃሉ ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ቢሆንና ሃይማኖታዊ አንድምታም ቢኖረው እነርሱ ግን ትክክለኛ ትርጓሜውን ከባለቤቶቹ ጠይቀው ከመረዳት ይልቅ ከዘመናዊ ፖለቲካቸው ጋር ማላተሙን እንደ አማራጭ ወስደውታል፡፡
እናም በዚህ የክርስቲያኖቹ ‹‹የእስራኤል አምላክ›› ንግግርና ጸሎት መነሻነት ከ1270-1966 ዓ.ም በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ሁኔታ ከትክክለኛ የክርስትና አካሄድ ወደ ‹‹ሰለሞናዊት ኢትዮጵያ›› የተቀየረበት ነው በሚል ይከሷት ይዘዋል (ዐብዱልጀሊል፤ 2012፡72)፡፡ በዚህ ድርጊታቸው የአክሱማዊውንና ዛጔዌውን ጊዜያት አክስማ ወደ ‹‹ሸዋ ንግሥና›› እንዳቀናች በመናገር ዳር ዳር የሚሉት ዛሬ ላይ ‹‹የአማራ ሃይማኖት›› ለሚሏት ሐሜታቸው መንገድ ለመጥረግ ይመስላል፡፡
የአክራሪ እስልምናው መነጽር በበጎ ቅላጼ ካልተመለከታቸው ነገሮች ውስጥ ሌላኛው፡- ‹‹ዓርብ ዓርብ ይሸበራል ኢየሩሳሌም›› የሚለውን ዘለሰኛ ነው፡፡ ‹‹ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በዚህ መዝሙሯ መላ ዓለምን በአፍሪካ ምድር አቀናጅታ የመስቀል ጦርነትን ለመምራት ያላት ምኞት ነው›› ሲል ይከሳል (ዐብዱልጀሊል፤ 2012፡68)፡፡ ይህ ዘለሰኛ ከምን አኳያ በዚህ መልኩ ሊተረጎም እንደሚችል ግን ፍንጭም ሆነ ምንጭ አይጠቅስም፤ በራሱ ድምዳሜ ግን የማጥላላት ሥራውን ሰርቶበታል፡፡
በቅዱስ መጽሐፋችን ላይ የተጻፉ፣ እስልምናና ሙስሊሞቹ በምድረ ገጽ ላይ ከመከሰታቸው በርካታ ሺህ ዘመናት በፊትም የታመነባቸውን የክርስትና ጽንሰ ሀሳቦችንም በራሳቸው ጭንቅላት ልክ አጥብበው ለመሞገት ይዳዳቸዋል አክራሪዎቹ፡፡ ለምሳሌ፡- ‹‹እኛ የጨዋዪቱ የሣራ ልጆች (ይስሐቃውያን) ነን እንጂ የባሪያዪቲ የአጋር ልጆች (እስማኤላውያን) አይደለንም›› የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መነሻ ስብከት ‹‹ትምክህተኝነትና ትንኮሳ›› አድርጎ አሉታዊ አንድምታ መስጠት ተጀምሯል (ዐብዱልጀሊል፤ 2012፡67)፡፡
‹‹እስማኤላውያን›› የሚለውን ቃልም ሆነ ትርጉም ከአክራሪ ሙስሊሞቹ ጋር ለመኖር ስንል ከቅዱሳት መጻፍት ላይ ልንፍቅ አንችልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻም ሳይሆን እንደ ቅዳሴ ማርያም ባሉት መጻሕፍትም ላይ ቢሆን፡- ‹‹እግዚአብሔርን ‹አንድ ገጽ፣ አንድ አካል› የሚሉ እስማኤላውያንን እነሆ እንሰማቸዋለን…ልቦናቸውን ያሳወሩ ናቸው›› የሚል ቃል አለ፡፡ የዚህ ዐውዳዊ ፍቺ በክርስትና እምነት የማያምኑ፣ የእግዚአብሔርን አንድነት እንጂ ሦስትነት የማይቀበሉትን ሁሉ የሚያጠቃልል ነው፡፡ ይኸ ከሆነ ደግሞ ሙስሊሞችን ብቻም ሣይሆን ይህንን አስተምህሮ የማይቀበሉ ሌሎች ቤተ እምነቶችንም ጭምር ነውና ‹‹ሙስሊሞችን ለመተናኮል የተነገረ›› አስመስሎ ማቅረብ ትርፉ ድካም ብቻ ነው፡፡
አክራሪዎቹ በእስልምና መነጽር መቃኘት የጀመሩት ‹‹አረማዊ›› የሚል ቃል ያለባቸውን ማንኛቸውንም የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ጭምር ነው፤ ቃሉን ‹‹እስላም›› ከሚለው ጋር በአቻነት ተርጉመው ስለተቀበሉ፡፡ ጽንሰ ሀሳቡ ግን ‹‹አምኖ ያልተጠመቀውን ሁሉ›› እንጂ የተወሰኑ የእምነት ቡድኖችን ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ እነርሱ በተደጋጋሚ የሚጠቅሱትና ‹‹እስላም›› የሚለው በግልጽ የተጻፈበት ራዕየ ማርያም ደግሞ እነርሱ እንደሚሉት ‹‹ቤተ ክህነት ያሳተመችው›› (ዐብዱልጀሊል፤ 2012፡76) ሣይሆን ያለ ቤተ ክርስቲያኒቱ እውቅና በግለሰቦች ተነሳሽነት የተጻፈ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ለዚህ ማረጋገጫው ደግሞ በ1960 ዓ.ም ታትሟል የተባለው መጽሐፍ ዛሬ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ካለመኖሩም በላይ የአማርኛው ትርጉም ምንጭ በሆነው የግእዝ ጽሑፍ ላይ እንዲህ የሚል ጽርፈታዊ አገላለጽ አለመኖሩ ነው (አስፈላጊ ከሆነ ይህንን የሀሰት ትርክትና የቤተ ክርስቲያኒቱን ትክክለኛ ምላሽ የተመለከተ ጽሑፍ ወደፊት ለብቻ ለማስነበብ እንሞክራለን)፡፡
2.5. አቡነ ተክለ ሃይማኖትን እንደ አመጽ መሪ
————————————————–
ዐብዱልጀሊል (2012:84-85) ላይ፡- ‹‹አቡነ ተክለ ሃይማኖት የዛጔዌን ሥልጣን አስለቅቀው ‹ሰሎሞናዊውን› ሥልጣን ወደ ይኩኖ አምላክ ለመመለስ ጉልሕ ሚና ተጫውተዋል፤ ለነገሥታቱ ወደ ደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል መስፋፋትም አስተዋጽዖ አድርገዋል›› ብሎ ይከሳቸዋል፡፡ ይህንን ደግሞ ‹‹የአማራ ፖለቲካ›› ሲልም ይገልጸዋል፡፡ ጻድቁ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ታቦት የተቀረጸላቸውም ‹‹ለዚህ ውለታቸው ነው›› እስከማለትም ተዳፍሯል፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ግን ለዚህ ድምዳሜው ምንጭ አድርጎ የጠቀሰው የተስፋዬ ገ/አብን ‹‹የስደተኛው ማስታወሻ›› ተረት መሆኑ ነው፡፡
ለዚህ ጽሑፍ ግብዐት ሲባል ብቻ የአንዱን አክራሪ መጽሐፍ ጠቀስን እንጂ እንደ አህመዲን ጀበል ባሉት ግለሰቦችም እየተጻፉ ያሉ መጻሕፍትና የማኅበራዊ ሚዲያ ዲስኩሮች ከዚህ የተለዩ አይደሉም፡፡ እናም ምንም እንኳን ጉዳዩ የታሪክ መዛነፍ ቢመስልም ከታሪክነቱ ይልቅ ሃይማኖታዊ ትንኮሳነቱ ስለሚያመዝን ለየት ባለ ትኩረት ማየት የሚያስፈልግ ነው፤ ዛሬ የቤተ ክርስቲያኒቱን አይነኬዎችን እንዳሻቸው መዘርጠጥ የጀመሩበት አካሄዳቸው ነገ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ለማጤን አያዳግትምና፡፡
ምንም እንኳን ይህ በልዩ ርዕስ በስፋት ልንመለስበት የሚገባ ጉዳይ ቢሆንም ለጊዜው ግን የዚህን ትርክት ፍጹም ሀሰትነት ለአንባቢያን ለማሳየት ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ‹‹ኢትዮጵያዊው ሱራፊ-የአቡነ ተክለ ሃይማኖት የሕይወት ታሪክና አስተዋጽዖ›› በሚል (ጥር 2011 ዓ.ም) የጻፈውን 1,082 ገጾች ያሉት ድንቅ ምርምራዊ መጽሐፍ በደንብ እንዲያነቡ ለመጠቆም እንወዳለን ፡፡ መጽሐፉ ገና ሲጀምር ‹‹ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሚነገሩ የተለያዩ አመለካከቶች›› ብሎ መሰል ትርክቶችን በማስተባበል ሲሆን በተለይ ከገጽ.31-56 ያለው ይህንኑ ሀሳብ ብቻ በተጨባጭ ማስረጃዎች አስደግፎ የሚሞግት ነው፡፡
ሀሳቡም በአጭሩ ሲጠቃለል፡- እንኳንስ አጼ ይኩኖ አምላክን ሊነግሡ ይቅርና አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ ሸዋ የመጡት ንጉሡ ካረፈ በኋላ ድኅረ 1277 ዓ.ም እንደነበር (እንኳንስ ተገናኝተው ይህን ሁሉ የሤራ ፖለቲካ ሊዶልቱ ቀርቶ)፣ ንጉሡ ወደ ሥልጣን ሲመጣ እርሳቸው በዳሞት አከባቢ በስብከት አገልግሎት ላይ ይደክሙ እንደነበር (ምናልባት በጸሎት ተሳትፈው ካልሆነ በቀር)፣ ወደ ሸዋ (ደብረ አስቦ) መጥተውም በዋሻ ውስጥ እንደተቀመጡ (‹‹ታዲያ ‹ንጉሥ ቀይሮ ሢሦ መንግሥት የተቀበለ ሰው› ዋሻ ውስጥ ምን ይሰራል?›› ሲል ይጠይቃል)፣ የመጀመርያው የደብረ ሊባኖስ ቤተ ክርስቲያን የተሠራውም እርሳቸው (አቡነ ተክለ ሃይማኖት) ካረፉ ከ200 ዓመታት በኋላ በአጼ ይስሐቅ ዘመን እንደሆነ (እንኳንስ በቁማቸው ከይኩኖ አምላክ ሽልማት ሊቀበሉ፣ ጽላት ሊቀረጽላቸው ቀርቶ በስማቸው ገዳም መመሥረቱን እንኳን በወቅቱ እንዳልደረሱበት)፣ ወዘተ. በደንብ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት በተገኙ ተጨባጭ ማስረጃዎች በማቅረብ የአክራሪ ሙስሊሞቹንና የዘመኑን የጎጥ ፖለቲከኞች ትርክት ራቁቱን አስቀርቶታል፡፡
2.6. የቤተ ክርስቲያን ታሪክን የማፋለስና የማጠልሸት ጥረቶች
————————————————————
አክራሪ ሙስሊሞቹ የሀገሪቱን ታሪክ ብቻ ሣይሆን በማያገባቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ውስጥም ገብተው ለመፈትፈት፣ ሆን ብለውም ለማፋለስ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ የሁሉንም ጸሐፍት ለመዘርዘር ቢያዳግትም በቅርቡ በዐብዱልጀሊል ዐሊ የተጻፈውን ‹‹ተምኔታዊ ደሴት›› መጽሐፍ (ጥር 2012 ዓ.ል) እንኳን ስንመለከት የሚከተሉትን ዋና ዋና ሕጸጾች እናገኛለን፡-
• ‹‹የአርዮስ ተከታዮች በአክሱማውያን ቤተ መንግሥት ነበሩ›› ይለናል (ገጽ.43)፡፡ በተቃራኒው የቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ የሚነግረን ግን የአርዮስን ትምህርት በማውገዛቸው ምክንያት ስደት የደረሰባቸው ተሰዓቱ ቅዱሳን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ሕዝቡን ማስተማራቸውን፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ከተለያዩ ቋንቋዎች መተርጎማቸውን፣ ገዳማትን መገደማቸውን፣ ወዘተ. ነው፡፡
• ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባበትን ጊዜ 334 ከማድረጉም በላይ ያኔም ቢሆን ክርስትና ‹‹ገባባት›› የተባለችው ኢትዮጵያ ግን የዛሬዋ አይደለችም ሲል ይገልጻል (ገጽ.26)፡፡ በጸሐፊው የተጠቀሰው ግን ክርስትና የገባበት ሣይሆን አብርሃና አጽብሐ ‹‹ብሔራዊ ሃይማኖት›› አድርገው ያወጁበት ዘመን ነው፡፡ በዚያን ወቅት ከዚህች ሀገር ውጭ ‹‹ኢትዮጵያ›› የምትባል ሌላ ሀገር መኖሯንም የሚጠቁም የታሪክ ድርሳን አይገኝም (የመልክዓ ምድር ስፋትና ጥበት ልዩነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ)፡፡
• ክርስትናን ወደ ኢትዮጵያ ይዘውት ገቡ የሚለው ሶርያውያንን ነው (ገጽ.27)፡፡ ምናልባትም ሥልጣነ ክህነትን (መንበረ ጵጵስናን) ከመንበረ ማርቆስ ካመጣልን ከሶርያዊው ፍሬምናጦስ (አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን) ታሪክ ጋር ተምታቶበት ሊሆን ይችላል እንጂ ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባው ግን በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ (የንግሥት ህንደኬ ገንዘብ ሚኒስቴር) መሆኑ ግልጽ ነው (ሥራ.8፡26-41)፡፡
• ፊልጶስ ያጠመቀው አንድ ኢትዮጵያዊ ብቻ እንደሆነ ይጠቅሳል (ገጽ.27)፡፡ የቤተ ክርስቲያንና የዓለም ታሪክ ድርሳናት ግን ‹‹እንኳንስ ያኔ ቀርቶ ዛሬም ቢሆን አንድ ባለሥልጣን ብቻውን አይንቀሳቀስም፤ ባለሥልጣኑ የተቀበለውን ነገር ደግሞ ተከታዮች ሊያፈነግጡ አይችሉም›› በሚለው አመክንዮ መሠረት ባለሥልጣኑን አጅበው ወደ እስራኤል አቅንተው የነበሩ በርካታ ዜጎች አብረው እንደተጠመቁ፣ ወደ ሀገራቸው ገብተውም ወንጌልን በተለያዩ የሀገሪቱ አቅጣጫዎች እንዳስፋፉ ይስማማሉ፡፡
• ‹‹እስልምና በአፍሪካ ቀንድ የተስፋፋው ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሲሆን በተቃራኒው ግን ክርስትና የተስፋፋው በማስገበር (Conquest) ነበር›› ብሎ የራሱን ገመና ወደ ሌላው ለማላከክ ሞክሯል (ገጽ.125):: ጥንቱን እስልምና የተስፋፋው በሰላማዊ መንገድ ከሆነ አሁን ላይ ደርሶ ለምን ወደ ኋላ መመለስ (በኃይል መታገዝ) ጀመረ? ያሰኛል፡፡ እንደሚባለው እስልምና ‹‹የሰላም ሃይማኖት›› ከሆነስ ‹‹ሀበሾችን አትንኩ›› የሚለውን የነቢዩን ንግግር ራሱ ምን አመጣው? ብለን እንድንጠይቅም ያስገድደናል፤ ‹‹አትንኩ›› የሚለው ትእዛዝ ቀድሞ ነገር ‹‹መንካት/ማጥቃት ልማድ መሆኑን›› የሚጠቁም ነውና፡፡
• ‹‹ቀሳውስት የጥላቻና የጦርነት ስብከቶች አድርገው፣ ጦረኛ የሃይማኖት ነገሥታትን ፈጥረው አወድሰውና አጀግነው ከኦርቶዶክስ ውጭ ባሉ የኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ ጦርነት ያዘምታሉ፤ ቀሳውስትም ታቦት ተሸክመው ጦር ሜዳ ይወርዳሉ›› ብሏል (ገጽ.130-131)፡፡ ጸሐፊው ይህን መሰል ትልቅ ድምዳሜ ላይ ሲደርስ ግን አንዳችም ማስረጃና ምንጭ ሳይጠቅስ መሆኑ ነገሩን ‹‹ተረት›› ያደርገዋል፡፡ ምናልባት ለማለት የተፈለገው ታቦተ ጊዮርጊስ የተሳተፈበትን የዓድዋ ጦርነት ለማለት ከሆነ ደግሞ ውጊያው የተካሄደው ከጣሊያን ጋር እንጂ ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር አይደለም፤ ሀገራዊም እንጂ እስልምናዊ አንድምታም አልነበረውም፡፡
2.7. ‹‹አንዱ በጋሻ ሌላው በትከሻ››—የሙስሊሞቹ አዲስ የይዞታ ክስ
————————————————————–
ከጥንትም ጀምሮ አክራሪ ሙስሊሞቹን የእግር እሳት ሆኖ ሲለበልባቸው የሚኖረው ቀደምት የኢትዮጵያ ነገሥታት በዚህች ሀገር ውስጥ ኦርቶዶክስን ‹‹መሬት አስይዘው›› የማለፋቸው ጉዳይ ነው፤ በእነርሱ አመለካከት በቀላሉ ተገፍታ ልትጠፋ በማትችልበት ሁኔታ፡፡ ለዚህ ማሳያ አድርገው የሚያቀርቡት ደግሞ በተለያዩ የሀገሪቱ አቅጣጫዎች የተከሏቸው አብያተ ክርስቲያናት፣ የገደሟቸው ገዳማትና የመሠረቷቸው የአብነት ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ እነዚህ መሠረታዊ ነገሮች ዛሬም ድረስ ላለው የመንፈሳዊ አገልግሎት መቀጠል ዋና ምክንያት ከመሆናቸውም ባሻገር ዛሬ በቀላሉ ሊገኙ የማይችሉ ይዞታዎች በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሥር እንዲካለሉ አድርገዋል፡፡
በአንጻሩ ደግሞ የእስልምና ተቋማትን የመመሥረትና ይዞታዎችን የማረጋገጡ ሂደት ተግዳሮቶች ነበሩ ሲሉ ነገሥታቱን ይከሳሉ አክራሪዎቹ፡፡ ለዚህ እንደማሳያ ከሚያነሷቸው ነጥቦች መካከል ‹‹በአክሱም ዛሬም ድረስ መስጊድ የለም›› የሚለውን ነው፡፡ በእርግጥም የቤተ ክርስቲያናችን 5ኛ ፓትርያርክ የነበሩት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ (የሀገሪቱ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ናቸው የተናገሩት የሚሉ ቢኖሩም) ይህንኑ ጉዳይ ተጠይቀው የሰጡት ምላሽ፡- ‹‹ይህ የሚሆነው በመካ ቤተ ክርስቲያን ሲተከል ነው፤ ለእነርሱ ቅዱስ ቦታቸው በዚያ እንደሆነ ለእኛ ደግሞ አክሱም ቅድስት ቦታችን ናት›› ማለታቸው ተዘግቧል፤ (አባ ሳሙኤል፤ በኢትዮጵያ የሃይማኖት መቻቻል አለን? 2000፡50)፡፡ በዚያ ያንን ማሰብ ካልተቻለ በዚህ ይህንን ማድረግ ይከብዳል ማለታቸው ነው፤ ‹‹መቻቻል›› የሚባለው መፈክር ሁለቱንም በዚህ አግባብ ካላስተናገዳቸው በቀር ዋጋ የለውምና፡፡ በመካ ቤተ ክርስቲያንን መትከል ‹‹ፈጽሞ የማይታሰብ›› ከሆነ ደግሞ ይህኛውም የሚገርም አይሆንም፤ ደግሞም ለኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ጽላተ ሙሴ ከከዓባ ድንጋይ ይልቅ እጅግ ትከብራለችና፡፡
ያም ሆነ ይህ ከዚህን በፊት የነበረው የሙስሊሞቹ ጥያቄ መስጊድ የመሥራት መብታችን አልተከበረልንም፤ የመቃብር ቦታ አልተሰጠንም የሚል ነበር፡፡ ይህ በተግባር ከመረጋገጥም አልፎ ከእምነቱ ተከታዮች ቁጥር አንጻር ሲታይ የአብያተ ክርስቲያኑንም ቁጥር እየበለጠው መምጣቱ ይፋ ሲሆን ደግሞ ሌላ ትንኮሳ ጀመሩ፤ ‹‹አሁን የመስጊድ ቁጥር ብቻ ሣይሆን እያንዳንዱ መስጊድ የእያንዳንዱን ቤተ ክርስቲያን ያህል ስፋት ያለው ቦታ ሊኖረው ይገባል›› የሚል መፈክር እየተቀጣጠለ ነው፡፡
በቅርቡ ብቅ ማለት የጀመረው ይህ ጥያቄአቸው በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የአብያተ ክርስቲያናትና የመስጊዶችን ይዞታ (የቦታ ስፋት) በካሬ እያነጻጸሩ ‹‹አድልዖ ተፈጽሞብናል›› በሚል መቀስቀስ ነው፡፡ ይህንን አቋማቸውን ደግሞ ከማሰብና ከመናገር አልፈው ወደ ጽሑፍ አሳድገውታል፡፡ ‹‹የእምነት ተቋማት ይዞታ— አንዱ በጋሻ ሌላው በትከሻ›› በሚል ርዕስ ተንኳሽ ጽሑፍ ማስነበባቸው የዚህ ማሳያ ነው፡- የአዲስ አበባ መሬት ለኦርቶዶክሱ በጋሻ ሲቸረው፣ እነርሱ ግን መሬት ሊባል የሚችል ሰፊ ይዞታ ሳይኖራቸው አየር ላይ (በትከሻ) ታዝለው እንደተቀመጡ አስመስለው፣ በመጽሔት አሳትመው ለሕዝብ አሰራጩ (ቀሠም፤ ሰኔ 2011 ዓ.ል፤ ቅጽ-1፣ ቁጥር 06)፡፡ በዚህ መጽሔት ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙት የብዙ መስጊዶች ቦታ ሲደመር ከአንድ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር ተመሳሳይ መሆኑ ተጠቅሶ ለማሳጣት ሙከራ ተደርጓል፡፡ አሁን የሙስሊሙ ቁጥር ከክርስቲያኑ ጋር ተቀራርቧል ብለው ‹‹የቦታ ይዞታ ምጣኔ›› ማስላት ከጀመሩ፣ በዚህ አያያዛቸው ነገ ቁጥራቸው ከዚህም በላይ ሲያሻቅብ ደግሞ ‹‹በቁጥራችን መሠረት የመሬት ስፋቱ እንደገና ተለክቶ ይከፋፈልልን›› በሚል ከነባሩ የአብያተ ክርስቲያናት ይዞታ ጭምር ተቆርሶ እንዲሰጣቸው ላለመጠየቃቸው ምንም ዋስትና የለም፡፡
በሌላ መልኩ ጥንት በነገሥታቱ ዘመን የተተከሉትን አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ጭምር አሁን ባለው መንግሥት ሕግ መሠረት ለመዳኘትም እየዳዳቸው ነውና ሀገሪቱን በአዲስ መልክ አፍርሰን እንሥራት ሳይሉ የሚቀሩ አይመስሉም፡፡ ለምሳሌ፡- አስቀድሞ በተጠቀሰው መጽሔታቸው ‹‹በአምልኮ ማካሄጃ ቦታ አፈቃቀድ መመሪያ ቁጥር 1/2010 መሰረት የአምልኮ ማካሄጃ ቦታ ስፋት ከ2000 እስከ 4000 ካሬ ሜትር ነው… በተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት መካከል ሊኖር የሚገባው ርቀት 500 ሜትር ሬድየስ መሆን ይኖርበታል፡፡›› ብለው የኢህአዴግን ሕግ የሚጠቅሱት ለዘመነ ምኒልክ አብያተ ክርስቲያናት ጭምር መሆኑ ነገሩን አስገራሚ ያደርገዋል፡፡ ሕግ ወደኋላ አይሰራም እንጂ ይሥራ ከተባለ ደግሞ ወደ ትክክለኛው የንጉሥ አርማህ (በእነርሱ ‹‹ነጃሺ››) ዘመን መመለስም ይመጣና ያን ጊዜ ‹‹በሀገሪቱ ገብታችሁ በሰላም ተቀመጡ ተባላችሁ እንጂ መስጊድ እንድትሠሩ ማን ፈቀደላችሁ?›› መባልም ሊመጣ ነው ማለት ነው፡፡
በአንጻሩ ይህንኑ የዘመኑን ሕግ እንኳን ሌላውን ለመክሰስ ያህል ይጠቀሙበታል እንጂ ራሳቸውም ሲያከብሩት ግን አይታዩም፡፡ ለምሳሌ፡- እንደ አዲስ አበባ ያሉ ትልልቅ ከተሞች በወጥ ማስተር ፕላን የሚመሩ፣ ለቤተ እምነቶች መፈቀድ የሚችሉና የማይችሉ ቦታዎች አስቀድመው በካርታው ላይ የሚተለምባቸው ሆነው ሳለ ሙስሊሞቹ ግን ከዚህ በተቃራኒ የግለሰቦችንና እድር ቤት ይዞታዎችን ገዝተው ወደ መስጊድነት መቀየር የተለመደ ተግባራቸው ነው፤ ራሳቸው በሚያዘጋጇቸው ሰነዶችም ጭምር ይህን መሰል ስትራቴጂ እንደሚጠቀሙ ደጋግመው ሲጽፉና ‹‹በገዛ ገንዘባችን የገዛነው ነው›› እያሉ በኩራት ሲናገሩ አንዳችም የሕገ ወጥነት ስሜት አልተሰማቸውም፡፡ እንደ አቡ ሱመያ ያሉ መስሊሞች (‹‹የመስጂዶች ታሪክ በአዲስ አበባ›› መጽሐፍ ጸሐፊ) ‹‹…አብዛኞቹ መስጂዶች የግለሰቦች ቤትና ይዞታ፣ ስጦታ፣ የእድር ቦታዎች፣ በህብረት ተከራይተው የሚሰገዱባቸውና በለጋስ ግለሰቦች እርዳታ ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው›› እያሉ ሲጽፉ ‹‹መንግሥት ሕጋዊ ቦታ ስላልሰጠን የራሳችንን እርምጃ ወስደናል›› በማለት መንግሥትን ለመክሰስ ነበር፡፡ ይህ እውነታነት ያለው ንግግራቸው በአግባቡ ሲጤን ግን መልሶ እነርሱኑ የሚያስከስስ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ምክንያቱም ከግለሰቦች በስጦታም ሆነ በራስ ገንዘብ ተገዝቶ መደበኛው ካርታ በቤተ እምነት ይዞታነት ያላካተተውን ቦታ ወደ መስጊድነት መቀየር ራሳቸው ይደግፋቸው ዘንድ ከሚጠቅሱትም ሕግ ውጭ ነውና! ባልተፈቀደ ቦታ ላይ ጨለማን ተገን አድርገው በግለሰቦች መኖርያ ላይ ጨረቃ ሰቅለው ካደሩ በኋላ ‹‹ከካርታ ውጭ ነው የሰራችሁት›› ሲባሉ ደግሞ ‹‹የክርስቲያኑ መንግሥት አፈረሰብን፣ በገዛ ቦታችን ሕጋዊ ሰነድ ተከለከልን፣ እስልምና በልዩ ሁኔታ እየተገፋ ነው!›› የሚል የተለመደ ልቅሶአቸውን ያቀልጡታል፤ ዜጎችም እውነታው እስኪጣራ ድረስ በዚህ መወዛገባቸው ይቀጥላል፡፡
3. የኢትዮጵያ ታሪክን በአዲስ መልክ ለመከለስ የሚደረጉ ጥረቶች
======================================
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከአክራሪ ሙስሊሞቹ ሰፈር የሚነገሩና የሚጻፉ መልእክቶች የትናንት ታሪካዊ ኩነቶችና ግንዛቤዎች በዛሬ ተጨባጭ መነጽር እንዲታዩና በዘመናችን ሕጎችም እንዲዳኙ የሚጠይቁ፣ የሀገሪቱም ታሪክ በአዲስ መልክ ተከልሶ እንዲጻፍ የሚገፋፉ ናቸው፡፡ በነገሥታቱ ዘመን የነበሩ ክስተቶችን ከብዙ ሺህ ዓመታት በኋላ በተፈለሰፈው ሚዛን ለመመዘን፣ በዚያው አግባብም ለመፍረድ ይቃጣቸዋል፤ የታሪክን አጠናን ያለማወቅ ችግር፣ አውቆም ለመተግበር አለመፈለግ ትልቅ የአክራሪዎች ደዌ! እስልምናን በተራው የበላይ የምታደርግ አዲስ ኢትዮጵያ መመሥረት፣ እንደ ወራሪና ጨፍጫፊ ይታዩ የነበሩትን አካላት በጀግና መዝገብ ላይ ማስፈር፣ ያልነበረን ንጉሥ በምናብ ፈጥሮ ማንገሥ፣ ወዘተ. የዚህ እንቅስቃሴ አካል ናቸው፡፡ እንደሚከተለው አሳጥረን እንመልከታቸው፡-
3.1. ‹‹አዲሲቷን ኢትዮጵያ›› የመመሥረት ዒላማ
—————————————————-
አሁን አሁን ብቅ ማለት በጀመሩት ኢትዮጵያውያን አክራሪ ሙስሊሞች ከሚቀነቀኑት ሀሳቦች መካከል ሌላኛው ነጥብ የአሁኗ ኢትዮጵያ ከጥንቷ የተለየች የመሆኗ ጉዳይ ነው፡፡ በእነርሱ አመለካከት የጥንቷ ኢትዮጵያ (በተለይ ከአጼ ይኩኖ አምላክ በፊት የነበረችው) ለእስልምናና ሙስሊሞች ያላት ቦታ ጥሩ የነበረ ሲሆን ከዚህ ዘመን (በእነርሱ አገላለጽ ‹‹የሸዋ ሥርወ መንግሥት››) በኋላ ግን ነገሮች ተገለባብጠው ‹‹የአማራ ኦርቶዶክስ›› ምሥረታና ክርስቲያናዊ ርእዮተ ዓለም ብቻ ሲቀነቀን ቆይቷል ባይ ናቸው፡፡ አጼ ይኩኖ አምላክን እንደ መለያ መሥመር ለመጠቀም የፈለጉትም አስቀድሞ እንደተገለጸው በኢትዮጵያ ክርስትና ዘንድ ትልቅ ቦታ ያላቸውን ጻድቅና ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ለመተናኮል ስለፈለጉ ነው፡፡
አንዳንዶች ደግሞ (ለእስልምና ያላትን አቋም አስመልክቶ) የኢትዮጵያን ከጥንትነቷ መንሸራተት ይቀበሉና ጊዜውን ግን ቀረብ ያደርጉታል፡፡ ለምሳሌ፡- Najib Mohammed የተባለ ግለሰብ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካይነት በሚታተመው ‹‹ሰላምታ መጽሔት›› ላይ (ነሐሴ 03 ቀን 2004 ዓ.ም ባቀረበው ድረ ገፅ ላይም ጽሑፉ ይነበባል)፡- በአስራ አራተኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ የሰባት እስላማዊ ሱልጣኔቶች አገር እንደነበረች ጠቅሶ አሁን የምናያት ኢትዮጵያ በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ በፖርቱጋሎች እርዳታ እንደተመሰረተች አቅርቦልናል፡፡ በእርግጥ ይህኛው አመለካከት ምናልባትም መልክዓ ምድራዊ አከላለሏ ለመጨረሻ ጊዜ የተጠናቀቀበትን ጊዜ ለመጥቀስ ካልሆነ በቀር ቢያንስ እነርሱ ራሳቸው ‹‹እስልምና ወደ ኢትዮጵያ የገባው በ7ኛው መ/ክ/ዘመን ነው›› ብለው የሚያምኑትን ትተው ‹‹ኢትዮጵያ በዚያን ጊዜ አልነበረችም›› ሊሉን የሚደፍሩ አይመስለንም፡፡
የዘመናችን አክራሪ እስልምና ጸሐፍት የሀገሪቱን የቀድሞ ታሪኮችንም በአብዛኛው ‹‹ተረት ተረቶች›› ሲል ይገልጹአቸዋል (ዐብዱልጀሊል፤2012፡15)፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ነጥሎ ማየት አለመቻል›› የሚለውን እንደ ትልቅ ክስ ያቀርባሉ (ዐብዱልጀሊል፤2012፡79)፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክን በትክክል እናጥና ከተባለ ግን አዎ፤ እነዚህን ሁለቱን ነጣጥሎ ማየት ምን ማለት እንደሆነ ይህንኑ ሞክረው ‹‹በእሳት እንደመጫወት›› የሆነባቸውን ቀደምቶቻቸውን እንዲጠይቁ መጠቆም ተገቢ ይሆናል፡፡
ያም ሆነ ይህ አዲስ የኢትዮጵያ እስልምናን ታሪክ የምትጽፍ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ትኖር ዘንድ በየዕለቱ የሚፈበረኩ ተረቶች እየበዙ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ እስልምና ወደ ኢትዮጵያ የገባው እንኳን በታሪክ ከተመዘገበው 615 በፊት እንደሆነ ለመከራከር እየዳዳቸው ነው፤ ተጨባጭ ምስክር የላቸውም እንጂ፡፡ ይህንን የሚያደርጉት ‹‹ጥንቱንም የሙስሊም ሀገር ነበረች›› ለማስባል ይመስላል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በመንግሥት ደረጃ የሚወጡ ኦፊሴላዊ መረጃዎችን (በተለይም የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤቶችን) ፖለቲካዊ ውሳኔ እንጂ ትክክለኛ ቁጥራችን አይደለም በሚል ለመቀበል የማይፈልጉትም ‹‹ለምን የሙስሊሙ ቁጥር በልጦ አልመጣም?›› በሚል ነው (ዐብዱልጀሊል፤ 2012፡7)፡፡
እናም በእነርሱ አመለካከት መሠረት፡- ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ›› ተቀባይነት ሊኖረው የሚችለው ኢትዮጵያ ጥንቱን የእስልምና ምድር መሆኗን ሲያውጅ፣ ልጅ ኢያሱ ‹‹ያልተዘመረለት ንጉሥ›› የሆነው ‹‹ለእስልምና ካለው አዎንታዊ አመለካከት›› የተነሣ ስለሆነ የእርሱ ገናንነት ጎላ ብሎ ሲወጣ፣ እንደ አጼ ዮሐንስ ዓይነቶቹ ነገሥታት የወሎ ሙስሊሞችን ‹‹የጨፈጨፉበት ታሪክ›› ጠንከርና በርከት ብሎ ሲጻፍ፣ በአድዋ ጦርነት ላይ የተዋደቁት አብዛኞቹ ሙስሊሞች እንደሆኑ እንጂ የክርስትናው ሚና (የጳጳሳቱ ቡራኬ፣ የካህናቱ ማጀገኛ ኑዛዜና የታቦተ ጊዮርጊስ ፊታውራሪነት) ሲደበዝዝ፣ ወዘተ. ብቻ ነው፡፡
ሲጠቃለል ግን ‹‹አዲሲቷን ኢትዮጵያን›› ምን አስናፈቃቸው? ብለን ስንጠይቅ ኦርቶዶክሳዊነትን እንደ መነሻ ሳትጠቅስ ታሪኳን መናገር የማትችል ኢትዮጵያን አፈራርሰው የእስልምናን የበላይነት የሚያውጅ ታሪክ ያላትን ሀገር ለመፍጠር የሚደረግ ሤራ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ መልኩ ሀገርን አፍሶ መሥራት ደግሞ መጽሐፍ እንደመጻፍና ሚዲያ ላይ ወጥቶ እንደመደስኮር ቀላል አይደሉም፡፡ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ በሚደረገው ጫጫታና በሰላማዊ ሰልፍ ጋጋታም ሊሳካ የሚችል አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ጉዳዩን ቀለል አድርጎ ማየትም አስፈላጊ አይደለም፡- የእነርሱም ስትራቴጂካዊ መፈክር እንደሚገልጸው የዛሬዎቹ ትግሉን በዚህ መልኩ ከጀመሩት፣ ነገ የሚወለዱት ልጆቻው ሊያሸንፉ፣ የልጅ ልጆቻቸው ደግሞ ዓለምን በእስልምና ሊወርሱ ይችላሉና!
3.2. ታሪካዊውን የኢትዮጵያ መከራ መናፈቅ፡- ‹‹ውዳሴ ግራኝ አህመድ ወዘመነ መሳፍንት››
———————————————————————-
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የግራኝ አህመድ ተግባራት ትክክል እንደሆኑ፣ ይኸው ታሪክ ዛሬም ለኢትዮጵያ እንደሚያስፈልጋት አድርገው ወንጀለኛውን እንደ ጻድቅ የማሞጋገስ አካሄዶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ እንዲያውም በሀገሪቱ ታላላቅ ሲኒማ ቤቶችና መሰብሰቢያ አዳራሾች ጭምር ግራኝ አህመድን የሚያወድሱ መድረኮች በልዩ ሁኔታ እያስተዋልንም ነው፡፡ በ2011 ዓ.ም እንኳን ግራኝን የሚያወድስ የኪነ ጥበብ ዝግጅት በአዲስ አበባ ተዘጋጅቶ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ከዚያም ባሻገር በተገኙት ሰልፎችና በየጁምዓ ቀናቱ በተሰበሰቡ ቁጥር ‹‹እኔም ግራኝ አህመድ ነኝ›› የሚሉ የባነር መፈክሮችን ይዘው የሚታዩ ወጣቶችንም ስናስተውል ‹‹ወዴት እያመራን ነው?›› ያስብላል፡፡ ይህ የወጣቶች አዲስ እንቅስቃሴ ደግሞ የሚመራው በምሁራን ነን ባይ አክራሪዎች የሀሰት ትርክት መሆኑን የምንገነዘበው፡- ‹‹ኢማም አህመድ ኢብራሂም (ግራኝ) ሰሎሞናዊውን መንግሥት ድል አድርገው ሥልጣኑን ሲይዙ የተኮነኑትም ሆነ ስማቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ በጥዋትና በሌሊት ቅዳሴ የሚጠፋው ከዚሁ ጋር በተያያዘ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል›› ብለው ስለቀሰቀሱ ነው (ዐብዱልጀሊል፤ 2012፡109)፡፡ ይኸው መጽሐፍ ግራኝ አህመድ እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ነገሥታት ‹‹አጼ›› መባል እንዳለበት ይሞግታል፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥም ‹‹ወራሪ›› ተብሎ መገለጹን ይቃወማል፡፡ ይኸው ሀሳብ የተጋባባቸው የዘመናችን አክራሪ ሙስሊም ወጣቶችም ‹‹እኔም ግራኝ አህመድ ነኝ!›› የሚል የቲሸርት መፈክር አሳትመውና ለብሰው በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ታይተዋል፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ ዘንድሮ (ጥር 24 ቀን 2012 ዓ.ም በመርሳ ከተማ፣ ወሎ ውስጥ) ‹‹የኢማም አህመድ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ›› በሚል የመሠረት ድንጋይ መቀመጡን እየሰማን ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እውነት ከሆኑና በቸልታ እየታለፉ ከመጡ ሀገሪቱ ወዴት እያመራች ነው? ያሰኛል፤ ውጤቱን አብረን የምናየው ይሆናል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ በየጎጡ ተከፋፍሎ የኢትዮጵያን አንድነት ይፈታተን የነበረውን የዘመነ መሳፍንት ታሪክ አክራሪው እስልምና የሚናፍቀው ሌላ ክስተት ሆኗል፤ ‹‹ሁሉን አካታች የነበረ የስኬት ዘመን›› በሚል (ዐብዱልጀሊል፤2012፡106)፡፡ እንደ እውነቱ አንዳንድ የሙስሊም ሱልጣነቶች በየግዛታቸው የማዘዝ ሙሉ ሥልጣን ስለነበራቸው ካልሆነ በቀር ‹‹ሀገር›› የምትባለውን የአንድነት ድንኳን ለመፍጠር ምንም ዓይነት ፍላጎት በዘመነ መሳፍንት እንዳልነበር ታሪክን የሚያውቁ ሁሉ የሚመሰክሩት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ደግሞ ከክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጋር ሆነው ለዚህች ሀገር ዳር ድንበር መከበር በጋራ ሲዋደቁ እንደነበሩ እንጂ በዚህ መልኩ ‹‹የተከፋፈለች ሀገር›› የተመኙበት ዘመን ከታሪክ አላነበብንምና ‹‹እስልምና በኢትዮጵያ ልዩ ጠባይ እያመጣ ነው›› ለሚለው ድምዳሜአችን አንዱ ማሳያ ይኸው የዘመነ መሳፍንት ዳግም ምጠት ፍላጎታቸውን ባጤንን ጊዜ ነው፡፡
3.3. ‹‹አልነጃሺ››፡- ምናባዊው ሙስሊም ንጉሥ በኢትዮጵያ
————————————————————
በአክራሪዎቹ እየተውጠነጠነ ያለው አዲሱ የኢትዮጵያ ታሪክ፡- ‹‹በመጀመርያዎቹ የሙስሊሞች ስደት ወቅት የተቀበላቸው ንጉሥ ሰልሟል፤ የመጀመርያው ሙስሊም የኢትዮጵያ ንጉሥም ሆኗል›› የሚለው ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ የእስላም አገር ናት ወደሚለው ታሪክ ያንደረድራል ማለት ነው፡፡
ለምሳሌ፡- በቅርቡ ‹‹ተምኔታዊ ደሴት›› በሚል በኢትዮጵያ ክርስትና ላይ ትችት የጻፈው ዐብዱልጀሊል ዐሊ ‹‹ኢትዮጵያ የመጀመርያው ሙስሊም ንጉሥ ሀገር መሆኗ ምንም ጥርጥር የለውም›› በማለት ትርክቱን እንደወረደ ተቀብሎ አስተጋብቷል (2012፡32፣115)፡፡ በኢትዮጵያ የነበረውን እስልምና ከጥንስሱ እስከ ድፍርሱ አፍረጥርጠው ያጠኑት ምሁራን ግን እንኳንስ ንጉሡ ሊሰልም ቀርቶ ወደ ኢትዮጵያ ሸሽተው ከመጡት የመጀመሪያዎቹ የነቢዩ ተከታዮች መካከል በፈቃዳቸው ወደ ክርስትና የተመለሱ እንዳሉ ነው የጻፉት፤ ከእስልምና ወደ ክርስትና የተመለሱ የመጀመርያዎቹ ሰዎች መሆናቸውንም መስክረዋል (Trimingham, P.45)፡፡ የአክራሪዎቹ ውሸት ተደጋግሞ በትውልዱ ጆሮ እየገባ ‹‹ታሪክ›› ወደመሆን ሊሸጋገር ሲል ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶሷ አማካይነት መክራ፣ በተጨባጩ የሀገሪቱ ታሪክ ላይ ተመሥርታ፣ መጻሕፍትን በማስረጃነት ጠቅሳ ‹‹በኢትዮጵያ የሰለመ ንጉሥ የለም፤ ነጃሺ የሚባል ንጉሥም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አልነበረም›› የሚል ቁርጥ ያለ መግለጫዋን አውጥታለች፡፡
ተረቱን ታሪክ የማስመሰል አካሄዳቸውን በጽሑፍና በንግግር ብቻም ሣይሆን በፊልሞችም ጭምር እያቀነባበሩ ለዓለም ለማሳወቅ እየጣሩ ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ‘Untold Ethiopia an Islamic Journey’ በሚል ርእስ Dr. Abdullah Hakim በተባለ አሜሪካዊ የተሠራው ‹‹ጥናታዊ›› ዘገባ ነው፡፡ የፊልሙ ዋና ጭብጥ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እስልምና ተገቢውን ትኩረት አግኝቶ በበቂ ሁኔታ እንዳልተዘገበ ማሳየት እንደሆነ ለማወቅ ይቻላል፡፡
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ እስልምና አስቀድመው ከተጠቆሙትና በአክራሪ ሙስሊሞቹ ከሚቀነቀኑት ነጥቦች የተነሣ ነባር እሴቶቹን እየተነጠቀ፣ ከክርስቲያን ወገኖቹም ጋር በሰላም ለመኖር እየተቸገረ መምጣቱ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እየኖሩ በአረብ ጭንቅላት ማሰብ፣ ያልተለመዱ የጭካኔ ጥቃቶችን በገዛ ወገን ላይ መሰንዘር፣ ታሪክን እያጣመሙ መጻፍና መሰል ትንኮሳዎችን መፈጸም የአንድነቱን ገመድ የሚያላላ፣ ነባሩንም የአብሮነት እሴት የሚያደበዝዝ ስለሆነ ሁሉም ቆም ብለው እንዲያስቡ ለመጠቆም እንወዳለን፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.